በታንዛንያ አስተናጋጅነት እየተካሄደ የሚገኘው የአፍሪካ ከ17 ዓመት በታች ዋንጫ የሴካፋ ዞን ውድድር የምድብ ጨዋታዎች ዛሬ ሲጠናቀቁ ኢትዮጵያ በቀዳሚነት ምድቡን በማጠናቀቅ ወደ ግማሽ ፍፃሜ ማለፍ ችላለች።
ዛሬ በተመሳሳይ ሰዓት በቻማዚ እና ዳሬ ሰላም ስታድየሞች በተደረጉ ጨዋታዎች ኢትዮጵያ ኬንያን 4-2 በሆነ ውጤት በማሸፍ በ100% ድል ምድቡን በበላይነት አጠናቃለች። ከአፍሮ ፅዮን የተገኘው በየነ ባንጃ ሦስት ጎሎች አስቆጥሮ ሐት-ትሪክ ሲሰራ ባለፉት ሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች ግብ ያስቆጠረው ምንተስኖት እንድርያስ ቀሪዋን አንድ ጎል አስቆጥሯል። ውጤቱን ተከትሎም ኢትዮጵያ ከ4 ጨዋታ ሙሉ 12 ነጥቦችን በመሰብሰብ በቀዳሚነት ወደ ግማሽ ፍፃሜ ተሻግራለች። በተመሳሳይ ሰዓት ጅቡቲን ገጥማ 8-0 ያሸነፈችው ዩጋንዳ ደግሞ በ9 ነጥቦች ቀይ ቀበሮዎቹን ተከትለው ወደ ግማሽ ፍፃሜ መግባት ችለዋል።
የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታዎቹ ቅዳሜ በዳሬ ሰላም ናሽናል ስታድየም ሲከናወኑ ኢትዮጵያ ከሩዋንዳ፣ ዩጋንዳ ከአስተናጋጇ ጋር የሚጫወቱ ይሆናል።
ከጨዋታው በኋላ የብሔራዊ ቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ተመስገን ዳና ለሶከር ኢትዮጵያ አስተያየቱን ሰጥቷል:-
ስለ ጨዋታው
የመጀመርያው 45 ላይ ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ ነበር ያደረግነው። በሁለተኛው ግን የተሻልን ነበርን። ኬንያዎች በመከላከል ላይ ጠንካራ ቢሆኑም ወደ ግማሽ ፍፃሜ ለማለፍ ጨዋታውን የግድ ለማሸነፍ የማጥቃት እንቅስቃሴ እንደሚመርጡ ስለተረዳን ለማጥቃት ከግብ ክልላቸው ነቅለው በሚወጡበት ጊዜ ሰፊ ክፍተቶችን ለመጠቀም ተነጋግረን ነበር የገባነው። ያሰብነውንም በሚገባ ተግብረን አሸንፈን ወጥተናል።
ወደ ግማሽ ፍፃሜ ስለማለፍ
ወደ ግማሽ ፍፃሜ ማለፋችን ያስደስታል። ምድቡን በአንደኝነት ማጠናቀቃችን ብቻ ሳይሆን እያንዳንዱን ጨዋታ ማሸነፋችን እና በየእለቱ እንደ ቡድን እድገት እያሳየን መምጣታችን ይበልጥ ያስደስታል።
ስለ ግብ አስቆጣሪዎቹ ተጫዋቾች
ሁለቱም ልጆች (በየነ እና ምንተስኖት) ጥሩ እንቅስቃሴ እያሳዩ ነው። ነገር ግን በግል የተለየ ተዓምር እየሰሩ ሳይሆን የቡድን ስራው ነፀብራቅ ናቸው። አጥቂ እንደመሆናቸው እንደ ቡድን የተሰራውን ስራ ነው የሚጨርሱት። እንደ አጠቃላይ ስትመለከት ልጆቹ ላይ የተለየ አቅም እንዳለ ይታያል። ግብ ጠባቂው አላዛርም ተስፋ የሚጣልበት እንደሆነ እየታየ ነው።
ስለ ቀጣይ ጨዋታ
ከሩዋንዳ ጋር ለሚደረገው የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ እንደ ሌሎች ጨዋታዎች ሁሉ ተዘጋጅተን እንገባለን። ድክመት እና ጥንካሬያቸውን ስለምናውቅ አሸንፈን እንደምናልፍ አምናለሁ።
ፎቶ – @tanfootball