በካሜሩን አስተናጋጅነት ጁን 2019 ላይ ለሚከናወነው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ላይ ተሳታፊ የሆነው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከሴራሊዮኑ ጨዋታ በፊት የመጀመሪያ ልምምዱን ዛሬ በሀዋሳ ሰርቷል፡፡
በአሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ መሪነት በጳጉሜ ወር ከሴራሊዮን ጋር ሁለተኛ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ ያለበት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የመጀመሪያ ልምምዱን በሀዋሳ አለም አቀፍ ስታዲየም ከቀኑ 11 ሰአት ላይ ሰርቷል፡፡ ከጋና፣ ሴራሊዮን እና ኬኒያ ጋር የተደለደለው ብሔራዊ ቡድኑ ዛሬ ቀትር ላይ ሀዋሳ የገባ ሲሆን ማረፊያቸውን በሀዋሳ ሴንትራል ሆቴል ያደርጋሉ ቢባልም ምቹ የጂም እና የመዋኛ እንዲሁም ሌሎ አገልግሎቶች ከመፈለግ አንፃር በሀዋሳ ሮሪ ሆቴል እንዲቆዩ ሆኗል።
ብሔራዊ ቡድኑ አስቀድሞ ትላንት ረቡዕ ልምምዱን ይጀምራል ተብሎ የነበረ ቢሆንም ሁሉም ተጫዋቾች የጤና ምርመራ የሚደረግላቸው በመሆኑ ዘግይተው ልምምድ ጀምረዋል። ጥሪ ከተደረገላቸው 34 ተጫዋቾች መካከል 27ቱ በመጀመሪያው ቀን ሊገኙ ችለዋል። ከሀገር ውጪ የሚጫወቱት ኡመድ ዑኩሪ፣ ሽመልስ በቀለ፣ ቢኒያም በላይ እና ጋቶች ፓኖም በፊፋ ህግ መሰረት ከነሀሴ 25 በኃላ ቡድኑን እንደሚቀላቀሉ ይጠበቃል። ከሀገር ውስጥ ደግሞ ግብ ጠባቂው ሳምሶን አሰፋ ነገ ልምምድ የሚጀምር ሲሆን ጌታነህ ከበደ በጀርመን የኢትዮጵያውያን ፌስቲቫል ላይ እየተካፈለ በመሆኑ እንዲሁም ነገ ወደ ሰርቢያ ለሙከራ የሚያቀናው ከነዓን ማርክነህ ሌሎች ያልተገኙ ተጨዋቾች ናቸው።
ዛሬ 11:00 ላይ በሀዋሳ ዓለም አቀፍ ስታድየም ለአንድ ሰዓት የቆየ የሜዳ ላይ ተግባሮችን የሰሩ ሲሆን በልምምዱ ወቅት አጥቂዎቹ አቡበከር ነስሩ እና አማኑኤል ገብረሚካኤል በመጠነኛ ጉዳት ምክንያት አራፊ ሆነዋል።
ብሔራዊ ቡድኑ ከነገ ጀምሮ በቀን ሁለት ጊዜ ጠዋት ከ12 ሰዐት ጀምሮ በሀዋሳ ሰው ሰራሽ ስታድየም እንዲሁም ከሰአት ከ10 ሰዐት ጀምሮ ደግሞ በአለም አቀፉ ስታድየም ልምምዱን እንደሚቀጥል ሲጠበቅ ከቀጣዩ ሳምንት ጀምሮ ግን በጂምናዝየም እና በክፍል ውስጥ የስነ-ልቡና እና ታክቲካል ስልጠናን እንደሚሰጥ ተነግሯል።
ስታድየሙ በስሎቫኪያው ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ተቋም አማካኝነት የስክሪን እና የካሜራ ገጠማ እየተከናወነለት ሲሆን ጳጉሜ 4 ላይ ኢትዮጵያ ከሴራሊዮን በሚያደርጉት ጨዋታ ላይ አገልግሎት መስጠት ይጀምራል ተብሏል።