በአዳማ የቡድን ስብስብ ውስጥ የሚቀጥሉ ተጨዋቾች ሲታወቁ ከወጣት ቡድን የማደግ ዕድል የሚሰጣቸውም እንደሚኖሩ ታውቋል።
ከአሰልጣኝ ተገኔ ነጋሽ ስንብት በኋላ አሰልጣኝ ሲሳይ አብርሀምን እና ዳዊት ታደሰን ወደ ኃላፊነት ያመጣው አዳማ ከተማ በዝውውር መስኮቱ በመጠኑ በመሳተፍ አምስት ተጨዋቾችን ማስፈረሙ ይታወሳል። ባሳለፍነው የውድድር አመት ጥሩ እግር ኳስን የሚጫወት እና በወጣቶች የተገነባ ቡድንን ያሳየው አዳማ ምንም እንኳን ሙጂብ ቃሲም እና ሱራፌል ዳኛቸው የመሳሰሉ ተጫዋቾችን ቢያጣም የተወሰኑት ተጨዋቾቹን ደግሞ አብረውት እንዲቀጥሉ አድርጓል።
በዚህም መሰረት ተከላካዩ ሱለይማን ሰሚድ እንዲሁም የፊት አጥቂዎቹ ዳዋ ሁቴሳ እና ቡልቻ ሹራ ለሁለት የውድድር አመታት በአዳማ እንደሚቆዩ ሲታወቅ የረጅም ጊዜ ልምድ ባለቤቶቹ ሱለይማን መሀመድ እና አዲስ ህንፃ ደግሞ የ2011 የውድድር ዓመትን በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታድየም እንመለከታቸዋለን። ከዚህ በተጨማሪም አዳማ ከተማ በሃያ ዓመት በታች ቡድኑ ውስጥ ላሉ ስድስት ተጨዋቾቹ ወደ ዋናው ቡድን የማደግ የሙከራ ዕድል የሚሰጥ ሲሆን ከሙከራው በኃላ ሦስቱ ተጨዋቾች የዕድሉ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ይጠበቃል።