የዝውውር መስኮቱ ከተከፈተ ሁለት ተጨዋቾችን ብቻ በማስፈረም ተቀዛቅዞ የቆየው ሲዳማ ቡና የኋላ መስመሩ ላይ ያተኮረ የአምስት ተጨዋቾች ፊርማን አጠናቋል።
ሰንደይ ሙቱኩ እና ተስፉ ኤልያስ ወደ ሲዳማ ካመሩ በኋላ ቡድኑ ከዝውውር ገበያው ገለል ብሎ ቆይቷል። ሲዳማ ምንም እንኳን በተጨዋቾች ሽምያው በሌሎቹ ክለቦች ፍጥነት እየተጓዘ ባይገኝም ዛሬ በተሰማው ዜና ተጨማሪ አምስት ተጨዋቾችን የበድኑ አካል አድርጓል። በአመዛኙም ትኩረቱ ከከፍተኛ ሊግ በተገኙ ተጨዋቾች እና የተከላካይ መስመሩን በማጠናከር ላይ የሆነ ይመስላል።
ከአምስቱ ፈራሚዎች መካከል በፕሪምየር ሊጉ የረጅም ጊዜ ልምድ ያለው ግርማ በቀለ ተጠቃሽ ነው። የአበበ ጥላሁንን ከክለቡ መለየት ተከትሎ በቦታው ተጨዋች ያስፈልጋቸው የነበሩት ሲዳማዎች ግርማን ምርጫቸው አድርገዋል። በ2009 የውድድር ዓመት መጀመሪያ ኢትዮ ኤሌክትሪክን ተቀላቅሎ የነበረው የመሀል ተከላካዩ ከቀድሞው ክለቡ ጋር ሁለት የውድድር ዓመታትን አሳልፏል። ከዚያ ቀደምም ያደገበት ሀዋሳ ከተማን ለረጅም ጊዜ አገልግሎ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የግማሽ የውድድር ዘመን ቆይታ ማድረጉ ይታወሳል።
ሌቸቹ ሁለት ፈራሚዎች ደግሞ ከከፍተኛው ሊግ የተገኙት ሚሊዮን ሰለሞን እና ዳግም ንጉሴ ናቸው። የግራ መስመር ተከላካይ የሆነው ሚሊዮን ሰለሞን በዓመቱ መጀመሪያ ሀምበርቾን ለቆ ዘንድሮ በአዲስ አበባ ከተማ ያሳለፈ ሲሆን ለሲዳማ ቡና ከተስፉ ኤልያስ ቀጥሎ ሁለተኛው የቦታው ፈራሚ ሆኗል። ከወላይታ ድቻ በመልቀቅ በኢኮስኮ አንድ የውድድር ዓመትን መቆየት የቻለው ሦስተኛው የሲዳማ ቡና ፈራሚ ዳግም ንጉሴም ወደ ፕሪምየር ሊጉ የመመለስ ዕድል አግኝቷል።
በተያያዘ ዜናም ክለቡ ሌሎች ሁለት ተጨዋቾችን ከከፍተኛ ሊግ ቢያስፈርምም አሁን በሚገኙበት ቡድናቸው ውስጥ ወሳኝ ጨዋታዎች የሚጠብቋቸው በመሆኑ ስማቸውን ከመጥቀስ ተቆጥቧል።