‹‹ ጣልያናዊ ነኝ ›› መልካሙ መለስ ታውፈር


ትውልደ ኢትዮጵያዊው ባለ አስደናቂ ክህሎት ታዳጊ በጣልያን ሴሪ አ ለኢንተር ሚላን ተሰልፎ ሲጫወት ልንመለከተው ተቃርበናል፡፡ የከተማዋ እና የክለቡ ጋዜጦችም መልካሙ የኢንተርን ስብስብ ሰብሮ የመግባት አቅም እንዳለው መሞገት ጀምረዋል፡፡ ገና የ16 አመት ታዳጊ መሆኑን ስንረዳ ከወዲሁ በብዙዎች ልብ ውስጥ መግባቱ አስገራሚ ነው፡፡

የኢንተር ሚላን ከ17 አመት በታች ቡድን አምበል የሆነው መልካሙ አሁን ጣልያናውያን ተስፋ የጣሉበት የቀጣዩ ዘመን ድንቅ አማካይ ነው፡፡ ፌብሩዋሪ 8 ቀን 1998 በጎንደር የተወለደው መልካሙ ኢትዮጵያዊነቱን ባይሸሽግም ይበልጥ ጣልያናዊነት ይሰማዋል፡፡ ‹‹ የተወለድኩት ጎንደር ነው … ነገር ግን እኔ ጣልያናዊ ነኝ ፣ ያደግኩት እዚሁ ነው፡፡ በማደጎ ወደ እዚህ ሃገር ስመጣ የ3 አመት ጨቅላ ነበርኩ፡፡ ›› ሲል በልጅነቱ ከለቀቃትና ምንም ትውስታ ከሌለው የትውልድ ሃገሩ ይልቅ ጣልያንን እንደሚያስቀድም ይናገራል፡፡

‹‹ በምኖርበት ፓላዞሎ መንደር እግርኳስን መጫወት ስጀምር ገና የ6 ወይም የ7 አመት ልጅ ብሆን ነው፡፡ ወላጆቼ ለእግርኳስ እምብዛም ፍቅር የሌላቸው በመሆኑ ፕሮፌሽናል እግርኳስ ተጫዋች የሆናል ብለው አላሰቡም ነበር፡፡ እኔም እግርኳስን እጫወት የነበረው ለደስታ ነበር፡፡ በፓላዞሎ የህፃናት ክለብ ከታቀፍኩ በኋላ ግን እግርኳስን የምር ያዝኩት፡፡ ትንሽ ቆይቶም ከአሰልጣኝ ቲሮኒ ጋር ተገናኘሁ፡፡ እሳቸው ወደ ኢንተር ላደረግኩት ጉዞ ትልቁን ሚና ተጫውተዋል፡፡ ››

ከ3 አመታት በኋላ መልካሙ ኔራዙሪዎቹን ተቀላቀለ፡፡ የ ‹‹ ክላስ ኦፍ 98 ›› አባላት መሪም ሆነ፡፡ ነገር ግን በልጅነቱ ከቤተሰቡ መራቅ ለመልካሙ አስቸጋሪ ነበር፡፡ ‹‹ ቤተሰቦቼ ለብሬሽያ እንድፈርም ፈልገው ነበር፡፡ ሌሎች ክለቦችም ፈልገውኝ ነበር፡፡ ነገር ግን ትክክለኛ ማረጋገጫ ወዳገኘሁበት ኢንተር ሚላን አመራሁ፡፡ ክለቡ ቤተሰቦቼን ቶሎ ቶሎ እንድጠይቅ ትራንስፖርት ቢያመቻችልኝም የቤተሰብ ናፍቆት አስቸግሮኝ ነበር፡፡ ››

መልካሙ በቅርብ ጊዜያት በማርዮ ባሎቴሊ ፊት አውራሪነት የተጀመረው የጥቁር ጣልያናውያን ተጫዋቾች አብዮት አካል ነው፡፡ እንደውም ማርዮ እና መልካሙ የሚመሳሰሉበት ታሪክ አላቸው፡፡ ሁለቱም እግርኳስን የጀመሩት ከኢንተር ሚላን አካዳሚ ተነስተው ነው ፣ ሁለቱም በማደጎ መልክ ከአፍሪካ ወደ ደቡብ አውሮፓዊቷ ሃገር ያመሩት ገና በልጅነታቸው ነው፡፡ ነገር ግን መልካሙ እንደ ማርዮ ፈተናን አልቀመሰም፡፡

‹‹ ባሎቴሊ ላይ የነበረው ዘረኝነት ትንኮሳ እስካሁን አላጋጠመኝም፡፡ ወደ ሜዳ ስገባ ሙሉ ትኩረቴ እግርኳስ ላይ ነው ፤ ተመልካቹ ስለሚጮኸው ነገር መስማትም አልፈልግም፡፡ ›› ሲል ለጥቁር እግርኳስ ተጫዋቾች አስቸጋሪ በሆነው ጣልያን ይህ ስሜት እንደማይሰማው ይገልጻል፡፡

የአእምሮ ጥንካሬን እና የቴክኒክ ተሰጥኦን የታደለው መልካሙ ኢንተር ሚላንን በአምበልነት መርቶ የጣልያን ከ17 ዓመት በታች ሊግ ዋንጫን ሁለት ጊዜ አሸንፏል፡፡ የጣልያን ብሄራዊ ታዳጊ ቡድንንም በአምበልነት መርቷል፡፡ በጣልያን ታላቅ ክብር ያለው 10 ቁጥር ማልያን የሚለብሰው ታዳጊ ስብእናው እና አጨዋወቱ እንደ ባርሴሎናው ኮከብ አንድሬስ ኢንየስታ እንዲሆንም ይጥራል፡፡

‹‹ የኳሱ እንቅስቃሴ በእኔ ዙርያ እንዲሆን እፈልጋለሁ፡፡ ቶሎ ቶሎ ኳሶችን ማግኘትና ቀዳዳ ለመፍጠር መጣር ያስደስተኛል፡፡ አንድሬስ ኢንየስታ ሮል ሞዴሌ ነው፡፡ የእሱን እንቅስቃሴዎች ለመኮረጅ ሁልጊዜም እጥራለሁ ››

ያጋሩ