በዝውውር መስኮቱ በርካታ ተጫዋቾችን እያስፈረመ የሚገኘው ጅማ አባ ጅፋር ሦስት ተጫዋቾችን በዛሬው እለት በይፋ ማስፈረሙን አስታውቋል።
ከቅዱስ ጊዮርጊስ የረጅም ዓመታት ቆይታ በኋላ ክለቡን የለቀቁት አሉላ ግርማ እና ዘሪሁን ታደለ እንዲሁም ከኢትዮጵያ ቡና የለቀቀው አስቻለው ግርማ ጅማ አባጅፋርን የተቀላቀሉ ተጫዋቾች ናቸው።
በ2001 ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ዋናው ቡድን በማደግ በፍጥነት የመጀመርያ ተሰላፊ መሆን ችሎ የነበረው አሉላ ግርማ በቀጣይ ዓመታት በብሔራዊ ቡድን እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ውጤታማ ጊዜን ማሳለፍ ችሎ ነበር። ሆኖም ያለፉትን ሁለት ዓመታት ከጉዳት ጋር በተያያዘ ሲቸገር ተስተውሏል። ከፈረሰኞቹ ጋር መለያየቱን ተከትሎም በሁለት ዓመት ውል ጅማን ተቀላቅሏል። በተከላካይ እና አማካይ ስፍራ ላይ መጫወት የሚችለው አሉላ በኄኖክ አዱኛ መልቀቅ የተፈጠረውን ክፍተት እንደሚሸፍን ታምኖበታል።
እንደ አሉላ ሁሉ በሚሌንየሙ መጀመርያ ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ዋናው ቡድን ማደግ የቻለው ዘሪሁን ታደለ ሌላው በሀለት ዓመት ውል ጅማን የተቀላቀለ ተጫዋች ነው። ዘሪሁን በመጀመርያዎቹ ጊዜያት ብዙዎች ተስፋ ጥለውበት የነበረ ግብ ጠባቂ ቢሆንም በውሰት በመድን ካሳለፈው ጊዜ ውጪ በቅዱስ ጊዮርጊስ በመደበኛነት የውጪ ዜጋ ግብ ጠባቂዎች ተጠባባቂ ሆኖ ቆይቷል።
አስቻለው ግርማ ሶስት የቡና ቡድን ጓደኞቹን ተከትሎ ወደ ጅማ አምርቷል። አስቻለው በ2005 አጋማሽ ሱሉልታ ከተማን ለቆ ወደ ቡና ካመራ በኋላ ድንቅ ጊዜን አሳልፎ በ2008 ወደ ሀዋሳ ከተማ አምርቶ በ2009 በድጋሚ ወደ ቡና በመመለስ ያለፉት ሁለት የውድድር ዘመናትን ማሳለፍ ችሏል። የመስመር አጥቂው በጅማ የአንድ ዓመት ውል የፈረመ ሲሆን ውሉን ወደ ሁለት ዓመት ከፍ ለማድረግ ድርድር መሆኑ ተገልጿል።
ጅማ አባ ጅፋር የሶስቱ ተጫዋቾችን ዝውውር ጨምሮ እስካሁን በዝውውር መስኮቱ 11 ተጫዋቾችን ማስፈረም ችሏል።