ከጅማ አባ ጅፋር ጋር እንደሚቀጥል ሲጠበቅ የነበረው ታታሪው አማካይ ሳይጠበቅ ለወልዋሎ ፈርሟል።
ባሳለፍነው የውድድር አመት ሙሉ ወጥ የሆነ ብቃት በማሳየት ጅማ አባ ጅፋርን ለድል ካበቁ ተጨዋቾች መካከል አንዱ የሆነው ይሁን እንዳሻው ቀጣይ ማረፊያው ሳይታወቅ ቆይቶ ነበር። ይሁን እንጂ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ለይ ከምዕራቡ ክለብ ጋር እንደሚቀጥል ተነግሮ የነበረ ቢሆንም በቅርቡ የጋብቻ ስነስርዐቱን የፈፀመው ተጨዋቹ የአሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም ዘጠነኛ ፈራሚ በመሆን ወልዋሎ ዓ.ዩን ተቀላቅሏል።
ከጅማ አባ ጅፋር ጋር የሊጉን ዋንጫ ከማንሳቱ አስቀድሞ በመተሀራ ስኳር እና ድሬዳዋ ከተማ ተጫውቶ ያለፈው ይሁን ከዚህ ቀደም በአሰልጣኝ ዮሀንስ ሳህሌ ዘመን ለዋልያዎቹ የመጠራትን ዕድልም አግኝቷል። ትናንት ይፋ በሆነው የአሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ የመጀመሪያ የተጨዋቾች ዝርዝር ውስጥ አለመካተቱ ግርምትን የፈጠረው አማካዩ በአባጅፋር ከአሚኑ ነስሩ ጋር የፈጠረው የመሀል ሜዳ ጥምረት በሊጉ ካሉ አማካዮች መሀል ጎልቶ እንዲወጣ ያስቻለው ነበር።
የዝውውር መስኮቱ ከተከፈተ በኋላ አጣማሪው አሚኑን ጨምሮ በርካታ የቡድን አጋሮቹ ከጅማ መልቀቃቸው እሱንም ተመሳሳይ መንገድ እንዲከተል ሊያደርገው ይችላል ተብሎ ሲጠበቅ ከጅማ ጋር ከሚቀጥሉ ተጨዋቾች ጋር ስሙ መካተቱ ለሻምፒዮኖቹ እረፍትን የሰጠ ነበር። ሆኖም ተጨዋቹ ወደ ቢጫ ለባሾቹ ቤት በድንገት ማምራቱ ዕውን ሆኗል። በጉዳዩ ዙሪያ ሀሳቡን ለሶከር ኢትዮጵያ የሰጠው ይሁን ” በጅማ ለመቆየት ተስማምቼ የነበረ ቢሆንም በመጨረሻ ላይ ያደረግነው ድርድር ባለመሳካቱ ወደ ወልዋሎ ላመራ ችያለው” ብሏል።