ከአሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም ጋር እንደሚቀጥል የታወቀው ወልዋሎ ዓ.ዩ ግዙፉን የደደቢት ግብ ጠባቂ በእጁ አስገብቷል።
በተጠናቀቀው የውድድር አመት ሊጉን የተቀላቀለው ወልዋሎ በሀገር ውስጥ ግብ ጠባቂዎች ከሚጠቀሙ ጥቂት ክለቦች መካከል አንዱ እንደነበር ይታወሳል። በዚያ ወቅት የቡድኑ ዋነኛ ግብ ጠባቂ የነበረው በረከት አማረ ለብሔራዊ ቡድን እስከመመረጥ ያደረሰውን ብቃት ማሳየት ችሎ ነበር። ሆኖም በሁለተኛው የውድድር አጋማሽ በተለይም በረከት በመከላከያው ጨዋታ በተፈጠረው ግርግር ቅጣት ከተላለፈበት በኋላ ዘውዱ መስፍን እና በአመቱ አጋማሽ ቡድኑን የተቀላቀለው ዮሀንስ ሽኩር ቦታውን ሸፍነው ተጫውተዋል።
በሁለቱ ግብ ጠባቂዎች ብቃት ያልረኩ የሚመስሉት ወልዋሎዎች አሁን ደግሞ የውጪ ግብ ጠባቂዎችን ከሚጠቀሙ ክለቦች ተርታ ተቀላቅለዋል። ላለፉት ሁለት የውድድር አመታት በደደቢት የምናውቀው አማራህ ክሌመንት ደግሞ የቢጫ ለባሾቹ ምርጫ ሆኗል። በሁለተኛው ዙር አቋሙ ከቡድኑ ጋር በሚመሳሰል መልኩ የወረደው ጋናዊው ግብ ጠባቂ ደደቢት በመጀመሪያው ዙር ላሳየው ብቃት ትልቅ ሚና በመወጣት በሶከር ኢትዮጵያ የታህሳስ ወር ምርጥ ቡድን ውስጥ መካተት ችሎ ነበር።
ግብ ጠባቂው የክለቡ አራተኛ ፈራሚ ሲሆን የኋላ መስመራቸውን በማጠናከር ላይ ትኩረት ያደረጉት ወልዋሎዎች ከዚህ በፊት የተከላካይ መስመር ተጨዋቾቹን ዳንኤል አድሀኖም ፣ ብርሀኑ ቦጋለ እና ቢንያም ሲራጅን እንዳስፈረሙ ይታወሳል።