ከተገኔ ነጋሽ ጋር የተለያየው አዳማ ከተማ የአሰልጣኝ ቡድኑን በአዲስ በማዋቀር ሲሳይ አብርሀምን ዋና አሰልጣኝ፣ ዳዊት ታደሰን ረዳት አሰልጣኝ አድርጎ ቀጥሯል።
በ2007 ወደ ፕሪምየር ሊግ ከተመለሰ በኋላ በተከታታይ ለሦስት የውድድር ዘመናት 3ኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው አዳማ ዘንድሮ ወደ አምስተኛ ወርዶ ማጠናቀቁን ተከትሎ ከዋና አሰልጣኙ ጋር መለያየቱ የሚታወስ ሲሆን ከፍተኛ ግምት አግኝተው የነበሩት አሰልጣኝ ሲሳይ አብርምን መሾሙ ተረጋግጧል።
የቀድሞው የሼር ኢትዮጵያ እና የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን (ረዳት) አሰልጣኝ የተጠናቀቀውን ዓመት አክሱም ከተማን በመያዝ ቢጀምሩም ብዙም ሳይቆዩ ተለያይተው ያለፉትን ወራት ያለ ክለብ ተቀምጠው በመጨረሻም የአዳማ ከተማ አሰልጣኝ ሆነዋል።
በተገኔ ስር ምትክል አሰልጣኝ የነበሩት አስቻለው ኃይለሚካኤል ምትክ የሲሳይ አብርሀም ረዳት በመሆን ለመስራት የተሾመው አሰልጣኝ ዳዊት ታደሰ ነው። ወጣቱ አሰልጣኝ ከአዳማ 20 ዓመት በታች ቡድን ወደ ገላን ከተማ በማምራት ክለቡን ወደ ከፍተኛ ሊግ እንዲያልፍ ከመርዳቱ በተጨማሪ በወጣቶች ላይ የተመሰረተ ቡድን በመገንባት በአንደኛ ሊጉ የብዙዎችን ቀልብ ስቧል። አሰልጣኙ አዳማ እየተካሄደ ከሚገኘው የማጠቃለያ ውድድር ፍፃሜ በኋላ ወደ ክለቡ እንደሚቀላቀሉ ይጠበቃል።
ከክለቡ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው ሁሉም የቅጥር ውል ለአንድ ዓመት የሚቆይ ሲሆን ከነገ ጀምሮ ወደ ዝውውር እንቅስቃሴ እንደሚገቡም ተገልጿል።