ወደ አንደኛ ሊግ ለማደግ ከነሀሴ 6 እስከ 21 ድረስ በሀዋሳ ከተማ የሚደረገው የክልል ክለቦች ሻምፒዮና ዛሬ ተጀምሯል፡፡
በስምንት ምድቦች ተከፍሎ የሚደረገው የኢትዮጵያ ክልል ክለቦች ሻምፒዮና ለቀጣዮቹ 15 ቀናት በ31 ቡድኖች መካከል የሚከናወን ሲሆን ዛሬ ሁለት የመክፈቻ ጨዋታዎች ተከናውነው የፋሲል እና ወልዋሎ ቢ ቡድኖች ድል አስመዝግበዋል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ እንዲሁም አቶ ገልገሎ ገዛኸኝ የደቡብ ክልል ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ም/ኃላፊ፣ ኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው እና የፌዴሬሽኑ ጊዜያዊ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሰለሞን ሰለሞን ገ/ስላሴ በክብር እንግድነት በመገኘት ውድድሩን በይፋ አስጀምረዋል፡፡
3:00 ላይ አስቀድሞ የጎንደር ውሀ ስራ ቡድን ተብሎ የተመዘገበው ፋሲል ከተማ B ቡድን ከደቡብ ክልሉ አንጋጫ ከተማ ያደረገውን ጨዋታ 2-1 በሆነ ውጤት አሸንፏል። በጨዋታው እምብዛም ሳቢ ያልሆነ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴን ብንመለከትም ፋሲሎች በአመዛኙ የተሻሉ ሆነው ታይተዋል። 5ኛው ደቂቃ ላይ ዳዊት ዳሎ ያገኘውን ግልፅ የግብ አጋጣሚ አግዳሚ የመለሰበት በአንጋጫ በኩል ቀዳሚ ሙከራ የነበረች ሲሆን በ11ኛው ደቂቃ ላይ ሚካኤል በለጠ ሞክሮ በግብ ጠባቂው ነብዩ ክንፈ የወጣበት በፋሲል በኩል ቀዳሚው ሙከራ ነበር። 19ኛው ደቂቃ ላይ በፋሲል በኩል ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው አማካዩ ቅዱስ ግርማይ ግሩም ግብ አስቆጥሮ ቡድኑን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል። 30ኛው ደቂቃ ላይ የአንጋጫው ግብ ጠባቂ በሰራው ጥፋት በተሰጠ የፍፁም ቅጣት ምት ፋሲሎች መሪነታቸውን የማስፋት እድል ቢያገኙም አቤል እያዩ መትቶ ግብ ጠባቂው አድኖበታል፡፡
በሁለተኛው አጋማሽ ፋሲሎች ሙሉ የጨዋታ ብልጫ የነበራቸው ቢሆንም ግብ ሊያስተናግዱ ተገደዋል የ። 71ኛው ደቂቃ ላይ ሰላሙ ካሳ ግሩም ግብ አስቆጥሮ አንጋጫን አቻ ማድረግ ችሏል። ከጎሉ በኋላ ፋሲሎች ተደጋጋሚ ጥቃት በመሰንዘር 87ኛው ደቂቃ ላይ አጥቂው ቢኒያም አማረ በግምት ከ25 ሜትር ርቀት ባስቆጠረው ጎል 2-1 አሸንፈው ወጥተዋል።
በቀጣይ 5፡00 ላይ የጀመረው የኦሮሚያው ሀሩታ ከተማን ከወልዋሎ B ቡድን ያገናኘው ጨዋታ በወልዋሎ 2-1 ውጤት አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ እጅግ ጥሩ ፉክክር እና እልህ አስጨራሽ የሜዳ ላይ እንቅስቀሴን በተመለከትንበት ጨዋታ 7ኛው ደቂቃ ላይ ጣሂር ሰይፉ በድንቅ አጨራረስ አስቆጥሮ ሀሩታን መሪ ማድረግ ችሏል። የመጀመሪያው አጋማሽም በሀሩታ መሪነት ተጠናቋል።
በሁለተኛው አጋማሽ ብልጫ የነበራቸው ወልዋሎዎች ማራኪ እንቅስቃሴ በማሳየት ውጤቱን መቀልበስ ችለዋል። 62ኛው ደቂቃ ላይ አማካዩ ሀብቶም ዓለም ወልዋሎን አቻ ሲያደርግ 70ኛው ደቂቃ ላይ የሀሩታው ተከላካይ መሀመድ ከማል በሳጥን ውስጥ ኳስ በእጅ በመንካቱ የተሰጠውን የፍፁም በቅጣት ምት ዳዊት ብርሀነ አስቆጥሮ ጨዋታው በወልዋሎ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።
በቂ ትኩረት የተነፈገው ይህ ውድድር እንደ ፕሪምየር ሊጉ እና ከፍተኛ ሊግ ሁሉ ሰፊ ጥናት በማድረግ ትኩረት ሰቶ ወጣቶች የሚፈሩበት ለማድረግ እንሰራለን ሲሉ አቶ ኢሳይያስ ጂራ ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል፡፡