በዝውውር መስኮቱ ዝምታን መርጠው ከነበሩ ክለቦች መካከል አንዱ የሆነው አዳማ ከተማ ሱራፌል ዳንኤልን አስፈርሟል።
ሲሳይ አብርሀምን ወደ አሰልጣኝነቱ ያመጣው አዳማ ከተማ እንደተጠበቀው ሁሉ ወደ ዝውውር ገበያው ወጥቷል። በወጣት ተጨዋቾች የተገነባውን ቡድኑ ራሱን ለማጠናከር በማሰብ የድሬዳዋ ከተማው ሱራፌል ዳንኤልን በእጁ አስገብቷል። ከቡድኑ ወሳኝ ተጫዋቾች አንዱ የነበረው የመስመር አማካዩ ሱራፌል ዳኛቸውን የለቀቀው አዳማ የቦታው አማራጮቹን ይበልጥ ለማስፋት በማሰብ ይመስላል ዝውውሩን የፈፀመው።
በዝውውሩ ወደ ትውልድ ከተማው እና በተስፋ ቡድን ወደተጫወተበት ክለብ የተመለሰው ሱራፌል ድሬዳዋ ከተማ ወደ ፕሪምየር ሊጉ እንዲያድግ ትልቅ አስተዋፅኦ ካበረከቱ ተጨዋቾች መካከል የሚነሳ ሲሆን በተለይም በ2009 የውድድር አመት በምስራቁ ክለብ በተደጋጋሚ የመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ የሚገባ ተጨዋች ነበር። ባጠናቀቅነው የውድድር አመትም መጠነኛ መቀዛቀዝ ቢታይበትም በሁሉተኛው ዙር የሊጉ ጨዋታዎች ድሬዳዋ በሊጉ እንዲቆይ የራሱን ሚና ተወጥቷል። ቀጣዮቹን ሁለት የውድድር አመታት በአዳማ ከተማ እንደሚቆይ የሚጠበቀው ሱራፌል በአዳማ የመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ ለመካተት ከነ በረከት ደስታ፣ ቡልቻ ሹራ እና ጫላ ተሺታ ጋር ብርቱ ፉክክር እንደሚያደርግ ይጠበቃል።