በታላቁ የባርሴሎና የወጣቶች ማሰልጠኛ ማዕከል ላማሲያ ውስጥ የሚገኙ ሁለት ትውልደ ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾች በክለቡ የወጣት ቡድን ውስጥ እየተጫወቱ ይገኛሉ።
ባርሴሎና ከ17 ዓመት በታች ቡድን (Cadete A) ውስጥ ሁለት ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾች በስብስቡ ተካተው የ2017/18 ውድድር ዘመንን አጠናቀዋል። አስቻለው ሳንማርቲ የተከላካይ መስመር ተጫዋች ሲሆን ከዚህ ቀደም በድረገፃችን ላይ ያስተዋወቅናችሁ አጥቂው አንዋር ሜዴይሮ ሌላው የዚህ ቡድን አባል ነው። ሁለቱ ተጫዋቾች በጳጉሜ ወር በሚጀመረው አዲሱ የ19 ዓመት በታች ውድድር ላይ የሚካፈለውን የባርሴሎና ቡድን (ጁቬኔይል ቢ) እንደሚቀላቀሉ ይጠበቃል።
አስቻለው ሳን ማርቲ አጉዊላር ፌብሩዋሪ 1 ቀን 2002 ኢትዮጵያ ውስጥ የተወለደና በስፔናዊያን ቤተሰቦች በማደጎ የተወሰደ ታዳጊ ነው። በካታላን ግዛት የሚገኘውና በርካታ ታዳጊዎችን ለባርሴሎና እና ኤስፓኞል የሚመግበው ኮርኔሊያ የህፃናት ቡድን ውስጥ ታቅፎ መጫወት ከጀመረ በኋላ ከፍተኛ እድገትን ማሳየት ችሏል። በ2014 በብራዚል ሳኦ ፓውሎ በተደረገ ዓለምአቀፍ የታዳጊዎች ውድድር ላይም ኮርኔሊያ ተስፋ ያለው እንቅስቃሴ ሲያደርግ ደምቀው ከታዩ ተጫዋቾች መካከል አንዱ መሆን ችሏል።
የ16 ዓመቱ የመሐል ተከላካይ ስፍራ ተጫዋች አስቻለው ከኮርኔሊያ ቆይታው በኋላ በ2015 ወደ ባርሴሎናው ዝነኛ የወጣቶች ማሰልጠኛ ማዕከል ላማሲያ አመራ። በተለያዩ የእድሜ እርከኖች ከ300 በላይ ተጫዋቾችን ያቀፈው ላማሲያ ውስጥ በየዓመቱ እድገት በማሳየት በ3 ዓመት ውስጥ ሶስት የእድሜ እርከኖችን ተሻግሮ የተጠናቀቀውን ውድድር ዓመት በካዴት ኤ (ከ17 ዓመት በታች ቡድን) ውስጥ ማሳለፍ ችሏል። የአስቻለውን እድገት የተመለከትን እንደሆነ በቀጣይ የውድድር ዘመን በ19 ዓመት በታች ቡድኑ ውስጥ ልንመለከተው እንችላለን።
ሌላው በባርሴሎና ታዳጊ ቡድን ውስጥ የሚገኘውና በአንድ ወቀት የስፔን መገናኛ ብዙሀን ትኩረት ስቦ የነበረው አንዋር ሜዴይሮ ሮድሪጌዝ ከአስቻለው ጋር በአንድ ቡድን ታቅፎ የውድድር ዘመኑን ያሳለፈ ተጫዋች ነው። በ2015 ከሴልታ ቪጎ አወዛጋቢ በሆነ ዝውውር ወደ ባርሴሎና ያመራው አንዋር የተወለደው ማርች 3 ቀን 2002 አዲስ አበባ ነው። በጋላሲያን ግዛት የሚኖሩ ስፔናዊያን በማደጎነት ከወሰዱት በኋላ በሴልታ ቪጎ አካዳሚ መነጋገርያ የሆነ ብቃት ማሳየት የቻለ ሲሆን እንደ አስቻለው ሁሉ ባርሴሎናን ከተቀላቀለ በኋላ ባሉት ጊዜያት በየዓመቱ የእድሜ እርከን እድገት ማሳየት ችሏል።
በተለያዩ የአጥቂ አማራጮች መሠለፍ የሚችለው የ16 ዓመቱ አንዋር በአዲሱ የውድድር ዘመን የባርሴሎና ከ19 ዓመት በታች ቡድንን እንደሚቀላቀልም ይጠበቃል።
(ከዚህ ቀደም በሶከር ኢትዮጵያ ስለ አንዋር ያዘጋጀነውን ጽሁፍ ማያያዣውን በመጫን ያገኛሉ | LINK )
ቲዮ ሱራፌል ቤርናርዶ ጋሌጎ በሚል ሙሉ ስም የሚጠራው ሱራፌል ሌላው በባርሴሎና ወጣት ማዕከል የነበረ ትውልደ ኢትዮጵያዊ ነው። ኖቬምበር 14 ቀን 2003 የተወለደው ሱራፌል የተከላካይ ስፍራ ተጫዋች ሲሆን ማርቲኔንክ እና ዳም በተሰኙ የታዳጊ ቡድኖች አሳልፎ እንደ ሁለቱ ተጫዋቾች ሁሉ በ2015 ባርሴሎናን ተቀላቅሏል። የ15 ዓመቱ ሱራፌል በ2016/17 የውድድር ዓመት በብዙዎች አድናቆት የተቸረው ከ15 ዓመት በታች ስብስብ (የወደፊቱ ታላቅ ተጫዋች እንደሚሆን የተተነበየለት ዣቪ ሲመንስ የሚገኝበት) ውስጥ አባል የነበረ ሲሆን ባለፈው ክረምት ክለቡን ለቋል። (ምስል ከታች)