ይድነቃቸው ተሰማ ፡ የአፍሪካ እግር ኳስ አባት (ክፍል 1)


በሲራክ ተመስገን


ጋዜጠኛ ገዳሙ አብርሃ «የጅብራልታር ቋጥኝ» ስለሚላቸው ድንቅ የአፍሪካ ሰው ብዙዎች የእድሜ እኩያዎቼ አያውቁም። ሚዲያዎችም ስለዚህ የአፍሪካ እግር ኳስ አባት ሲያወሩ አይታይም። ቅድስ ጊዮርጊስ በስማቸው ከሰየመላቸው የታዳጊዎች ውድድርና አዲስ ያስገነባውን አካዳሚ በስማቸው ከመሰየሙ በስተቀር ይድነቃቸው ከነመፈጠራቸው ተረስተዋል። እነዚህ መግፌኤዎች ናቸው ስለዚህ ድንቅ አፍሪካዊ ብዕሬን እንድመዝ ያስደረገኝ። ይህን ፅሁፍ ሳዘጋጅ ይድነቃቸው በአለምና በስፖርት አለም የሚለው መፅሐፍ ትልቅ የመረጃ ግብአት ሆኖኛል።

ይድነቃቸው ተሰማ ማናቸው?

ክቡር ይድነቃቸው ተሰማ ከአባታቸው ባለቅኔ ከነጋድራስ ተሰማ እሸቴ እና ከእናታቸው ከወ/ሮ ሙላቷ ገ/ስላሴ መስከረም 1 1914 ዓም በጅማ ከተማ ተወለዱ። እንደማንኛውም የዘመኑ ልጆች እድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ የቄስ ተማሪ ቤት ገቡ።

ከ6—14 ዓመት ዕድሜያቸው ዘመናዊ የፈረንሳይኛ ትምህርት በአሊያንስ፣ በዳግማዊ ምንሊክና በተፈሪ መኮንን ት/ቤቶች ተከታትለዋል። ዕድሚያቸው 14 በሆነበት ጊዜ ጣሊያን ኢትዮጵያን በመውረሩ በኢጣሊያ ሚሲዮን ትምህርት ቤት በመዘዋወር ለሀገር ተወላጆች የሚሰጠውን ትምህርት አጠናቀዋል። ከዚህ በኋላ ያለውን ቀሪ እድሜያቸውን በተጫዋችነት ፣ አሰልጣኝነት እና በአመራርነት አሳልፈው ነሐሴ 13/1979 ከዚህ አለም በሞት ተለይተዋል።

እኚህ ሰው ከእድሜያቸው 45 አመታት ያህል ኳስ በመጫወት፣ በማሰልጠን፣ ኳስን በመዳኘት፣ የኳስ ዳኞችን በማሰልጠን፣ አንዳንዴም በሬዲዮ ኳስ በማስተላለፍ፣ የእግር ኳስ ክለቦችና ፌዴሬሽኖችን በማደራጀት አለማቀፍ የስፖርት ጉባኤዎች ላይ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ፣ የስፖርት ህጎች እና ደንቦችን ወደ አማርኛ በመተርጎም፣ በምክትል ሚኒስትርነት የኢትዮጲያ ስፖርት መሪ በመሆን ነበር ያሳለፉት።

ዋና ዋና የይድነቃቸው ስራዎች

እግር ኳሰኛው ይድነቃቸው

ይድነቃቸው እግር ኳሰኛ ብቻ ሳይሆን ብስክሌተኛና ሯጭም ጭምር ነበር። ይድነቃቸው ለአንጋፋው ቅ/ጊዮርጊስ ክለብ ለ23 ዓመታት ተጫውቷል። በእነዚህ የ23 አመታት ቆይታ ይድነቃቸው በጊዜው ዝነኛ ተጫዋች ነበር።

ጣልያን ሀገራችንን በወረረ ጊዜ የሮማ ብርሃን የተሰኘ ጋዜጣ ይታተም ነበር። ይህ ጋዜጣ በአንድ ወቅት የያኔው አራዳ የአሁኑ ቅ/ጊዮርጊስ ክለብ ከ 6ኪሎ ክለብ ጋር ያደረገውን ጨዋታ ዘገባ ማንበብ የይድነቃቸው ብቃት ምን ያህል እንደነበር ለመገንዘብ ይረዳል።

«. .. ነገር ግን ምንም በራቸውን (6ኪሎዎች) አጠንክረው ይዘው ቢጫወቱም ኳሲቱ ዙራ ዙራ ከዚያው ከይድነቃቸው እግር ገባችና ይድነቃቸው እንደልማዱ ኳሲቱን ይዞ ከፊት ያገኘውን ልጅ ሁሉ እያሳለፈና እያስዘለለ ሲሮጥ ኳሲቱ በገዛ እጅዋ የምትሮጥ ትመስል ነበር እንጂ እሱ በእግሩ የሚነዳት አይመስልም ነበር።»

በወቅቱ አራዳ(ያኔ የቅ/ጊዮርጊስ ስም አራዳተብሎ ተቀይሮ ነበር) 6ኪሎዎችን ሶስት ለምንም ነበር የረታው። ሶስቱንም ግቦች ይድነቃቸው ነበር ያስቆጠራቸው።

ይድነቃቸው ለ23 አመታት በቅ/ጊዮርጊስ ክለብ ሲቆይ አሰልጣኝም፣ ተጫዋችም(አምበል) ሆኖ አሳልፏል። ለኢትዮጲያ ብሄራዊ ቡድንም ለ15 ጊዚያት ያህል ተሰልፎ ተጫውቷል። ከዚህ በተጨማሪ የብሄራዊ ቡድንም ዋና አሰልጣኝ ነበር። የ3ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የኢትዮጲያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝም እሱ ነበረ።

አመራሩ ይድነቃቸው

በ1936 ዓም የማስታወቂያ ሚኒስቴር በነበሩት ከክቡር አቶ ዓምደሚካኤል ደሳለኝ በተደረገላቸው ድጋፍ የስፖርት ፅ/ቤት አቋቋሙ። ነገር ግን አቶ ይድነቃቸው ከስፖርት ፅ/ቤት የሚያገኙት ወርሃዊ ደሞዝ ሊባቃቸው ስላልቻለ ወደ ሚኒሊክ ሆስፒታል አስተዳዳሪነት ተዘዋወሩ። የስፖርት ፅ/ቤት ምስረታውም በዚሁ ከሸፈ። ይድነቃቸው የነፍስ ጥሪያቸው ስፖርት ነበረችና ከአራት አመታት በኋላ ስራቸውን ትተው ከጄነራል ሙሉጌታ ቡሊ በተገኘ የ500 ብር ብድር እና አንድ ክፍል ፅ/ቤት እንደገና በጃንሜዳ የስፖርት ፅ/ቤት አቋቋሙ። ወርሃዊ ክፍያውም ከሜዳ ገቢ 5% እንዲሆን ተወሰነ።

በ1944 ዓም ነገሮች ሁላ እየተስተካከሉ ሄደው የኢትዮጲያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ተመሰረተ። ይድነቃቸውም ዋና ፀሀፊ ሆነው በመመረጥ የሙሉ ጊዜ ስራቸው ሆነ።

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን መስራቹ ይድነቃቸው

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን በ1957 ካርቱም ላይ በሱዳን፣ በግብፅ፣ በኢትዮጵያና በደቡብ አፍሪካ አባልነት ተመሰረተ። ይህ ኮንፌዴሬሽን በአፍሪካ ምድር የተመሰረተው የመጀመሪያው አህጉራዊ ማህበር ነው።

በዚህ ማህበር ምስረታ ላይ ይድነቃቸው ጉልህ አስተዋእፆ አድርገዋል። ይድነቃቸው በ1965 አራተኛው የኮንፌዴሬሽኑ ፕሬዘዳንት በመሆን ለአራት የስልጣን ዘመናት ማለትም ህይወታቸው እስካለፈችበት ነሃሴ 13/1979 በፕሬዘዳንትነት አሳልፈዋል።

ይድነቃቸው በዚህ የስልጣን ዘመናቸው ለአፍሪካ እግር ኳስ የተለያዩ ስራዎችን ሰርተዋል። የትንባሆና የአልኮል ማስታወቂያዎች በአፍሪካ ስታድየሞች እንዳይሰቀሉ ማድረጋቸው ፣ እንደ ድርጅት አፓርታይድን መቃወማቸው፣ የአፍሪካ ዳኞች እና ኮሚሽነሮች የአለም አቀፍ ውድድሮች ልምድ እንዲቀስሙ ማድረጋቸው፣ አፍሪካ በራሷ ሀኪሞች፣ አሰልጣኞች እና ዳኞች ራሷን እንድትችል ማድረጋቸው ይድነቃቸው ለአፍሪካ እግር ኳስ ከሰሯቸው ከብዙ በጥቂቱ ናቸው።

በኢትዮጲያ ስፖርት ላይ የነበሩት ማዕረጎች

1.. በ1952 የኢትዮጲያ ስፖርት ኮንፌዴሬሽን ዋና ፀሐፊ
2. በ1955 በዋና ዳይሬክተርነት ማዕረግ የኢትዮጲያ ስፖርት ኮንፌዴሬሽን ዋና ፀሐፊ
3. በ1960 የረዳት ሚኒስቴር ማዕረግ
4. በምክትል ሚኒስተርነት ማዕረግ
5. ከ1968 እስከ 1973 በኮሚሸርነት ማዕረግ

አለም አቀፍ ተግባራቶች
1. ከአራት የስልጣን ዘመናት (እያንዳንዱ አመት የአራት የስራ አመታት አሉት) የአፍሪካ እግርኳስ ኮንፌዴሬሽን ፕሬዘዳንት
2. የአለም አቀፍ ኦሎምፒክ ኮሚቴ አባል።

ስለዚህ የስፖርት ሰው ብዙ ማለት ይቻላል። በዚህች ቁንፅል መጣጥፍ የይድነቃቸውን ለሀገራችን ስፖርት አልፎም ተርፎ ለአህጉራችን ስፖርት ያደረጉትን ተጋድሎ መግለፅ አይቻልም።

እኚህ ሰው ለአንድ ግማሽ ምእተ አመት ስለስፖርት እድገት ሲያስቡ፣ ስለስፖርት እድገት ሲሰሩ፣ ስለስፖርት እድገት በአህጉር ደረጃ ሲመክሩ ያሳለፉ ድንቅ ኢትዮጲያው ሰው ነበሩ።


ክፍል 2ን ለማግኘት ይህንን ይጫኑ

የይድነቃቸው ተፅዕኖ በአፍሪካ መድረክ


 

ያጋሩ