የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን(EBC) ለሁለተኛ ጊዜ የሚያከናውነው “የኢቢሲ ስፖርት ሽልማት”ን አስመልክቶ በተቋሙ ቅጥር ግቢ ውስጥ ዛሬ ከሰዓት ስለ ዝግጅቱ እና ስለ እጩዎቹ ማብራሪያ ተሰጥቷል።
8:30 ላይ በጀመረው ጋዜጣዊ መግለጫ በርከት ያሉ ሃሳቦች የተነሱ ሲሆን በዋናነት አምና በሁለት የስፖርት ዓይነቶች እና በአራት ዘርፎች የተጀመረውን የሽልማት ዝግጅት ዘንድሮም ለማስቀጠል እንደታሰበ እና ምን ምን አዳዲስ ነገሮች ዘንድሮስ አሉ በሚሉት ጉዳዮች ላይ ማብራሪያዎች ተሰጥተዋል። በመግለጫው ላይ ኢቢሲን በመወከል አቶ አቤል የኢቢሲ ምክትል ስራ አስፈፃሚ ፣ አቶ ደመረ የኢቢሲ ማርኬቲንግ ሃላፊ ፣ አቶ ዮናስ የኢቢሲ የስፖርት ክፍል ሃላፊ እና አቶ ጋሻው የኢቢሲ የብራንዲንግ እና ፒ አር ሃላፊ ተገኝተው ስለ ዝግጅቱ በየኃላፊነታቸው ገለፃ አድርገዋል።
የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በየዓመቱ የስፖርት ሽልማት የሚያዘጋጀው በስፖርተኞች ጠንካራ የፉክክር ስሜት ለመፍጠር እና የሃገራችንን ስፖርተኞች በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ ውጤታማ እንዲሆኑ የራሱን አስተዋጸኦ ለማበርከት እንደሆነ እና የስፖርት ቤተሰቡ የሀገር ውስጥ ስፖርት ላይ ያለውን ተሳትፎ ከፍ እንዲል በማሰብ እንደሆነ ተነግሯል። አቶ አቤል ስለ አላማው በዝርዝር ሲያስረዱ”ዋና ዓላማችን ስፖርቱን ለማበረታታት ነው። እንደ አንጋፋነታችን ብዙ ስራዎችን ከዚህም በላይ መስራት እንደሚጠበቅብን ብናውቅም የማህበራዊ ግዴታችንን እየተወጣን ወጣቶች እና ታዳጊዎች እንዲነሳሱ ለማድረግ ነው ይህንን የሽልማት ፕሮግራም አምና የጀመርነው” ብለዋል። አቶ አቤል ጨምረው “ዘንድሮ ከአምናዎቹ አራት ዘርፎች ሁለት አዳዲስ አምና ያልነበሩ ዘርፎችን ለመጨመር አስበን ከኮሚቴው ጋር ተነጋግረን ነበረ ፤ ነገር ግን ከኛም አቅም አንፃር ቀስ እያልን ብንሄድበት ያሻላል ብለን አንድ ዘርፍ ብቻ ነው የጨመርነው” ብለዋል። አቶ አቤል የአመቱ ምርጥ ወንድ እግር ኳስ ተጨዋች ፣ የአመቱ ምርጥ ሴት እግር ኳስ ተጨዋች ፣ የአመቱ ምርጥ ወንድ አትሌት ፣ የአመቱ ምርጥ ሴት አትሌት እና ዘንድሮ የተካተተው የህይወት ዘመን ተሸላሚ በተባሉ በአጠቃላይ በአምስት ዘርፎች ሽልማቶች እንደሚኖሩ ጠቁመዋል።
የስፖርት ባለሙያዎች ፣ የስፖርት ምሁራን እና የስፖርት ጋዜጠኞች በአባልነት ያቀፈ የቴክኒክ ኮሚቴ መዋቀሩን እና እጩዎችን የመምረጥ ስራ መሰራቱን የኮሚቴው ሰብሳቢ ጋዜጠኛ ዮናስ በመቀጠል የተናገሩ ሲሆን ከስፖርት ባለሙያዎች ውስጥ ከእግር ኳስ ፌደሬሽኑ እንዲሁም ከአትሌቲክስ ፌደሬሽኑ የተወከሉ ሰዎች እንዳሉበትም ጠቁመዋል። አቶ ዮናስ ስፖርተኞቹ የሚመረጡት 70 በመቶ ከዚሁ የቴልኒክ ኮሚቴ ድምፅ እንዲሁም ቀሪው 30 በመቶ የሚሆነው ድምፅ ደግሞ ከአድማጭ ተመልካቹ እንደሚሆን ጨምረው አስረድተዋል። በመቀጠል ዕጩዎች ስለተመረጡበት መንግድ አቶ ዮናስ ማብራሪያ ሲሰጡ “በሁለቱም የስፖርት አይነቶች ዕጩዎችን ለመምረጥ በጣም ተቸግረን ነበረ ፤ በተለይ በእግር ኳሱ። በኮሚቴው ውስጥ ከሁለቱም የስፖርት አይነቶች ከእግር ኳሱም ከአትሌቲክሱም የመጡት ባለሙያዎች መረጃ ይዘው ነው የመጡት ነገር ግን በእግር ኳሱ የተደራጀ መረጃ እንደፈለግነው አላገኘንም ነበር። ከአትሌቲክስ ፌደሬሽን የመጡት ሰዎች በጣም የተደራጀ እና የተሟላ መረጃ ነው ይዘው የመጡት ይህ ደግሞ ትንሽ ነገሮችን አቅለውልን ነበር። “ብለዋል። “ኮሚቴው የየራሱን ምርጫ በመጀመሪያ እንዲያደርግ ነበር ያደረግነው። በመቀጠልም በየግል የተመረጡትን በጋራ ከተነጋገርንበት እና መግባባቶች ላይ ከደረስን በኃላ የመጨረሻዎቹን ለማሳወቅ ወደናል” ብለዋል አቶ ዮናስ።
በመቀጠል ከጋዜጠኞች ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሾች የተሰጡ ሲሆን በተለይ ስፖርተኞቹ የተመረጡበትን መስፈርት እና በማብራሪያው ያልተነሱ ጉዳዮች ላይ ምላሾች ተገኝተዋል። መስፈርቱን በተመለከተ ከ2009 ነሃሴ ወር እስከ 2010 ነሃሴ ወር በሁለቱም የስፖርት ዓይነቶች ስፖርተኞች የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ለማየት እንደተሞከረ እና በወንዶቹ የእግር ኳስ ዘርፍ በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ እና በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የሚደረጉ ጨዋታዎችን ከብሄራዊ ቡድን እንቅስቃሴ ጋር ለመፈተሽ እንደተሞከረ ተገልጿል። የሴቶችን የእግር ኳስ ዘርፍ በተመለከተ ደግሞ በአንደኛ ዲቪዝዮንም ሆነ በሁለተኛ ዲቪዝዮን የሚደረጉ ጨዋታዎችን ለማየት እንደተጣረ እና ሉሲዎቹ በቅርቡ በሴካፋ ውድድር ያደረጉዋቸውን ጨዋታዎች ከግምት ገብተዋል። ዝግጅቱ ቅዳሜ መስከረም 6 በሸራተን ሆቴል እንደሚደረግ ሲሆን ከአምናው የተሻለ ድባብ ለመፍጠር እንደሚጣርም ተነግሯል። በአጠቃላይ በመግለጫው ላይ ከዘንድሮ የሽልማት ዝግጅት ውጪ በቀጣይ ተቋሙ በተለያዩ ዘርፎች ሽልማት ለማዘጋጀት እንደሚሰራ እና ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ስፖርቱን ለማሳደግ እንደሚለፋ ተገልጿል።
የኢቢሲ የስፖርት ሽልማት የወንዶች እግር ኳስ ዘርፍ ዕጩዎች
ተመስገን ገ/ኪዳን ከጅማ አባ ጅፋር ፣ ከነዓን ማርክነህ ከአዳማ ከተማ ፣ ይሁን እንዳሻው ከጅማ አባ ጅፋር ፣ አብዱልከሪም መሃመድ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ ሄኖክ አዱኛ ከጅማ አባ ጅፋር ፣ አማኑኤል ገ/ሚካኤል ከመቐሌ ከተማ ፣ አዲስ ግዳይ ከሲዳማ ቡና ፣ አማኑኤል ዩሃንስ ከኢትዮጵያ ቡና ፣ ሙሉአለም መስፍን ከቅዱስ ጊዮርጊስ እና ምንይሉ ወንድሙ ከመከላከያ
የኢቢሲ የስፖርት ሽልማት የሴቶች እግር ኳስ ዘርፍ ዕጩዎች
ምርቃት ፈለቀ ከሃዋሳ ከተማ ፣ ሎዛ አበራ ከደደቢት ፣ ህይወት ደንጊሶ ከንግድ ባንክ ፣ አረጋሽ ካልሳ ከኢት.ወጣቶች አካዳሚ ፣ ሴናፍ ዋቁማ ከአዳማ ከተማ ፣ ብርቱካን ገ/ክርስቶስ ከደደቢት ፣ እመቤት አዲሱ ከመከላያ ፣ ሰናይት ቦጋለ ከደደቢት ፣ አለምነሽ ገረመው ከኢት.ኤሌክትሪክ እና መሰሉ አበራ ከቅዱስ ጊዮርጊስ።
የስፖርት ቤተሰቡ በአጭር የፅሁፍ መልዕክት(SMS) ፣ በኢቢሲ ማህበራዊ ትስስር ገፆች እና በድረ ገፅ ለዕጩዎቹ በተሰጠ መለያ ኮድ በመጠቀም ድምፅ መስጠት እንደሚችል ተጠቁሟል።