የጅማ አባ ቡና ቅሬታ
በኢትዮጽያ ከፍተኛ ሊግ በ2010 በምድብ ለ ውድድር ተመድቦ ውድድሩን እያደረገ የሚገኘው ጅማ አባቡና ባሳለፍነው ሳምንት ከቡታጅራ ጋር ባደረገው ጨዋታ 2-1 መሸነፉ የሚታወስ ነው። በጨዋታው ላይ ቅሬታ እንዳላቸው የለገለፁት ጅማዎች ለፌዴሬሽኑ ደብዳቤ አስገብተዋል።
የጅማ አባቡና ስፖርት ክለብ ስራ አስኪያጅ አቶ ግርማ ከበደ ስለ ቅሬታቸው ለሶከር ኢትዮጵያ ይህን ብለዋል፡-
“ጨዋታውን ከመጀመራችን በፊት ፕሪማች ላይ ሜዳው አጥር እንደሌለው የገልፅን ቢሆንም በቂ ጥበቃ እንደሚመደብ ተነግሮን የተገኘው የፀጥታ ኃይል ግን ከስድስት የማይበልጡ ነበሩ። በጨዋታው 75ኛው ደቂቃ ላይ የኛ ተጨዋች ከኳስ ተቀባዮች ኳስ በሚቀበልበት ወቅት ኳስ አቀባዩን መተሃል በሚል ህዝቡ ወደ ሜዳ በመግባት ድብድባ አከናውኖብናል፣ ንብረቶች ጠፍተዋል፣ አንድ ተጫዋችንም በመጎዳቱ ወደ ሆስፒታል ተልኮ በሪፈራል ጥቁር አንበሳ ህክምናውን የሚከታተል ይሆናል። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆነን ጨዋታውን እንድጨርስ የተገድድን ሲሆን ይህም ተጫዋቹችን ላይ ከፍተኛ ጫና አሳድሯል። በዚህም ከኳስ እስከ ስልክ በርካታ ንብረት የጠፋብን ሲሆን ጨዋታውን ተገደን መጫወታችን ከግምት ገብቶ ውሳኔ እንዲሰጠን ጠይቀናል። በቀጣይ ከሜዳችን ውጭ ለምናደርገው ጨዋታ ተመሳሳይ ድርጊት እንዳይፈፀምብን በቂ የፀጥታ ኃይል እኖዲኖር ቢደረግ፤ ይህ የማይሆን ከሆነ ግን በገለልተኛ ሜዳ እንድንጫውት እንዲያደርግ ጠይቀናል። ”
የአሰልጣኞች ቅጥር
በቀጣይ ዓመት ለከፍተኛ ሊግ የሚወዳደሩ ቡድኖች ራሳቸውን ለማጠናከር ስራቸውን አሰልጣኝ ከመቅጠር ለመጀመር ያቀዱ ይመስላሉ። ዘንድሮ ወደ ከፍተኛ ሊግ የወረደው አርባምንጭ ከተማ አሰልጣኝ መሳይን በመቅጠር ቀዳሚ ሲሆን አሁን ደሞ ሌላኛው ከፕሪምየር ሊግ የወረደው ወልድያ የአሰልጣኝ ቅጥር ማስታወቂያ አውጥቷል። ሌላው ከፕሪምየር ሊግ በመጨረሻው እለት የወረደው ኤሌክትሪክም ከአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ጋር የመቀጠሉ ጉዳይ አጠራጣሪ ሲሆን ስሙ ከቀድሞው የክለቡ ታሪካዊ ተጫዋች አንዋር ያሲን ጋር ተያይዟል። 5 ጨዋታ እየቀረው ከአሰልጣኙ ጋር የተለያየው አዲስ አበባ ከተማ ማስታወቂያ እንደሚያወጣ ሲጠበቅ ኢትዮጵያ መድንም ሌላው አሰልጣኝ ፍለጋ ላይ የሚገኝ ክለብ ነው።
ቡራዩ እና ለገጣፎ ጨዋታቸውን ጨርሰዋል
የከፍተኛ ሊጉ ምድብ ሀ ሊጠናቀቅ 30ኛው ሳምንት መርሐ ግብር ብቻ ይቀራል። ሆኖም የማደግ ተስፋም ሆነ የመውረድ ስጋት የሌለባቸው ቡራዩ ከተማ እና ለገጣፎ ለገዳዲ ጨዋታቸውን ቀደም ብለው በማድረግ የውድድር ዘመናቸውን አገባደዋል። ዛሬ ረፋድ ላይ የተደረገው የሁለሁ ቡድኖች ጨዋታ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ሲጠናቀቅ ሱራፌል አየለ በ15ኛው ደቂቃ ለለገጣፎ፣ አብዱልከሪም ከድር በ38ኛው ደቂቃ ለቡራዩ ግቦቹን አስቆጥረዋል።
የምድብ ሀ 30ኛ ሳምንት መርሐ ግብር
እሁድ ነሀሴ 13 ቀን 2010
04:00 ባህር ዳር ከተማ ከ አአ ከተማ
04:00 አውስኮድ ከ ኢትዮጵያ መድን
04:00 ሱሉልታ ከተማ ከ ሰበታ ከተማ
04:00 ነቀምት ከተማ ከ አክሱም ከተማ
ሰኞ ነሀሴ 14 ቀን 2010
04:00 የካ ክ/ከተማ ከ ኢኮስኮ
06:00 ፌዴራል ፖሊስ ከ ሽረ እንዳስላሴ
06:00 ደሴ ከተማ ከ ወሎ ኮምቦልቻ
የምድብ ለ 29ኛ ሳምንት ጨዋታዎች
እሁድ ነሀሴ 13 ቀን 2010
09:00 ሀምበሪቾ ከ ደቡብ ፖሊስ
09:00 ነጌሌ ከተማ ከ መቂ ከተማ
09:00 ካፋ ቡና ከ ዲላ ከተማ
09:00 ስልጤ ወራቤ ከ ቡታጅራ ከተማ
09:00 ጅማ አባ ቡና ከ ሻሸመኔ ከተማ
09:00 ናሽናል ሴሜንት ከ ሀዲያ ሆሳዕና
09:00 ሀላባ ከተማ ከ ቤንች ማጂ ቡና
09:00 ድሬዳዋ ፖሊስ ከ ወልቂጤ ከተማ