የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ 27ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በዛሬው እለት ተከናውነው ጅማ አባ ቡና እና ሀላባ ወሳኝ ድል በማስመዝገብ በእኩል ነጥብ ወደ መሪነት ከፍ ሲሉ ደቡብ ፖሊስ ነጥብ በመጣል መሪነቱን አስረክቧል።
በቴዎድሮስ ታደሰ እና አምሀ ተስፋዬ
ጅማ አባቡና ብዙዓየሁ እንደሻሁ ሐት-ትሪክ በሰራበት ጨዋታ ዲላ ከተማን 4-1 በማሸነፍ የምድቡ መሪነትን ከደቡብ ፖሊስ መረከብ ችሏል፡፡ የመጀመሪያውን አጋማሽ በፈጣን የማጥቃት እቅስቃሴ የጀመሩት ባለሜዳዎቹ በዳዊት ተፈራ የመጀመሪያዎቹ 5 ደቂቃዎች ላይ ከርቀት በሞከራቸው አስደንጋጭ ሙከራዎች መነሳሳትን ሲፈጥሩ ዲላዎች በአንፃሩ ወደኋላ እንዲያፈገፍጉ አስገድዷቸዋል። በ6ኛው ደቂቃ ጀሚል ያዕቆብ ተከላካዮችን በማለፍ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ የዲላ የተከላካዮች መዘናጋትን በመጠቀም ብዙዓየሁ አባቡናን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል። በ12ኛው ደቂቃ ኪዳኔ አሰፋ ከሳጥን ውጭ አክርሮ የመታው የዲላን ተከላካዮች ጨርፍ የግቡን አግዳሚ በመለተም ሲወጣ በ24ኛው ደቂቃ ብዙዓየሁ እንደሻው የዲላ ከተማ ግብ ክልል ውስጥ ተጎትቶ በመውደቁ የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት ራሱ አስቆጥሮ የአባቡናን መሪነት ወደ 2-0 ከፍ ማድረግ ችሏል።
ከግቧ መቆጠር በኃላም የአባቡና ጫና ሲቀጥል ዲላዎች መረጋጋት ሲሳናቸው እንዲሁም ተደጋጋሚ ስህተቶችን ሲሰሩ ተስተውለዋል። በመጀመሪያው አጋማሽም ይህ ነው የሚባል እቅስቃሴም ሆነ የጎል ሙከራ ማድረግ ሳይችሉ ቀርተዋል። የመጀመሪያው አጋማሽ ከመጠናቀቁ በፊት ብዙዓየሁ በ44ኛው ደቂቃ ከሳጥኙ የቀኝ ጠርዝ መሬት ለመሬት አክርሮ በመምታት የባለሜዳዎቹን መሪነት ወደ 3 ከፍ ሲያደርግ ገና እረፍት ሳይወጡም ሐት-ትሪኩን ማጠናቀቅ ችሏል።
ከእረፍት መልስ ከመጀመሪያው አጋማሽ በተቃራኒው ዲላዎች አጥቅተው ለመጫወት የቻሉ ሲሆን በጨዋታ አቀራረባቸውም ሆነ በእንቅስቃሴ ረገድ ከአባ ቡና ተሽለው ቀርበዋል። በ50ኛው ደቂቃ ከግራ መስመር የተሻገረውን ኳስ መና በቀለ በግንባሩ በመግጨት የጎል ልዩነቱን በማጥበብ አባቡናን ጫና ውስጥ መክተት ችሏል። በ69ኛው ደቂቃ ላይ በመልሶ ማጥቃት የሻገረውን ኳስ የዲላው ግብ ጠባቂ ፍቃዱ ዘውዴ ከሳጥን ውጭ ኳስ በእጅ በመንካቱ በቀጥታ በቀይ ካርድ ከሜዳ ከወጣ በኃላ የዲላዎችን ተስፋ ያዘቀዘ አጋጣሚ ነበር። በእለቱ ጥሩ ሲቀሳቀስ የነበረው የአባቡናው ተመስገን ደረሰ በ80ኛው ደቂቃ ከግብ ጠባቂው ጋር ፊት ለፊት ተገናኝቶ ያመከነው እንዲሁም ብዙዓየሁ በግንባሩ ሞክሮ በዲላ ተከላዮች ርብርብ የወጣው ተጠቃሽ አጋጣሚዎች ነበሩ። በስተመጨረሻም በጭማሪ ደቂቃ ላይ ተመስገን ደረሰ ከግራ የሳጥኑ ጠርዝ ግሩም ግብ አስቆጥሮ ጨዋታው በአባቡና 4-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ረፋድ 04:00 ላይ የተደረገው የሀላባ እና ሻሸመኔ ከተማ ጨዋታ በባለሜዳዎቹ አሸናፊነት ተገባዷል። እንደ ወሳኝነቱ በበርካታ ደጋፊዎች ታጅቦ የተጀመረው ጨዋታ ሳቢና የአካል ንኪኪ የበዛበት ነበር። ቁመተ መለሎውን አጥቂ ስንታየሁ መንግስቱን በቅጣት ምክንያት ያጣው ሀላባ ተመስገን ይልማን ተክቶ በቦታው የገባ ሲሆን በ5ኛው ደቂቃ በአዩብ በቀታ የግንባር ሙከራ የተጀመረው የሀላባ ከነማ የማጥቃት እንቅስቃሴ በበርካታ ሙከራዎች የታጀበ ነበር። በ5ኛው እና በ13ኛው ደቂቃ አቦነህ ገነቱ ያደረጋቸው ሙከራዎች በሀላባ በኩል የሚጠቀሱ ሙከራዎች ሲሆኑ የተመስገን ይልማ የ25ኛ ደቂቃ ከቀኝ መስመር በኩል ከስንታየሁ አሸብር የተላከለትን ኳስ ወደግብነት ቀይሮ ሀላባን መሪ ማድረግ ችሏል። ከዚህች ግብ መቆጠር በኋላ የአቻነት ግብ ፍለጋ ጥሩ የተንቀሳቀሱት ሻሸመኔዎች ኃይል ላይ ያመዘነ ጨዋታ መከተልን የመረጡ ሲሆን በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ የሀላባው አጥቂ መሀመድ ናስር ላይ በተሰራውን ጥፋት ዳኛው በዝምታ አልፈዋል በሚል በጨዋታው መሀል 65ኛ ደቂቃ ላይ ሀላባዎች ክስ አስይዘው ጨዋታው ቀጥሏል። በ85ኛው ደቂቃ የቀድሞው የወልቂጤ ከተማ ተጫዋች መሀመድ ናስር ለቡድኑ ሁለተኛውን ግብ በማስቆጠር ጨዋታው 2-0 እንዲጠናቀቅ ሆኗል።
ወደ ነጌሌ ያመራው ደቡብ ፖሊስ 1-1 አቻ ተለያይቶ ከመሪነት ወደ 3ኛ ደረጃ ወርዷል። ደቡብ ፖሊስ በኬንያዊው አንጋፋ ኤሪክ ሙራንዳ ጎል ለረጅም ደቂቃዎች ቢመራም ነጌሌዎች በመጨረሻ ደቂቃ ባስቆጠሩት ጎል አቻ ተለያይተዋል።
በሌሎች ጨዋታዎች ስልጤ ወራቤ መቂ ከተማን 3-0 ሲያሸንፍ ካፋ ቡና ሀምበሪቾን 1-0 ረቷል። ወደ ወልቂጤ ያመራው ቤንች ማጂ ቡና ደግሞ 2-0 አሸንፎ ተመልሷል። ናሽናል ሴሜንት ከቡታጅራ ከተማ እንዲሁም ድሬዳዋ ፖሊስ ከሀዲያ ሆሳዕና በምስራቁ የሀገሪቱ ክፍል ባለው አለመረጋጋት ምክንያት ያልተካሄዱ ጨዋታዎች ናቸው።
የደረጃ ሰንጠረዥ