በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ 28ኛ ሳምንት በዛሬው እለት 6 ጨዋታዎች ተካሂደው ደቡብ ፖሊስ በግብ ተንበሽብሾ ወደ መሪነት የተመለሰበትን ሀላባ እና አባ ቡና የተሸነፉበት እንዲሁም መቂ ከተማ ከሊጉ መውረዱን ያረጋገጠበት ውጤቶች ተመዝግበዋል።
በቴዎድሮስ ታከለ እና አምሀ ተስፋዬ
ሀዋሳ ላይ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ሆኖ ወልቂጤ ከተማን ያስተናገደው ደቡብ ፖሊስ 5-2 አሸንፏል። በጨዋታም ሆነ የግብ ሙከራዎች የተሻሉ የነበሩት ፖሊሶች ግቦች ማስቆጠር የጀመሩት ገና በመጀመርያዎቹ ደቁቃዎች ነበር። 3ኛው ደቂቃ ላይ በእለቱ ድንቅ ብቃቱን ሲያሳይ የነበረው ሚካኤል ለማ ከቀኝ በኩል ያሻገረለትን ኳስ ኬኒያዊው አንጋፋ አጥቂ ኤሪክ ሙራንዳ አስቆጥሮ ቡድኑን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል። 7ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ብርሀኑ በቀለ ያመቻቸለትን እድል ፈጣኑ የመስመር አጥቂ ብሩክ ኤልያስ ወደ ግብ ለውጦ የፖሊስን መሪነት ወደ ሁለት ማሳደግ ችሏል።
በግማሽ የውድድር ዓመት መቐለ ከተማን ለቆ ወደ ወልቂጤ ያመራው ሙሉጌታ ረጋሳ በ12ኛው ደቂቃ ከአክሊሉ ተፈራ ያገኛትን ኳስ አስቆጥሮ ልዩነቱን ማጥበብ ችሏል። ከጎሉ በኋላ ደቡብ ፖሊሶች ተደጋጋሚ ሙከራዎች በማድረግ በ34ኛው ደቂቃ በብርሀኑ በቀለ አማካኝነት መሪነቱን በድጋሚ ማስፋት ችለዋል። የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ አንድ ደቂቃ ሲቀረው አበባየሁ ዮሀንስ ከርቀት የሞከራት ኳስ የግቡ አግዳሚ የመለሰበት ኳስ ሌላው በደቡብ ፖሊስ በኩል የሚጠቀስ ሙከራ ነበር።
ሁለተኛው አጋማሽ እንደተጀመረ ብዙም ሳይቆይ ወጣቱ የመስመር አጥቂ ብሩክ ኤልያስ በፈጣን እንቅስቃሴ ይዞ በመግባት ያመቻቸውን ኳስ ኤሪክ ሙራንዳ ወደግብነት ቀይሮ የቡድኑን 4ኛ ጎል ሲያስቆጥር 77ኛው ደቂቃ ላይ አበባየሁ ዮሀንስ በጥሩ ሁኔታ ያቀበለውን ኳስ ብርሀኑ በቀለ በአግባቡ ተጠቅሞ የደቡብ ፖሊስን የማሳረጊያ ጎል አስቆጥሯል። ጨዋታው ሊጠናቀቅ በጭማሪው ደቂቃ ላይ ወልቂጤወች በሙሉጌታ ረጋሳ አማካኝነት ጎል አስቆጥረው ጨዋታው በደቡብ ፖሊስ 5-2 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ጅማ አባ ቡና በቡታጅራ ተሸንፎ ከ5 ቀናት በኋላ ከመሪነት ወርዷል። ጨዋታው እድተጀመረ በ2ኛው ደቂቃ የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ኤፍሬም ቶማስ ግብ አስቆጥሮ ቡታጅራዎች መሪ መሆን ችለዋል። በ50ኛው ደቂቃ ኤፍሬም ቶማስ በድጋሚ ባስቆጠረው ጎል መሪነቱን ሲያሰፋ 71ኛው ደቂቃ ላይ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን እየመራ የሚገኘው ብዙዓየሁ እንደሻው ለጅማ አባ ቡና ግበረ አስቆጥሮ ልዩነቱን አጥብቧል። ጨዋታው ሊጠናቀቅ 13 ደቂቃዎች ሲቀሩ የተቋረጠ ሲሆን ከ45 ደቂቃ በኋላ በድጋሚ ተጀምሮ ተጨማሪ ጎል ሳይቆጠር ጨዋታው በቡታጅራ ከተማ አሸናፊነት ተጠናቋል።
በጨዋታው መቋረጥ ምክንያት ዙርያ የቡታጅራ ቡድን መሪ ልሶከር ኢትዮጽያ ይህን ብለዋል። “የጅማ አባ ቡና ተጨዋች የኳስ አቀባይ በመምታቱ ህዝቡ ወደ ሜዳ በመግባት ከተጫዋቹ ጋር ግብግብ ፈጥሯል። የማታ ማታ ህዝቡን ከስታድየሙ በማስወጣት ቀሪውን ጨዋታ እንዲከናወን አድርገናል። ” በጅማ አባ ቡና በኩል አስተያየታቸውን ለማከል ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።
ወደ ሆሳዕና ያቀናው ሀላባ ከተማ በሀዲያ ሆሳዕና 1-0 ሽንፈትን አስተናግዶል። የተከላካይ መስመር ተጫዋቹ አብነት አባተ በ63ኛው ደቂቃ ብቸኛውን የማሸነፊያ ጎል አስቆጥሯል።
መቂ ከተማ በሜዳው በካፋ ቡና 3-2 ተሸንፎ ወደ አንደኛ ሊግ መውረዱን አረጋግጧል። በመጀመሪያ 10 ደቂቃ ላይ መቂዎች ቀዳሚ መሆን ቢችሉም በ23ኛው ደቂቃ አቡበከር ወንድሙ ለከፋ ቡና ግብ አስቆጥሮ አቻ አድርጓል። የመጀመሪያው አጋማሽ መጠናቀቂያ ላይ ምንተስኖት ታረቀኝ በ45ኛው ደቂቃ ላይ አስቆጥሮ ወደ በካፋ ቡና 2-1 መሪነት ወደ እረፍት ሲያመሩ ቴዎድሮስ ሰለሞን በ62ኛው ደቂቃ ለመቂ ግብ አስቆጥሮ አቻ መሆን ችለወ ነበር። ሆኖም በ78ኛው ደቂቃ ከፌደራል ፖሊስ ወደ ከፋ ቡና በሁለተኛ ዙር ያመራው ሳሙኤል ብርሃኑ ለከፋ ቡና የማሸነፊያውን ግብ አስቆጥሮ ጨዋታው በካፋ 3-2 አሸናፊነት ተጠናቋል። ውጤቱን ተከትሎ መቂ በምድብ ሀ የሚገኘው ሱሉልታ ከተማን ተከትሎ ወደ አንደኛ ሊግ መውረዱን ያረጋገጠ ሁለተኛው ቡድን ሆኗል።
በሌሎች የምድቡ ጨዋታዎች ዲላ ከተማ በመና በቀለ ጎል ስልጤ ወራቤን፣ ሀምበሪቾ በቴዲ ታደሰ ጎል ነጌሌ ከተማን በተመሳሳይ 1-0 በሆነ ውጤት አሸንፈዋል።
በወቅታዊ የፀጥታ ችግሮች ምክንያት ሻሸመኔ ከተማ ከ ናሽናል ሴሜንት፣ ቤንች ማጂ ቡና ከ ድሬዳዋ ፖሊስ ሊያደርጉ የነበረው ጨዋታ ወደ ሌላ ጊዜ ተላልፏል።