የኢትዮጵያ ከ17 አመት በታች ብሔራዊ ቡድን ወደ በ2019 የታዳጊዎች አፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ለመሳተፍ ወደ ዳሬሰላም ያቀናው ቡድኑ ከመጀመሪያው ጨዋታ በፊት ልምምዱን ሰርቷል።
በተመስገን ዳና የሚመራው ቡድኑ ከሀምሌ መጨረሻ አንስቶ በሀዋሳ ሲሰናዳ የቆየ ሲሆን ማክሰኞ ረፋድ ወደ ምስራቅ አፍሪካዊቷ ሀገር ተጉዟል፡፡ ቀይ ቀበሮዎቹ የመጀመሪያ የመድረኩን ጨዋታቸውንም ከኡጋንዳ አቻቸው ጋር የፊታችን እሁድ በቻማዚ ስታድየም ያደርጋሉ። አሰልጣኝ ተመስገን ዳና ለሶከር ኢትዮጵያ እንደገለፁትም ቡድኑ የመጀመሪያ ልምምዱን ዛሬ በጄ ኤም ፓርክ አድርጓል።
ታዳጊ ቡድኑ 10 ሀገራት ተሳታፊ በሚሆኑበት ውድድር ላይ ለመካፈል በማጣሪያው ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቅ የሚጠበቅበት ሲሆን ይህንን የሚያሳካ ከሆነ በ2019 የአፍሪካ ከ17 አመት በታች ውድድር ላይ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ይሳተፋል።
የአፍሪካው ውድድር አስተናጋጅ በሆነችው ታንዛንያ አስተናጋጅነት በሁለት ምድብ ተከፍሎ የሚከናወነው የዚህ ውድድር ምድብ ድልድል ይህን ይመስላል፡-
ምድብ ሀ፡ ታንዛንያ፣ ሩዋንዳ፣ ቡሩንዲ፣ ሶማሊያ እና ሱዳን
ምድብ ለ፡ ዩጋንዳ፣ ኬንያ፣ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ሱዳን እና ጅቡቲ
8 ሀገራት በሚሳተፉበት የ2019 የአፍሪካ ከ17 ዓመት በታች ዋንጫ ላይ ሴካፋን ጨምሮ ከ7 የክፍለ አህጉር ውድድሮች ቻምፒዮን የሚሆኑ ቡድኖች ሲሸጋገሩ በአፍሪካ ዋንጫው ግማሽ ፍፃሜውን የሚቀላቀሉ ብሔራዊ ቡድኖችም በፔሩ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የዓለም ዋንጫ የሚያልፉ ይሆናል።
የኢትዮጵያ ጨዋታዎች
እሁድ ነሃሴ 6
ዩጋንዳ ከ ኢትዮጵያ (ቻማዚ)
ማክሰኞ ነሃሴ 8
ጅቡቲ ከ ኢትዮጵያ (ቻማዚ)
እሁድ ነሃሴ 13
ኢትዮጵያ ከ ደቡብ ሱዳን (ቻማዚ)
ረቡዕ ነሃሴ 16
ኢትዮጵያ ከ ኬንያ (ቻማዚ)