የፕሪምየር ሊጉ ቻምፒዮን ጅማ አባ ጅፋር በርካታ ተጫዋቾችን ለቆ አዳዲስ ተጫዋቾችንም ከማምጣት ተቆጥቦ መቆየቱ አግራሞት ሲፈጥር ቆይቷል። ዘግይቶ ወደ ዝውውር ገበያው የገባው ጅማ ሁለት ተጫዋቾችን አስፈርሟል።
ከ8 ዓመታት በኋላ ከቡና ጋር የተለያየው መስዑድ መሐመድ ወደ ጅማ ማምራቱ እርግጥ ሆኗል። የአማካይ ስፍራ ተጫዋቹ መስዑድ በ1990ዎቹ መጨረሻ ወደ ኤሌክትሪክ ዋናው ቡድን አድጎ በ2002 ወደ ቡና አምርቷል። ከቡና ጋር የሊጉን ዋንጫ ያነሳው መስዑድ በ2007 የዳዊት እስጢፋኖስን መልቀቅ ተከትሎ ቡድኑን በአምበልነት ሲመራ ቆይቶ ዘንድሮ ውሉን በመጨረስ ከክለቡ ጋር ተለያይቷል። በጅማም የአንድ ዓመት ኮንትራት መፈረሙ ታውቋል።
ኤርሚያስ ኃይሉ ሁለተኛው የጅማ አባ ጅፋር ፈራሚ ነው። በ2006 ከኒያላ ወደ ዳሽን ቢራ በመዛወር ክለቡ እስከፈረሰበት ጊዜ ድረስ ሲቆይ ፋሲል ከተማ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ካደገ በኋላም ያለፉትን ሁለት የውድድር ዓመታት ቆይታ ማድረግ ችሏል። የመስመር አጥቂው በጅማ የሁለት ዓመት ኮንትራት ፈርሟል።
ጅማ ከሁለቱ ፊርማ በተጨማሪ በቀጣይ ቀናት አዳዲስ ተጫዋቾችን ዝውውር እንደሚያጠናቅቅ ሲገለፅ የኤልያስ አታሮ፣ ንጋቱ ገብረስላሴ፣ ዳንኤል አጄይ እና ይሁን እንደሻውን ውል ማራዘሙ ተነግሯል።