በሰኔ ወር 2019 በካሜሩን አስተናጋጅነት እንደሚካሄድ የሚጠበቀው የአፍሪካ ዋንጫ ሁለተኛ የምድብ የማጣርያ ጨዋታዎች ጳጉሜ ወር ላይ ይከናወናሉ። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከሴራሊዮን ጋር የሚያደርገው ጨዋታ ሀዋሳ ላይ ጳጉሜ 4 እንዲከናወን መወሰኑ የሚታወስ ሲሆን በቀጣይ የሜዳቸው ጨዋታን የሚያከናውኑበት ስታድየምም ታውቋል።
ብሔራዊ ቡድኑ በ3ኛ ቀን መርሐ ግብር መስከረም 30 ቀን 2011 ኬንያን በሜዳው የሚያስተናግድበት ጨዋታ በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታድየም ላይ እንዲከናወን የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ወስኗል። የሚመለከተው አካልም አስፈላጊውን ዝግጅት እንዲያከናውን የሚገልፅ ደብዳቤ ማዘጋጀቱ ተገልጿል። ከዚህ ቀደም በርካታ የክለብ እና የብሔራዊ ቡድን ጨዋታዎች ያስተናገደው የባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታድየም ለመጨረሻ ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ያስተናገደው በሰኔ ወር 2007 ከሌሶቶ ብሔራዊ ቡድን ጋር እንደነበር የሚታወስ ነው።
የአፍሪካ ዋንጫው በውድድር ወቅት ለውጥ ምክንያት ወደ ሰኔ ወር መገፋቱን ተከትሎ የማጣርያ ጨዋታዎች ላይ ሽግሽግ የተደረገ ሲሆን ከመስከረም 28 እስከ ህዳር 3 ባሉት ቀናት ውስጥ ሁለት የምድብ መርሐ ግብሮች ይከናወናሉ። ኢትዮጵያም በሜዳዋ እና ከሜዳዋ ውጪ ከኬንያ ጋር ጨዋታዋን የምታከናውን ይሆናል።
ኢትዮጵያ በምድብ 6 ከጋና፣ ኬንያ እና ሴራሊዮን ጋር ተደልድላ በመጀመርያ የምድብ ማጣርያ ጨዋታዋ በጋና ከሜዳዋ ውጪ 5-0 መሸነፏ የሚታወስ ነው።