አምና በፕሪምየር ሊጉ ካየናቸው የውጭ ሃገር ግብ ጠባቂዎች አንዱ ነው፡፡ በመጣበት ዓመት ለአፄዎቹ ሁሉንም የሊግ ጨዋታዎች ተሰልፎ ተጫውቷል፡፡ በመጀመሪያ ዓመቱ ከጎንደሩ ክለብ ምርጥ ተጫዋቾች መካከል አንዱ መሆንም ችሏል፡፡ ሚኬል ሳማኬ ንጂ። ተጨዋቹ ዛሬ የመጀመሪያ ዓመት የኢትዮጵያ ቆይታው እና ተያያዥ ጉዳዮችን በተመለከተ ከሶከር ኢትዮጵያ የፈረንሳይኛ ባልደረበ ተሾመ ፋንታሁን ጋር ቆይታ አድርጓል። መልካም ንባብ!
በመጀመሪያ የእግር ኳስ ሕይወትህን እና እንዴት ወደ ኢትዮጵያ እንደመጣህ ንገረን…
ሚኬል ሳማኬ እባላለሁ። ኢትዮጵያ በውጭ ሃገር ፕሮፌሽናል ጨዋታን የጀመርኩባት ሃገር ናት። ለአምስት ዓመታት ያህል በሃገሬ በማሊ እጫወት ነበር፡፡ በ2015 ኢኳቶሪያል ጊኒ በተደረገው የአፍሪካ ዋንጫ ሃገሬን አገልግያለው፡፡ እንደምታውቀው ማሊ ውስጥ ያለፉትን ሶስት እና አራት ዓመታት የፖለቲካ አለመረጋጋት አለ፡፡ የባለፈው ዓመት ውድድር መጀመሪያ ላይ አንድ ናይጄሪያዊ የተጫዋች ወኪል ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ ክለቦች አንዱ ባንተ ላይ ፍላጎት አለው መሞከር ትፈልጋለህ ወይ ሲለኝ በደስታ ተቀብዬ ለሙከራ መጣሁ። ክለቡም ስለወደደኝ ለፋሲል ፈረምኩ ማለት ነው፡፡
ወኪልህ ያመጣህ ፋሲል ትጫወታለህ ብሎ ነግሮህ ነው ወይስ አንድ ክለብ አይጠፋም ልፈልግልህ በሚል ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ ክለቦች ሊሞክርልህ ነው?
አይ ወደ ኢትዮጵያ ስገባም ፋሲል በላከልኝ ግብዣ ነው ቪዛ ያገኘሁት፡፡ የመጣሁት በፋሲል ክለብ ለመጫወት ነው። ይሄን ኤጀንቱም ነግሮኝ ነበር ፤ እንደመጣሁ ደቡብ ሲቲ ካፕ ላይ ተጫወትኩ። የሙከራ ጊዜዬን በሚገባ አልፌ ለሁለት ዓመት በፋሲል ለመጫወት ፈረምኩ፡፡
ከመምጣትህ በፊት ስለኢትዮጵያ እግር ኳስ ታውቅ ነበር?
ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣቴ በፊት ስለሃገሪቱ እግር ኳስ ምንም መረጃ አልነበረኝም፡፡ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ውጭ የማውቀው ክለብ ስም እንኳን አልነበረም፡፡ በርግጥ ሁለት ሶስቴ በአዲስ አበባ በኩል ትራንዚት አድርጌ አልፌ አውቃለው፡፡ 2015 ወደ ጊኒ ስንሄድ በኢትዮጵያ በኩል ነበር የተጓዝነው፡፡ ከመጣሁ በኋላ ግን በሃገሪቱ ውስጥ ጥሩ የእግር ኳስ ደረጃ እንዳለ ተረድቻለው፡፡
ሊጉ ውስጥ አብዛኛው የውጭ ሃገር ግብ ጠባቂ ነው፡፡ በሃገሪቱ ውስጥ ያለውን የሃገር ውስጥ ግብጠባቂ ችግር እንዴት ታየዋለህ?
በጣም ከባድ ጥያቄ ነው፡፡ እውነትም ብዙ መሥራት ይጠይቃል፡፡ በርግጥ ጥሩ ጥሩ ግብ ጠባቂዎች አሉ። ለምሳሌ ሁለቱም የመከላከያ ግብ ጠባቂዎች በጣም ጥሩ ግብ ጠባቂዎች ናቸው፡፡ ደረጃቸው ከፍ ያሉ በረኞች ናቸው፤ ነገር ግን በነሱ ደረጃ ሌላ ግብ ጠባቂ አለማየቴ እኔንም ይገርመኛል፡፡ በሊጉ ውስጥ ጥሩ ጥሩ ኢትዮጵያዋን ተጫዋቾች አሉ በረኞች ግን በዛ መጠን አላየሁም፡፡
ከራስህና ከሃገርህ ልምድ በመነሳት ችግሩ ምን ይመስልሃል?
ችግሩ ስልጠናው ሊሆን ይችላል፤ የበረኞችን አቅም የሚያሳድግ ስልጠና ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ ፋሲል ውስጥ 3 ግብ ጠባቂዎች አለን፡፡ ነገር ግን ሰላሳ ሁለቱንም ጨዋታ የተጫወትኩት እኔ ነኝ ፤ 30 የሊግ ሁለት የጥሎ ማለፍ ማለቴ ነው፡፡ እኔ ሁሌም ብሰለፍ ደስ ይለኛል። ነገር ግን ለተጠባባቂዎች ደስ አይልም፡፡ አሰልጣኞቼ ደግሞ እኔን ይመርጣሉ፡፡ ሶስታችንም በተመጣጣኝ ደረጃ ብንሆንና ፉክክር ቢኖር ለሁላችንም የተሻለ ይሆናል፡፡
በክለብህ ያለውን የግብ ጠባቂ ሥልጠና እንዴት ታየዋለህ?
ጥሩ ስልጠና አለ። ነገር ግን ዘመናዊ እግር ኳስ ከዚህ በላይ ነው የሚጠይቀው፡፡ አሰልጣኞችም ቢሆን ዘመናዊ ስልጠና ያስፈልጋቸዋል፡፡ የቀድሞ በረኛ መሆን ለዘመናዊ እግር ኳስ በቂ አይደለም ፤ የእግር ኳስ ሳይንስ እንደሚታየው ዕለት ዕለት ይቀያየራል። ስለዚህ ከዘመኑ ጋር አብሮ መጓዝ ያስፈልጋል፡፡ አሰልጣኖቹ ወረቀት ያስፈልጋቸዋል፣ ትምህርት ያስፈልጋቸዋል፡፡ ምሳሌ በማሊ ብሔራዊ ቡድን የበረኛ አሰልጣኝ ሆኖ የሚያሰለጥነኝ የነበረው ማማዱ ሲዲቤ ለረጅም ዓመታት የማሊ ብሔራዊ ቡድንን ግብ የጠበቀ ታዋቂ ግብ ጠባቂ ነበር። ይህ ግብ ጠባቂ በፈረንሳይ እና በጀርመን ተጫውቶ አልፏል፡፡ ነገር ግን ወደሥልጠና ሲመጣ በግሪክ ሥልጠና ወስዷል፤ የአውሮፓ እግር ኳስ ማኅበር ወረቀትም አለው። ከዛም በፈረንሳይ ብዙ ሰልጠናዎችን ወስዷል፡፡ ይህ ለማሊ በረኞች ትልቅ ዕድል ነው፡፡ እኔም ከሱ ጋር በመስራቴ ዕድለኛ ነኝ፡፡
እግር ኳሳችን ውስጥ ዋና ችግር ምን ይመስልሃል? ምንስ መደረግ አለበት ?
የታዳጊዎች ችግር ዋናው ይመስለኛል፡፡ የታዳጊዎች መኖር ለአንድ ሃገር እግር ኳስ በጣም አስፈላጊ ነው ፤ ተተኪ በጣም ያስፈልጋል፡፡ ማንም ተጫዋች እግር ኳስን ዘላለም መጫወት አይችልም፡፡ ስለዚህ በቡድን ውስጥ ሁሌም ተተኪ ያስፈልጋል፡፡ ተተኪ ሲኖር ሲኒየር ተጫዋቾች በርትተው ይሰራሉ፡፡ ከታች አድጎ ክለቡን የሚረከብ ከሌለ ለእግር ኳሱ አደጋ ነው፡፡ ዘንድሮ የማሊ ብሄራዊ ቡድን ከ8 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ ባለቤት ነው። ሞንዲያሊቶ የሚባል የታዳጊዎች ውድድር አለ ፤ በዚህ ውድድር ክለቦችም ብሔራዊ ቡድኖችም ይሳተፋሉ፡፡ ማሊ በየዓመቱ ከ8፣ 10፤12 ዓመት በታች ትወዳደራለች፡፡ አየህ ሁሌም ተተኪ አለ ማለት ነው፡፡ ማሊ በአንድ ወቅት የኢትዮጵያ ዓይነት ችግር ገጥሟት ነበር ፤ ተተኪ የማፍራት፡፡ ከዛም እግር ኳሱን የሚመሩት ሰዎች ቁጭ ብለው መከሩ፡፡ እንደምታውቀው ማሊ ከ2015 ጀምሮ በዓለም የታዳጊዋች ሻምፒዮና ጥሩ ውጤት አላት፡፡ ይሄ ሁሉ ታዲያ የሥራ ውጤት ነው፡፡ ተተኪ ማፍራት የምርጫ ጉዳይ አይደለም። ግብ ጠባቂም ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡ የግብ ጠባቂ አሰልጣኞችም ታዳጊ ግብ ጠባቂዎችን ማፍራት አለባቸው፡፡ ታዳጊዎች ዘመናዊ ስልጠና ያስፈልጋቸዋል፡፡ ለበረኛ የሚያስቸግር ጥሩ አጥቂ ስለነበርክ የግብ ጠባቂ አሰልጣኝ መሆን አትችልም። በረኛ ስለነበርክም ብቻ የበረኛ አሰልጣኝ መሆን አትችልም፡፡ የግብ ጠባቂ አሰልጣኝነት ትልቅ ሙያ ነው። የተለየ ስልጠና የሚጠይቅ ትልቅ ሙያ፡፡
እስካሁን በተቃራኒ ከገጠምካቸው አጥቂዎች ማን ይበልጥ አስቸግሮሃል?
ብዙ አጥቂዎች አሉ ፤ እኔ ማንንም አልፈራም፡፡ ሁሉም የተለየ የራሱ ብቃት አለው ፤ ነገር ግን ከጠየቅከኝ አይቀር የቅዱስ ጊዮርጊሱ 19 ቁጥር (አዳነ ግርማ) የተሟላ አጥቂ ነው፡፡ የሚገርመው ነገር በደርሶ መልስ በሁለቱም ሜዳ ግብ አስቆጥሮብኛል፡፡ ለኔ አዳነ ጥሩ አጥቂ ነው፡፡
የፋሲል ጠንካራ እና ደካማ ጎን ምንድን ነው?
የፋሲል ጥንካሬ የተከላካይ ክፍሉ ይመስለኛል፡፡ እውነት ለመናገር ከፊቴ የነበሩት ተከላካዮች ተጋዳይ ነበሩ። የመጀመሪያ ዓመት ሥራዬን ቀላል ያረጉልኝ እነሱ ናቸው፡፡ ድክመታችን ደግሞ አዲስ ክለብ መሆናችን ይመስለኛል፡፡ ዓመቱ መጀመሪያ ላይ ክለቡን የተቀላቀልን እኔን ጨምሮ ብዙ ተጫዋቾች ነበርን፤ ይህ ደግሞ ብቻውን ውድድሩን ከባድ ያደርግብሃል፡፡ አብረን ለመስራትና ለመግባባት ጊዜ ፈጅቶብናል፡፡ ክለባችንንም ካየኸው የሆነው ይሄ ነው። ዕለት ዕለት እየተሻሻልን ነበር የመጣነው፡፡
አሁን ከሦስተኛ አሰልጣኝ ጋር ልትሰራ ነው የአሰልጣኝ መቀያየር በአንተ ላይ ያለው ተጽእኖ ምንድን ነው?
እኔ የፋሲል ግብ ጠባቂ ነኝ። የፈረምኩትም የምጫወተውም ለፋሲል ማሊያ ነው፡፡ ለአሰልጣኝ አይደለም፡፡ ማንም ቢያሰለጥን ለኔ ያው ነው፡፡ ግብ ጠባቂነት ሙያዬ ነው ፤ ለየትኛውም አሰልጣኝ ቢሆን ግዴታዬ ግብ መጠበቅ ነው ፤ አለቀ፡፡ አሰልጣኝ ሊመጣና ሊሄድ ይችላል። ሁሌም ታማኝ መሆን ያለብን ለማሊያና ለሙያችን ብቻ ነው፡፡ አሁን ሦስተኛ አሰልጣኝ ጋር ልሰራ ነው ማለት ነው፡፡ ሁሉም አሰልጣኝ የራሱ ብቃትና ስትራቴጂ አለው፡፡ ያንን መተግበር ደግሞ የኛ ግዴታ ነው፡፡ የአሰልጣኝ መቀያየር እንደ ቡድን እንጂ እኔ ላይ በተለይ የሚያመጣው ምንም ለውጥ የለም፡፡
በታሪካዊቷ የጎንደር ከተማ ያለህን ጊዜ እንዴት ትገልፀዋለህ?
ጎንደር በጣም ታሪካዊ ሃገር መሆኗን ነው የተረዳሁት፡፡ ሕዝቡ በጣም እንግዳ ተቀባይ፣ ሰው አክባሪ የሆነባት የፍቅር ከተማ ነች፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ከመጣሁበት ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ እንደልጃቸው ነው ሲያዩኝ የነበረው። በጣም የሚወደድ ሕዝብ ነው፡፡ ለዚህ ሕዝብ እኛ ሰጠነው ምላሽ በጣም ትንሽ ነው ፤ ከሻምፒዮንነት በላይ የሚገባው ደጋፊ ነው፡፡ ለዚህ ሕዝብ ያለኝን ሁሉ መስጠት እፈልጋለው፡፡
ስለፋሲል ደጋፊዎች?
ደጋፊው በጣም ያምራል። ለዚህ ደጋፊ ምን ልታደርግለት ትችላለህ ? ስንሸነፍም ፣ ስናሸንፍም በየክልሉ እየተጓዘ ደግፎናል፡፡ እንዳልኩህ ደጋፊው የሰጠንን ያህል መመለስ አልቻልንም፡፡ የደጋፊው ዕዳ አለብን። በመጪው ዓመት የቻልነውን ሁሉ አድርገን ይህን ደጋፊ ማስደሰት ይጠበቅብናል፡፡
በየስታዲየሙ ስለሚስተዋሉ ብጥብጦች….
በእግር ኳስ ሜዳ ላይ መታየት የማይመጥን ነገር ነው እያየን ያለነው፡፡ ይህ የእግር ኳስ ባህሪው አይደለም፡፡ ኳስ ትጫወታለህ፣ ታሸንፋለህ ፣ ትሸነፋለህ ወይ ደግሞ አቻ ትወጣለህ ፤ የትኛውንም ውጤት በጸጋ መቀበል ለማሻሻል መሥራት ነው። አለቀ ! ይህ ነው የእግር ኳስ ባህሪ፡፡ የብራዚል ብሔራዊ ቡድን በጀርመን በሜዳው ባዘጋጀው የዓለም ዋንጫ 7-1 ሲሻነፍ የብራዚል ሕዝብ ጀርመኖችን እንግደል አላሉም፡፡ ኳስ እንደዚህ ናት ዛሬ ትሸነፋለህ ነገ ደግሞ ታሸንፋለህ፡፡ ባርሴሎና ማድሪድ ሜዳ ላይ ያሸንፋል ሜዳው ላይ ደግሞ ሊሸነፍ ይችላል ምክንያቱም እግር ኳስ ነው፡፡ በእግር ኳስ ሁሌ ማሸነፍ ወይም ሁሌ መሸነፍ የለም፡፡
በመጨረሻ የምታስተላልፈው መልዕክት ካለህ…
የጎንደርን ሕዝብና ፣ የፋሲልን ደጋፊ በሙሉ አመሰግናለው፡፡ የቡድን ጓደኞቼን ፣ የፋሲልን ቤተሰብ በጣም አመሰግናለው፡፡ ሶከር ኢትዮጵያንም ለሰጣችሁኝ ጊዜ በጣም አመሰግናለው፡፡