በክረምቱ የዝውውር ገበያ በንቃት እየተሳተፉ ካሉ ክለቦች መካከል በዋነኝነት የሚጠቀሰው ፋሲል ከተማ ሙጂብ ቃሲምን ስድስተኛው ፈራሚው አድርጎታል።
በአዳማ ከተማ ከምኞት ደበበ ጋር ጠንካራ የመሀል ተከላካይ ክፍል በመፍጠር በቀላሉ ግብ የማያስተናግደው ቡድን ውስጥ ትልቅ አስተዋፅዖ የነበረው ሙጂብ አልፎ አልፎ በፊት አጥቂነትም ክለቡን በማገልገል ግቦችን ያስቆጥር እንደነበር ይታወሳል። ግዙፉ የመሀል ተከላካይ በሲዳማ ቡና ፣ ሀዋሳ ከተማ እና አዳማ ከተማ ከነበረው ቆይታ በተጨማሪ ለዋልያዎቹም ተመርጦ መጫወት ችሏል።
ፋሲል ከተማ በተደጋጋሚ ጉዳት የሚጠቃው የመሀል ተከላካዮቹን ጥምረት ለማደስ በሚመስል መልኩ ከከድር ኩሊባሊ በኋላ ሙጂብን ሁለተኛው የቦታው ፈራሚ አድርጎታል። በመሆኑም ክለቡ ውሉ የተራዘመው ያሬድ ባየህን ጨምሮ በመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ ለመካተት ብቃት ያላቸውን ተጨዋቾች በመያዝ የቦታውን ክፍተት በሚገባ የሸፈነ ይመስላል። በእስካሁኑም የዝውውር መስኮት ቡድኑ አሰልጣኝ ውበቱ አባተን ከሾመ በኋላ በዛብህ መለዮ፣ ሐብታሙ ተከስተ ፣ ሽመክት ጉግሳ ፣ ከድር ኩሊባሊን ፣ ሰለሞን ሀብቴን ማስፈረሙ ይታወሳል።