ወጣቱ የአዳማ ከተማ አማካይ ከነዓን ማርክነህ በቅርቡ ለሙከራ ወደ ሰርቢያ እንደሚያመራ ገልጿል።
በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ ከቅርብ ዓመታት ውስጥ ብቅ ካሉ ባለ ተሰጥኦ ተጫዋቾች መካከል አንዱ የሆነው ከነዓን ማርክነህ ከአዳማ ተስፋ ቡድን ለቆ በአአ ዩኒቨርሲቲ እና አዲስ አበባ ከተማ ከተጫወተ በኋላ አዳማ ከተማን በተጠናቀቀው የውድድር አመት ተቀላቅሎ የተዋጣለት እንቅስቃሴ ከማድረጉ ባሻገር ከአማካይ ስፍራ እየተነሳ 8 ጎሎችን ማስቆጠር ችሏል።
በሴካፋ ወድድር ላይ የመጀመርያ ተሰላፊ የነበረ ሲሆን በአሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ ብሔራዊ ቡድንም ጥሪ ቀርቦለታል። ተጨዋቹ በቅርቡ ለሙከራ ወደ ሰርቢያ እንደሚያመራ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልጿል።
” ዕድሉን ያገኘልኝ ከውጪ ኤጀንቶች ጋር ግንኙነት ያለው ቢንያም የሚባል ሰው ነው። አሁን ጉዳዩ በሂደት ላይ ነው። ከፌዴሬሽን የሚላክ ወረቀት አለ። እሱ ነበር የሚቀረው ዛሬ እንደሚላክ እጠብቃለው። ወረቀቱ ከደረሳቸው በኋላ ወደ ስፍራው እንዳመራ የሚልኩልኝን የግብዣ ወረቀት እጠብቃለው ማለት ነው። እዛው ሰርቢያ ውስጥ የሬድ ስታር ቤልግሬድ እህት ኩባንያ አለ። ሙከራውን የማደረገው እዛ ነው። ከተሳካ ወደ ፈለኩበት ክለብ የምፈርም ይሆናል።” ብሏል።