ባሳለፍነው የውድድር ዓመት አጋማሽ ላይ ነው ወደ ኢትዮጵያ የመጡት፡፡ ለኢትዮጵያ አዲስ ይሁኑ እንጂ ለአፍሪካ እግር ኳስ ግን አዲስ አልነበሩም፤ በሩዋንዳ፣ ካሜሩን እና አልጀሪያ አሰልጥነው ውጤታማነታቸውን አስመስክረዋል፤ የኢትዮጵያ ቡናው አሰልጣኝ ዲዲዬ ዳሮሳ ጎሜስ፡፡ ለእረፍት ከሄዱባት ሃገራቸው ፈረንሳይ እንደተመለሱ ለመጀመሪያ ጊዜ ከሶከር ኢትዮጵያ ፈረንሳይኛ ቋንቋ አዘጋጅ ተሾመ ፋንታሁን ጋር ተቀምጠው አውርተዋል፤ በቃለምልልሱም ስለቡድናቸው፣ ቡናን ስለለቀቁ ነባር ተጫዋቾች፣ ስለአዲሱ ቡድናቸውና ስለመጪው ዓመት ዕቅዳቸው በሰፊው ነግረውናል፤ መልካም ቆይታ፡፡
እንኳን በሰላም ተመለሱ፡፡ ዕረፍት እንዴት አለፈ ?
ዕረፍት በጣም ጥሩ ነበር፡፡ በርግጥ ሥራም ይበዛብኝ ነበር፡፡ ፈረንሳይ ውስጥ ወደሚገኙ ፕሮፌሽናል ክለቦች እየሄድኩ የቅድመ ውድድር ዝግጅት እመለከት ነበር፤ ከናፈቁኝ ቤተሰቦቼ ጋር ጊዜ ማሳለፍ ይጠበቅብኝ ነበር፡፡ እውነት ለመናገር በጣም የተማርኩበት የእረፍት ወቅት ነበር፡፡ እንደምታውቀው እግር ኳስ በየጊዜው ያድጋል፣ ይቀየራል፡፡ በቴክኒክ ብትል በታክቲክ ብዙ ነገር እየተቀያየረ ነው ስለዚህ ከዘመን ጋር አብሮ ማደግ፣ መቀየር ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ የዘመኑ ፋሽን በፈጣን የመልሶ ማጥቃት መጫወት ነው፡፡ ይህን ደግሞ እንዳለ አምጥተህ ቡና ውስጥ ልትተገብር አትችልም ምክንያቱም የቡና ደጋፊ ሙሉ ጨዋታውን ኳስ ይዘህ ተጫውተህ እንድታሸንፍ ነው የሚፈልገው፡፡ ስለዚህ ሳይንሱን ከደጋፊው ፍላጎት ጋር ለማስታረቅ ብዙ ማሰብ፣ መማርና መዘጋጀት ነበረብኝ፡፡ ወደድክም ጠላህም ሁሌም ከዘመን ጋር አብሮ ማደግ ያስፈልጋል፡፡
ቡና ዘንድሮ ብዙ ተጫዋቾችን በተለይ ደግሞ ነባሮቹን የለቀቀበት ምክንያቱ ምን ይሆን ?
ምንም የተለየ ነገር የለውም፡፡ ኮንትራታቸው ያለቀ ቡና ኮንትራቸውን የማያራዝምላቸው ተጫዋቾች ነበሩ፣ ሌሎች ኮንትራታቸው አልቆ ከቡና ጋር መቀጠል ያልፈለጉ ነበሩ፣ ሌሎች ደግሞ ኮንትራታቸው ሳያልቅ የቡና የመጪው ዓመት ዕቅድ ያልሆኑ ተጫዋቾችም ነበሩ፡፡ የምነግርህ ነገር ሁሉም ተጫዋቾች የለቀቁት ቡና የሚጠብቅባቸውን ማድረግ ባለመቻላቸው ነው፡፡ ለምሳሌ ሮቤል እና ትዕግስቱን ብታይ በዓመቱ እጅግ በጣም ጥቂት ጨዋታ ብቻ ያደረጉ ናቸው፡፡ ኤልያስና አስቻለውን ደግሞ ብትወስድ በቀደሙት ዓመታት ከነበራቸው ብቃት እጅግ እጅግ ወርደው ነው ያገኘኋቸው፡፡ ከሰማውት አንጻር ከነሱ በጣም ብዙ ጠብቄ ነበር፤ በኣካል ብቃት ከጠበኩት በታች ወርደው ነው ያገኘኋቸው፡፡ አክሊሉ ኮንትራቱ አልቋል። ነገር ግን ከቡና ይልቅ ጅማን መርጦ ሄዷል፤ ውሳኔውን እናከብራለን፡፡ እኔ እንዳሰልጣኝ መወሰን ነበረብኝ ስለዚህ ለቡና የሚጠቅመውን ነው የወሰንኩት፡፡ ወደፊትህን በታሪክ አትገነባም (You cannot build the future with the past) ቡና ወደፊት መራመድ አለበት፡፡ የሚቆጨኝ የመስዑድ ብቻ ነው፡፡ እሱ የተለየ ሰው ነው፡፡ ቢቆይ በጣም ደስ ይለኝ ነበር፡፡ እምነት የምትጥልበት ሰው ነው፡፡ የመጀመሪያ ረዳት አሰልጣኝ እንዲሆን ጠይቄው ነበር፡፡ ምክንያቱም መስዑድ ከማንም የተሻለ አሰልጣኝ መሆን እንደሚችል አምናለው፡፡
መስዑድ ከጎሜስ ምን ዓይነት ጥንድ መሆን እንደሚችል እስቲ አስበው ፤ ነገር ግን አልሆነም መስዑድ ለራሱ ምርጥ የሚለውን ውሳኔ ወስኗል ፤ አንድ ወይም ሁለት ወይም ከዚያ በላይ ዓመታት መጫወት ይፈልጋል፤ ውሳኔውን አከብራለው፡፡ አንድ ቀን ግን ወደቡና ቤት ተመልሶ እንደሚመጣ እርግጠኛ ነኝ፡፡ መስዑድ ለቡና ትልቅ ምልክት ነው፡፡ የቡና አርማ ነው፡፡ አብሮኝ ቢሰራ በጣም ደስተኛ ነበርኩ ነገር ግን አልሆነም፡፡ ምናልባት ይህን ቃለ-ምልልስ ካነበበው ትንሽ ቅር ያለኝ፤ መስዑድ ውሳኔውን ሳያሳውቀኝ በመሄዱ ነው፡፡ ደውሎ ወይ ቴክስት አርጎ ኮች ልሄድ ነው ቢለኝ በጣም ደስ ይለኝ ነበር፡፡ አንድ ቀን ግን ተመልሶ እንደምንገናኝ ተስፋ አለኝ፡፡
መስዑድ ይህን ያህል ያስፈልጎት ከነበረ በተጫዋችነት ለመያዝ አልሞከሩም?
እውነት ለመናገር ከሁለተኛው ዙር በኋላ የመስዑድ ብቃት ቡና እንደሚፈልገው አልነበረም፡፡ ከመጋቢት በኋላ መስዑድ በሜዳ ላይ በፊት የነበረውን ተጽዕኖ መፍጠር አልቻለም፡፡ በፊት እርሱ ወደሜዳ ሲገባ አንድ ነገር እንደሚፈጥር ሁሉም ያውቃል ፤ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ግን ይህ ነገር ሜዳ ላይ አልነበረም፡፡ የእርሱን ተጽእኖ ሜዳ ላይ ሳጣው አንደኛ ረዳት አሰልጣኝ እንዲሆን ጠይቄው ነበር፡፡ መስዑድ ሁሌም መጫወት ይፈልጋል፡፡ ታላቅ ሰው ነው ፣ የቡና ታሪካዊ ተጫዋች ነው ፤ ሁሌም ቡና በልቡ ውስጥ አለ፡፡ እኔን በብዙ ረዳኝ ታላቅ ተጫዋች ነው፡፡ ለመስዑድ ሁሌም የተለየ ክብር አለኝ፤ የቡና ቤት ሁሌም ለመሱድ በሩ ክፍት ነው፡፡ በሄደበት ሁሉ መልካሙን እመኝለታለው፡፡ አንድ ቀን ተመልሶ አብረን እንደምንሰራ ሙሉ እምነት አለኝ፡፡
ኤልያስስ ?
የኤልያስ ብቃት ለኔ ለራሴ አልገባኝም፡፡ በሁለቱ ዙሮች መሃል እረፍት ላይ ኤልያስን ጠርቼ ኤልያስ ክብደትህንና ሰውነትህን ልብ በለው ብዬ አስጠንቅቄው ነበር፡፡ ከኤልያስ ጋር ምንም ሌላ ችግር የለብኝም ፤ አእምሮው ፣ የማሸነፍ መንፈሱ ሁሌም ጥሩ ነው። ነገር ግን የሜዳ ላይ ብቃቱና አካል ብቃቱ ከዕለት ዕለት እየወረደ ነበር፡፡ ኤልያስን ልረዳው ሞክሬያለው፡፡ ሁሌም በቡድኔ ውስጥ እይዘው ነበር፡፡ ነገር ግን ኤልያስ ላይ ያን ያህል የተለየ መሻሻል አላየሁም ፤ መወሰን ነበረብኝ፡፡ ለዚህም አይደል እንዴ እነሚኪን ፣ አቡበከርን በቡድኑ ውስጥ የያዝነው፡፡ ሁሌም ቢሆን ታዳጊዎችን ከታች ወደዋናው ቡድን ስታሳድግ ትልልቆችን በዛው መጠን ከዋናው ቡድን መቀነስ ይጠበቅብሃል፡፡ ቡና ከኤልያስ ጋር የተለያየው የኤልያስ ብቃት እየወረደ ስለመጣ ብቻ ነው፡፡ ከኤልያስ ጋር በግል ምንም ችግር የለብኝም፡፡ መልካም ግንኙነት አለን፡፡ ኤልያስ ለቡና ታላቅ ታሪክ የሠራ ቁልፍ ተጫዋች ነው፡፡ ትንሽ በኤልያስ ያዘንኩት በቅርቡ ቡናን፣ ፕሬዝዳንቱንና ቦርዱን በሚመለከት በሰጠው አስተያየት ነው፡፡ ይሄ ኤልያስን አይመጥንም፡፡ ሰባት ዓመታትን ካሳለፍክበት ቤት ስትለቅ በሰላም በክብር አመሰግናለው ብለህ ሲሆን ደስ ይላል፡፡
ቡና ኤሊያስ ለቡነኑ ላደረገው ነገር ሁሉ አመስግኖታል…
ደሞዝ እየከፈለ አራት፣ አምስት ዓመታትን ያሳለፍክበትን ቤት ስትለቅ በዚህ መልኩ አስተያየት መልካም አይደለም፡፡ ምናልባት ከስሜታዊነት የመነጨ ሊሆን ይችል ይሆናል፤ ነገርግን ለኤልያስ ልነግረው የምፈልገው ቡና መቼም ቢሆን አይረሳህም፤ አንተ ለቡና ታላቅ ታሪክ የሰራህ ትልቅ ተጫዋች ነበርክ ስለዚህ ለቡና ታማኝ ሆነህ መኖር አለብህ ነው፡፡
ግብ ጠባቂው ሃሪስተንስ?
ከሃሪስተን ጋር ኮንትራታችን ማራዘም እንችል ነበር፡፡ ሃሪስተን አራት ዓመታትን በቡና አሳልፏል ፤ የመጀመሪያውን ዓመት በጣም ጥሩ የነበረ ይመስለኛል፣ ሁለተኛውን ዓመት ጥሩ ነበር፣ ስሦተኛውንም ደህና ነበር ይህን ዓመት ግን በፍጹም ጥሩ አልነበረም፡፡ የመጀመሪያው ዓመት ሃሪስተን ቢሆን ኖሮ የነበረን ዘንድሮ ዋንጫ እንበላ ነበር፡፡ ሃሪስተን ጥሩ ባልነበረበት ሁሉ ጊዜ ከጎኑ የነበርኩት እኔ ነበርኩ፡፡ በፍጹም ሜዳ ሊያዩት የማይፈልጉ ብዙ ሰዎች ነበሩ፤ በዛ ሁሉ ወቅት እኔ ከጎኑ ነበርኩ፡፡ ብዙ ልረዳው ሞክሬያለው፤ ወደ ብቃቱ እንዲመለስ ብዙ ጥሬያለው ነገር ግን ከዕለት ዕለት እየወረደ ነው የሄደው፡፡ ብዙ ጨዋታዎች ላይ በሱ ምክንያት ነጥብ ጥለናል፡፡ ይህም ሁሉ ሆኖ ግን በቡድኑ ውስጥ እንደሚቀጥል ነበር የማስበው ሆኖም ግን በእኔና በሱ መካከል አለመግባባት ተፈጠረ፡፡ ለኔ ክብር አልነበረውም አሰልጣኙን ማክበር ነበረበት፡፡ የቡናን አሰልጣኝ ሳያከብር ሲቀር የናቀው አሰልጣኙን ብቻ ሳይሆን የቡናን ቤተሰብ በሙሉ ነው፡፡ ማንም ቢሆን ከቡና በላይ ሊሆን አይችልም፤ አሰልጣኑም ቢሆን ተጫዋቹ ሁሉም ከቡና በላይ ሊሆን አይችልም፡፡ እኔና ሃሪስተን አንድ ቡድን ውስጥ አብረን ልንሰራ አንችልም ስለዚህ መለያየት ግድ ነው፡፡ ቡና በፍጥነት ከሱ ጋር ያለውን ነገር ያጠናቅቃል። በመጀመሪያዎቹ ሁለት ዓመታት ለሰራው ነገር ሁሉ ቡና ሁሌም ያመሰግነዋል፡፡ ቅድም እንዳልኩህ መጪውን ጊዜ በታሪክ ላይ ልንገነባ አንችልም፡፡ በርግጠኝነት ከሱ የተሻለ ወጣት ግብ ጠባቂ ይመጣል፡፡ እኔ ሁሌም ቢሆን ከወጣቶች ጋር መስራት ነው እምፈልገው፤ በቃ ይሄ ነው፡፡
የወጡትን ያህል አዳዲስ ተጫዋቾች ይመጣሉ ማለት ነው?
የወጡትን ያህል ስለመምጣታቸው እርግጠኛ አይደለሁም። ነገር ግን ከአስር የማያንሱ አዳዲስ ተጫዋቾች እንደሚያስፈልጉን እርግጠኛ ነኝ፡፡ በባለፈው ዓመት መጀመሪያ የዝውውር ወቅት ብዙ ስሕተቶችን ሰርተናል፡፡ እነዚህን ስህተቶች ላለመድገም ከሁለት ወራት በላይ ከክለቡ ፕሬዝዳንት ጋር በሚስጥር ስንሰራ ቆይተናል፡፡ የብዙ ተጫዋቾችን ፕሮፋይል ስናስተውል ነው የቆየነው፡፡ ስለዚህ የአምናውን ስህተት በፍጹም አንደግምም፡፡ ለምሳሌ አንድም ጨዋታ ያላደረጉ ልጆች ዓመቱን ሙሉ በክለብ ይዘን ደሞዝ ስንከፍል ቆይተናል፡፡ አንድ ተጫዋች በመጣበት ዓመት አንድም ጨዋታ ካላረገ ምልመላው ችግር ነበረበት ማለት ነው፡፡ ምልመላ ላይ ያለውን ስጋት መቀነስ ነው የዘንድሮ ዋና ዓላማችን፡፡
የተጫዋች ምልመላን መቶ በመቶ ከስጋት ነጻ ልታረገው አትችልም ነገር ግን ደግሞ እነደአምና ብዙ ስህተትም አንጠብቅም፡፡ የአምናው ምልመላ 40% ውጤታማ ነበር፡፡ እንደ ቶማስ አይነት ጥሩ ጥሩ ልጆች እንዳገኘንበት መካድ አልችልም፡፡ ዘንድሮ ደግሞ ወደ 80% ማድረስ ከቻልን ግባችንን አሳካን ማለት ነው፡፡
ወጣት ተጫዋቾች አሉን ዘንድሮ ከነሱ ብዙ ነገር እጠብቃለው፡፡ እነሱ ላይ መተማመን አንድ ነገር ነው። እነሱን ደግሞ ከታላቅ ተጫዋቾች ጋር ማጣመር ያስፈልጋል፡፡ ዕድሜው ከ25 ዓመት በላይ የሆነው ተጫዋች ብዙም አልፈልግም፡፡ በጣም ወጣት ቡድን ነው ይዤ መቅረብ የምፈልገው ፤ ከፕሬዝዳንታችን ጋር እየሰራን ያለነውም ለዚህ ነው፡፡ በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ የፈረንሳይ ቡድን በአማካይ የውድድሩን በጣም ወጣት ቡድን ይዛ የዓለም ዋናጫ ባለቤት ስትሆን አይተናል፡፡ የአሁን ብቻ ሳይሆን የወደፊት አሸናፊ ቡድን ነው መገንባት የምንፈልገው፡፡
ስንት አዳዲስ ተጫዋቾች እንጠብቅ?
አንድ ላይ ከአስር የማያንሱ አዳዲስ ልጆች በቅርቡ ዝውውራቸው ይጠናቀቃል፡፡ ከ20 ዓመትና ከ17 ዓመት በታችም የሚጠበቁ ይኖራሉ፡፡ አምና ሚኪና አቡበከር የሰሩትን ተመልክተናል፡፡ ኃይሌና አዲስን የመሰሉ ብሩህ ተስፋ ያላቸው ታዳጊ ልጆችንም አይተናል፡፡ በነሱ ላይ እምነት መጣል ያስፈልጋል፡፡ ዘንድሮም ደግሞ ሌሎች ታዳጊዎች ተመሳሳይ ነገር ያሳዩናል ብለን እንጠብቃለን፡፡ ከብዙ ወራት ጀምሮ አብረውን ልምምድ እየሰሩ ያሉ ብዙ ታዳጊዎች አሉ፡፡ ዘንድሮም ሶስት አዳዲስ ልጆች ይቀላቀሉናል እነዚህ ልጆች ከዋናው ቡድን ጋር ለወራት ሲሰሩ የነበሩ ናቸው፤ እርግጠኛ ነኝ እነሱም እንደነሚኪና አቡባከር አዳዲስ ነገር የመስራት አቅም ያላቸው ናቸው፡፡ በርግጥ ልምድ ያላቸው ታላላቅ ተጫዋቾችም ያስፈልጉናል፡፡ ለደጋፊዎቻችን ልነግራቸው የምፈልገው በዚህ ሳምንት ቡድናችንን የሚቀላቀሉ ታላላቅ ተጫዋቾች ይኖሩናል፡፡ ከፍ ያለ ፕሮፋይል ያላቸው ተጫዋቾች ናቸው፡፡ ለሃገራቸው ብሔራዊ ቡድን በመጫወት ላይ ያሉ፡፡ ከእነዚህ ተጫዋቾች ጋር ለወራት ስንነጋገር ነበር፡፡ በመጨረሻ ተስማምተናል፡፡ የወረቀትና የቪዛ ጉዳያቸውን እንደጨረስን ይገባሉ፡፡ እርግጠኛ ነኝ ደጋፊዎቻችን በጣም የሚደሰቱቸው ወጣት ግን ታላቅ ተጫዋቾች ናቸው፡፡ ደጋፊዎቻችንን አታስቡ አትጨነቁ የሚመጡት 23-24 ዓመት ልጆች ናቸው ነገር ግን ደረጃቸው ከፍ ያለ የብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች ናቸው በተለይ የነሚኪያስ እና ለነአቡበከር እድገት ሊያፋጥኑ ሊያስተምሩ የሚችሉ ናቸው ለማለት እፈልጋልው፡፡ በቡና እቅድ ተስማምተው ወደዚህ ለመምጣት ስለፈቀዱ አመሰግናቸዋለው፡፡
አምና በተለይ መጀመሪያው ዙር ላይ ነበረው ስብስብ ጥሩ እንዳልነበረ ይታወቃል፡፡ አሰልጣኝ ፓፒች ተስፋ ቆርጦ እንዲሄድ ያደረገ ነበር ፤ ዘንድሮ በርግጥ የተሻለ ስብስብ ይኖረዋል?
ይሄን በጣም እርግጠኛ ነኝ ከአምናው በጣም የተሻለ የቡድን ስብስብ ይኖረናል፡፡ ደጋፊውን በዚህ በጣም እርግጠኛ ሁኑ በልልኝ፡፡ በጣም የተሻለ ስብስብ ነው የሚኖረን፡፡ የምንፈልገው አጨዋወት አለ፡፡ የቡና ታሪካዊ አጨዋወት፤ ይህን ጨዋታ በማሸነፍ መንፈስ መገንባት ያስፈልጋል፤ ለዚህ የጨዋታ ዕቅድ የሚሆኑ ልጆችን መመልመል ያስፈልጋል፡፡ እኔ በባህሪዬ በጣም መሸነፍ አልወድም። አግሬሲቭ ነኝ። ይህ ባህሪ ወደ ልጆቹ እንዲጋባ እፈልጋለው፡፡ ሁለት ሶስት ወራት አብረን ስንሰራ በተለይ ታዳጊዎችን ወደዋናው ቡድን እያሳደግን እየተካን አሸናፊ ቡድን ይኖረናል፡፡
አምና ጥሩ ጥሩ ውሳኔዎች ወስነናል። ለምሳሌ አማኑኤልን ከተከላካይ ወደ አጥቂ አማካይነት ፤ ኃይሌን በቀኝ ኮሪደር፣ ኢያሱን በግራ ኮሪደር በነገራችን ላይ ኢያሱ በጣም የሚገርመኝ ተጫዋች ነው ፤ ታጋይ ሁሌም ቡና በልቡ ውስጥ ለ በፍጹም መሸነፍን የማይቀበል የትም ቦታ ልታጫውተው የምትችል የሚገርም ልጅ ነው፣ ሚኪን በግራ በኩል ለማጫወት አቡበከርን በቀኝ ንታምቢን በተከላካይ እንዲጫወቱ ያደረግንበት ሁሉ ውሳኔዎች በጣም ጥሩ ጥሩ ውሳኔዎች እንደሆኑ አይተናል ፤ ዘንድሮም የተሻለ ቡድን ይኖረናል፡፡ ምርጥ አጨዋወት አለን ቡና የሚታወቅበት ለዚህ ጨዋታ የሚሆኑ ልጆች መልምለናል በቅርቡ ብዙ ሰርፕራይዝ ይኖረናል፡፡ ለዚህም ነው የቅድመ ውድድር ዝግጅታችንን ቀደም ብለን ነው የጀመርነው፤ ከባድ ልምምዶችን እናረጋለን ፤ አስቀድመን ጀምራናል፣ በዚህ ሳምንት የአካል ብቃት ልምዶችን እንሰራለን ከዛም ወደ ባህርዳር ሄደን እንዘጋጃለን ማለት ነው፡፡
ታዳጊዎችንስ በሚመለከትስ አዳዲስ ልጆች እንጠብቅ?
በዚህ ሁለት ሳምንታት ውስጥ 8 ልጆች ከ20 ዓመት በታች ለሙከራ እንዲመጡልኝ ጠይቄያለው፡፡ ከነዚህ ስምንት ልጆች ሁለት ሶስት ከኛጋ መቀጠላቸው አይቀርም፡፡ ሁሌም ታዳጊዎች ወደዋናው ቡድን ሲመጡ ወዲያው ታላቅ ተጫዋች አይሆኑም፤ ጊዜ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ አምና ኃይሌ ወደዋናው ቡድን ሲመጣ ብዙ ጥሩ ነገሮች ይዞ ቢመጣም የሚቀሩት ነገሮች ደሞ እንደዛው ብዙ ነበሩ፡፡ ስለዚህ ዕድል እየሰጠን፣ እየገራን፣ እያረምን እያስተካከልን ኃይሌ ዓመቱ መጨረሻ ላይ ምን ያህል የሚያስፈራ ልጅ እንደሆነ ተመልክተናል፡፡ ሌሎቹንም የነኃይሌን መንገድ እየተከተልን ማሳደጋችንን እንቀጥላለን፡፡ ሁሌም ታዳጊዎችን ስታሳድግ በጣም ጠንቃቃ መሆን አለብህ እኔ በጣም ጠንቃቃ ነኝ ደጋፊውም ሲያደንቅም ሲመክርም ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡ ከልጆቹ ጋር ከዝግጅት በፊት የመጀመሪያ ስብሰባ የማድረግ ባህል አለኝና በዚህ ወቅት ሚኪንና ኃይሌን አግኝቼ ምን መሆን ነው የምትፈልጉት ራዕያችሁ ምንድን ነው ብዬ ስጠይቃቸው ኮች አውሮፓ መጫወት ነው የምንፈልገው አሉኝ እኔም አውሮፓ መጫወት የማይቻል ነገር አይደለም ጠንክረን አብረን እንሰራለን መጀመሪያ ግን ከቡና ጋር ዋንጫ ማግኘት አለብን አልኳቸው፡፡ የልጆቹ ርዕይ በጣም ነው ደስ ያሰኘኝ። ምክንያቱም ዓለምዓቀፍ ተጫዋች መሆን የሚፈልጉ ከሆነ ጠንክረው የመስራት ፍላጎት ኣላቸው ማለት ነው፡፡ እውነት ለመናገር ልጆቹ የፈለጉበት የመድረስ አቅም አላቸው፡፡
አማኑኤል በዚህ ዓመት እጅግ የተለወጠ ተጫዋች ነው። አሁን እንደውም ብሔራዊ ቡድን ተጠርቶ ልምምድ ላይ ይገኛል።
አማኑኤል በዚህ ዓመት እጅግ የተለወጠ ተጫዋች ነው። አሁን እንደውም ብሔራዊ ቡድን ተጠርቶ ልምምድ ላይ ይገኛል። ስለአማኑኤል ምን የሚሉት ነገር አለ?
የአማኑኤልን ብሔራዊ ቡድን መጠራት ሰምቼ በጣም ደስ ብሎኛል። ነገርግን ብዙም አልገረመኝም፤ ምክንያቱም ሁሌም ከጨዋታ በፊት ወይ በኋላ ዘንድሮ ብሔራዊ ቡድን ካልጠሩህ ዕለው ነበር፡፡ ለዚህ ጠንካራ ሥራው ክፍያ ነው በርግጥም አማኑኤል ይገባዋል፡፡ አማኑኤል በጣም ታታሪ ነው፡፡ የዘንድሮው ቡና ውጤት በተለይ አማኑኤል ባይኖር የሚቻል አልነበረም፤ እምትነግረውን ይሰማሃል በጣም ብልህ ነው የሚሰራውን ያውቃል ከቡድን ጓደኞቹ ጋር ምን ማድረግ እንዳለበት ያውቃል እኔ ምን ማድረግ እንደምፈልግ ይገባዋል የኔ የጨዋታ ፍልስፍና እንደአማኑኤል የገባው የለም፡፡ አማኑኤል ታላቅ ተጫዋች ነው በመጪዎቹ ሦስት እና አራት ዓመታት ደግሞ አማኑኤል በጣም ታላቅ ተጫዋች የሚሆን ወጣት ነው፡፡
አሁን የቡድናችን አምበል ነው። ከዚህ የበለጠ እያደገ እየበሰለ ሲሄድ ምክንያቱም የተሰጠው ኃላፊነት ቀላል አይደለም መስዑድን ነው የተካው። አማኑኤል ታላቅ ሰው የመሆን ዕድል ያለው ልጅ ነው፡፡ ከአማኑኤል ጋር አያይዤ ስለኢያሱም መናገር እፈልጋለው፡፡ እያሱ በጣም የሚገርም ተጫዋች ነው፡፡ እያሱ ሁሉም ቦታ መጫወት የሚችል ተጫዋች ነው። በረኛ እንኳ ልታረገው የምትችል ተጫዋች ነው፡፡ እያሱ የወደፊቱ መስዑድ የመሆን አቅም አለው፡፡ እንደዚህ ዓይነት ተጫዋች በቡና ሁሌም እንደሚቆይ ተረድቻለው፡፡ እንደሰው በጣም ጥሩ ልጅ ነው። የምትነግረውን ይሰማል ታታሪ ነው በጣም እንግባባለን፡፡ አንድ ተጫዋች የሚያስፈልገው ነገር ሁሉ አለው፡፡ ዘንድሮ ለሰራው ነገር ሁሉ ላመሠግነው እወዳለው፡፡ አሁን የቡድኑ አምበል አማኑኤል ነው ነገር ግን ኢያሱ ምክትል ሆኖ ይቀጥላል ማለት ነው ሁለቱም ይገባቸዋል፤ መሱድን ጠይቄያለው ራሳቸው ልጆቹን ጠይቄያለው፤ ሁለቱም ለቡና ያላቸውን የሚሰጡ ናቸው ሁለቱን ይዘን ለመጪው ሻምፒዮና እንታገላለን፡፡
ስለአሰልጣኝ ቡድንዎ ምን ይላሉ?
የግብ ጠባቂ አሰልጣኛችን ውብሸት በብሔራዊ ቡድን ግዴታ ላይ ነው፤ ሁለት ሶስት ወራት ከክለብ ግዴታ እየራቅክ ክለቡን ማገልገል በጣም ከባድ ነው፡፡ በረኞቹ አሁን በዝግጅት ወቅት ልምምድ ማድረግ አለባቸው፡፡ ሜዳ ላይና ከሜዳ ውጭ የአሰልጣኝ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ያለአሰልጣኝ ደግሞ ታዳጊዎችን ማሰብ ከባድ ነው፡፡ የአሰልጣኝ ቡድኑን እንደገና ማዋቀር ያስፈልጋል፡፡ አሁን ያሉት ምክትል አሰልጣኞች ታዳጊዎችን በተገቢው እየረዱአቸው አይደለም፡፡ ቡና ከዚህ የተሻለ ብቃት ያለው የአሰልጣኝ ቡድን ያስፈልገዋል ለዛም ነው መስዑድን ፈልጌ የነበረው፡፡ አንድ ሰው አሰልጣኝ ለመሆን ሲወስን 24 ሰዓት 7 ቀን እንደሚሰራ ማወቅ አለበት፡፡ አሰልጣኝነት በፍጹም ከሌላ ኃላፊነት ጋር የሚሰራ ሥራ አይደለም፡፡ የአሰልጣኖችን እገዛ የሚፈልጉ ብዙ ታዳጊዎች በቡድኑ ውስጥ አሉ፡፡ ይሄ ሁሉ ስራ ደግሞ በአሁኑ የአሰልጣኝ ቡድን የሚሰራ አይደለም ስለዚህ አሁን ያለው የአሰልጣኝ ቡድን አይቀጥልም፡፡ አሁን ምልመላ ላይ ነን በቅርቡ እናገኛለን ብዬ አስባለው፡፡ የበረኛ አሰልጣኝ አግኝተናል በቶሎ ይቀላቀናል ብዬ አስባለው፡፡ ከዛ በተጨማሪ ከፍተኛ ፕሮፋይል ያላቸው የአካል ብቃት አሰልጣኝ በሁለት ሳምንታት ውስጥ ቡድናችንን ይቀላቀሉናል፡፡ የተሟላ የህክምና ቡድን አለን፡፡ የሥነምግብ ባለሙያ አናግረን ጨርሰናል። እሱም በቅርቡ ይቀላቀለናል፡፡ የቪዲዮ ተንታኝም እንዲሁ ጠይቀናል እሱም ይሟላል ብለን እንጠብቃለን፡፡
የንታምቢን ቦታ ቅየራና ስኬት እንዴት ይገልጹታል አሁን በቡድኑ ውስጥ የቀረ የውጭ ተጫዋች እሱ ብቻ ነው።
ንታምቢ መሃል ላይ ሲጫወት አንድም ቀን አሳምኖኝ አያውቅም ነበር። ነገር ግን አንድ ቀን ከደደቢት ጋር በነበረ ጫዋታ የኋላ ተከላካያችን በቀይ ካርድ ሲወጣ ንታምቢ ሜዳ ውስጥ ነበር። ወደቴክኒክ ስፍራው ቀርቦ “ኮች እኔ እኮ አዚህ ቦታ መጫወት እችላለው። ግዴለህም” ሲለኝ ሞክር አልኩት፡፡ የመጀመሪያው ቀን ያሳየኝ ብቃት በጣም የሚደንቅ ነው፡፡ በዘመናዊ እግር ኳስ የኋላ ተከላካዮች ኳስ የማደራጀት ኃላፊነትም አለባቸው፡፡ ንታምቢ አሁን ቡና ውስጥ ካሉ የኋላ ተከላካይ ሥፍራ ተጫዋቾች ዋናው ነው፡፡ ንታምቢ በተጨማሪ የተለየ የቴክኒክ ተሰጥዎ አለው ይህ ችሎታው ኳስን ለመሃል ክፍል ተጫዋቾች አንዳንዴም በረዥም ለአጥቂዎች በመወርወር ይበልጥ እንድናጠቃ ይረዳናል፡፡ ይህ ቦታ ለሱም በጣም የጠቀመው ይመስለኛል፡፡ አሁን ንታምቢ የኡጋንዳ ብሔራዊ ቡድን ላይ የሚያስጠራው ብቃት ላይ ነው ያለው፡፡ ቦታው ለሱም አዲስ ነው ነገር ግን የወደፊት ተከላካያችን መሆኑን ተስፋ ሰጥቶናል ባለፉት ሦስትና አራት ወራት በፊት ያላየንበትን ታታሪነት በልምምድ ቦታም እያየንበት ነው፤ ለሰራው ነገር እሱንም ማመስገን ግድ ይለናል፡፡
የመጀመርያ ተመራጭ ተከላካይ ንታምቢ ይሆናል ብለን እንጠብቅ?
አሁን አራት የመጨረሻ ተከላካይ ሥፍራ ተጫዋቾች አሉን፡፡ ምናልባት በሶሥት ተከላካይ የመጫወት ምርጫን ይሰጠናል፡፡ ሶሥት ተከላካይ ሁለት አማካይ በጣም ጠንካራ ቡድን ይሆናል፤ ንታምቢ፣ ቶማስ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም ቢሆን ሃገር ካሉ ምርጥ የተከላካይ ሥፍራ ተጫዋቾች አንዱ ነው፣ ቦልተና ሌላ ታጋይ የሚያረገውን የሚያውቅ ምርጥ ተከላካይ ከሱም ብዙ እንጠብቃለን፣ አሁን ደግሞ ካስትሮን ከአርባምንጭ አስፈርመናል፤ ከዛ በተጨማሪ በተመላላሽ ቦታ ያለብን ችግር አሁን ይቀረፋል፡፡ ተካልኝና አህመድ ረሺድን አምጥነተናል፣ ተቀያይረው በቀኝና በግራ መጫወት የሚችሉ ልጆችን እያናገርን ነው፣ ኃይሌ አለ እያሱና አስራት ሁለቱም ቦታ መጫወት ይችላሉ፤ እነዚህን ሁሉ ስታይ የውድድሩ ምርጥ ተከላካይ እኛጋ እንዳለ ትረዳለህ፡፡
ለኔ ኃይሌ በቦታው ምርጥ ተጫዋች ነው፡፡ አዳዲሶቹ ተካልኝና አህመድ ረሺድ ከኃይሌና ከ አስራት የመጀመሪያ ተመራጭነትን ለመውሰድ ቀላል ፉክክር አይጠብቃቸውም፡፡ እያንዳንዱ ተጫዋች ቦታውን ለማስከበር ጠንክሮ መስራት ይጠበቅበታል፡፡ ዋናው ነገር ቡና ከአምናው በጣም የተሻለ የተከላካይ ክፍል ይኖረዋል፡፡ በክንፍ ለማጥቃም የተሻለ አማራጭ አለን አሁን ምክንያም ኃይሌ፣ ሽሪላ በባህያቸው የሚያጠቁ ልጆች ናቸው፡፡ ለምሳሌ እኔ ለምፈልገው የ5-3-2 አጨዋወት መሃል ሜዳው ላይ እንደአማኑኤል አይነት ሰው ይዘህ ወይም ደግሞ 4-4-2 ለመጫወት ብንፈልግ ለፈለግነው የጨዋታ አይነት የሚሆን የተሻለ የተከላካይ አማራጭ አለን፡፡ አሁን በረኛ ነው የቀረን። ከሱም ጋር እየተነጋገርን ነው በቅርቡ በጣም ግሩም በረኛ ቡድናችንን ይቀላቀላል፡፡
ወደ ኢትዮጵያ እንደመጡ በኳስ ቁጥጥር ላይ ያተኮረ ቡድን እንደሚመርጡ ገልጸውልን ነበር። ከሁለተኛ ዙር በኋላ ግን ይህ ሃሳብዎን ቀይረው ቀጥተኛ ኳስ ሲጫወቱ ነበር፡፡ ዘንድሮስ ምን ታስቧል?
አዎን አጫጭር ኳስ መጫወት ጀምረን ጥሩ ነበርን። ነገርግን ደግሞ በተለይ ሁለተኛ ዙር ፋዬን ከፊት አርገን ቀጥተኛ ጨዋታ ስንጫወትም ነበር፣ ይህ ብቻውን መጥፎ አይደለም። ምክንያቱም ወደፊት መጫወትም አስፈላጊ ነው ለምሳሌ የስፔንን ብሔራዊ ቡድን ብታይ ኳስ የመያዝ ችግር የለባቸውም፤ ግን ኳስ መያዝ ብቻውን ግን አሸናፊ አያደርግም፡፡ አምና ከሐዋሳ ጋር አዲስ አበባ ላይ፣ ከደደቢት ጋር በሁለቱም ዙር በተለይ ደግሞ ከድሬዳዋ ጋር በሜዳችን ያደረግናቸውን ጨዋታዎች ስታይ የግብ ማግባት ችግር እንደነበረብን ትረዳለህ፡፡ ኳስ የመያዝና የመጫወት ችግር የለብንም ከማንም በተሻለ ማድረግ እንችላለን ደግሞ በ30 ሜትር ውስጥ ኳስን ይዞ የመጨረስ ብቃት ያስፈልገናል፤ በዚህ ቅድም ውድድር ዝግጅት በተለይ ትኩረት ሰጥተን እንሰራለን፡፡ ክለቡ የቪዲዮ ተንታኝ እንዲቀጥርልን ጠይቀናል። ስህተቶቻችንን እያረምን የግብ ማግባት ብቃታችንን እናሻሽላለን፡፡ ከአጥቂዎች ጋር ብቻ ከግብ ፊት ለፊት የተለየ ስልጠና እንደሚያሰፈልገን አውቀን በቅድመ-ውድድር ወቅት ተጨማሪ ልምምድ በሳምንት ሁለት ቀን እናረጋለን፡፡ ውድድር ከተጀመረ በኋላም ቢያንስ በሳምንት አንድ ቀን እየሰራን እንቀጥላለን፡፡አንድ የጨረስነው የተሟላ አጥቂ አለ ቡድናችንን የሚቀላቀል፡፡ በጣም ከፍ ያለ ፕሮፋይል ያለው አጥቂ ነው። በብሔራዊ ቡድን የሚጫወት፤ ከሱ ጋር አቡባካር አለ። ስለዚህ የተሸለ የማጥቃት አቅም አለን፡፡ ግብ ማስቆጠር በመሰረቱ የቴክኒክ ጉዳይ ብቻ አይደለም። የአእምሮም ጭምር ነው፡፡ አጥቂዎቻችን ሳኑሚንም ጨምሮ ከጎል ፊትለፊት የጨራሽ እና የገዳይ አዕምሮ ዝግጅት ነበር የጎደላቸው፡፡ ከጎል ፊት ለፊት ስትሆን ሁሌም ገዳይ መሆን ነው ያለብህ፡፡ እኔ አጥቂዎች ገዳይ እንዲሆኑ ነው የምፈልገው፡፡ አምና ብዙ ጨዋታዎች ላይ የጊዮርጊስ ጨዋታን ጨምሮ ነጥብ ጥለናል፡፡ በልምምድ ላይ ጎል ስቶ የሚስቅ ተጫዋች በጣም ነው የሚያበሽቀኝ፡፡ ልታለቅስ ነው የሚገባው፡፡ በቴክኒክም በአዕምሮም ዝግጁ የሆነ አጥቂ ያስፈልገናል፡፡ስለዚህ በስነልቦናም በቴክኒክም የተሻለ አጥቂ እንዲኖረን እየሰራን ነው፡፡
ስለአካል ብቃትስ ምን ይላሉ፤ በተለይ ታዳጊዎቹ ተወዳዳሪ መሆን ይችላሉ?
የአካል ብቃት አሰልጣኝ እንዲቀጠር ጠይቀናል፡፡ በቅርቡ ከፍ ያለ ፕሮፋይል ያላቸው የአካል ብቃት አሰልጣኝ የአሰልጣኝ ቡድኑን ይቀላቀላሉ ብለን እንጠብቃለን፡፡ በተለይ ኃይሌ ሚኪ አዲስ ከሜዳ ላይ ልምምድ ባሻገር ተጨማሪ ጊዜ በጂም እንዲሰሩ ይደረጋል። የጡንቻ ማበልጸጊያ ልምምዶችን ይሰራሉ፡፡ በዚህ የዝግጅት ወቅት ታዳጊዎቹ በሙሉ አትሌት መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ ከባለሙያው ጋር ሆነን ይሄን እናረጋለን ብዬ እጠብቃለው፡፡
ሁሌም ቢሆን ለተጫዋቾቼ የምነግራቸው የእግር ኳስ ተጫዋች እንደጦር መሳሪያ መሆን ነው ያለበት፡፡ ኃይሌ በጣም ጥሩ ተጫዋች ነው ነገር ግን ኃይሌ ጡንቻው ቢዳብር የሱ ብቻ ሳይሆን የሚኪ እና አቡበከር ምን አይነት ተጫዋቾች እንደሚሆኑ አሰበኸዋል?! ቡድኑ ጂም እንዲያሰራልን ጠይቄ ፕሬዝዳንቱ ተቀብለውኝ ጂም እየተገነባልን ነው። ለዚህም ፕሬዝዳንቱን አመሰግናለው። ተጨማሪ የኣካል ብቃት ልምምዶችን እናረጋለን በዛውም የስነልቦና ዝግጅት እናረጋለን። ምክንያቱም ዘመናዊ እግር ኳስ የተሟላ የአካል ብቃት ነው፡፡ አንድ ተጫዋች የተሻለ እንዲሰጥህ ልታለፋው ይገባል፡፡ መልፋት መድከም የማይወድ ከሆነ እግር ኳስ ተጫዋች አይደለም፡፡ ጉዳት አድርስበት ማለት ሳይሆን ግን ልታፈጋው ልታለፋው ይገባል፡፡ እኔ ለተጫዋቾቼ የምላቸው ጨዋ ልጅ አያሸንፍም (Nice boy never wins)። ተጫዋቾቼ ሁሌም እንደቡና ደጋፊዎች እንዲሆኑልኝ ነው የምፈልገው። ለተጫዋቾቼ የምላቸው ጨዋ ልጅ አያሸንፍም እኔ የምፈልገው ተጫዋቾቼ ሁሉ እንደቡና ደጋፊዎች እንዲሆኑ ነው፡፡ በርግጥ ከመሃል ሽንፈትን የሚጸየፉ ጀግና ጀግና ልጆች አሉ ፤ ቶማስ፣ ኃይሌ፣ ወንድይፍራው፣ አቡበከር፣ አማኑኤል፡፡ እኔ ሁሉም የአውሬነት መንፈስ እንዲኖራቸው ነው የምፈልገው፡፡ በልምምድ ላይ ስምንት ለአስር ሆነው እርስ በርስ እንዲጋጠሙ አደርጋለው፤ ስምንቶቹ በጎዶሎ ልጅ ለማሸነፍ ያላቸውን መንፈስ ሁሉም ወደሜዳ እንዲያመጡት ነው የምፈልገው፡፡ ወደሜዳ ሲገቡ ሁሌም የምነግራቸው እስቲ ደጋፊውን ተመልከቱት ፤ የነሱን ሁለት እጥፍ እልህ ሊኖራችሁ ይገባል እላቸዋለው፡፡ እግር ኳስ ፌይር ፕሌይ አይደለም መሸናነፍ ነው፤ መጀመሪያ ማሸነፍ አለቀ፡፡
ለዕረፍት ከመሄድዎ በፊት ብዙ ተጫዋቾች ወደቡና እንዲመጡ ጠይቀው ነበር። ከጠየቋቸው ብዙዎቹ ወደሌላ ክለብ እንደሄዱ እየተነገረ ነው፤ ስለዚህስ ምን ይላሉ?
ባልመጡት ልጆች ምንም ጸጸት አይሰማኝም፤ የኔ አቋምም ከፕሬዝዳንታችን ጋር አንድ ዓይነት ነው፡፡ ከባለፈው ዓመት ጀምሮ ወደ ቡና እንደሚመጡ ቃል ገብተው የነበሩ ተጫዋቾች ከፍተኛ ደሞዝ ጠይቀው ወደሌላ ክለብ እንደሄዱ ፕሬዝዳንታችን ነገሩኝ፤ እኔም መጨነቅ እንደማይገባንና መፍትሔ እነደምንፈልግ ለፕሬዝዳንታችን ነገርኳቸው፡፡ እንደዚህ ዓይነት ደሞዝ ቡና ሊከፍል አይችልም፡፡ ስለሌላ ክለብ ሀሳብ መስጠት አልችልም፡፡ እነሱ የራሳቸው የገቢ ምንጭ ሊኖራቸው ይችላል፤ ትርፋማ ሊሆኑ ይችላሉ ፤ አያገባኝም፡፡ ለምሳሌ ፓሪ ሰን ዠርሜይን በጀተ አለው ከፍተኛ ደሞዝ መክፈል ይችላል ማርሴይ ደግሞ ብር የለውም መክፈል አይችልም፡፡ እግር ኳስ ብር ያለው ብቻ አይደለም፡፡ ፓሪ ሰን ዠርሜይን ለአውሮፓ ቻምፒንስ ሊግ ግማሽ ፍጻሜ ማለፍ አልቻለም ማርሴይ ግን የአውሮፓ ማህበረሰብ ዋንጫ ተፋላሚ ነበር ፤ ይሄ እግር ኳስ ውስጥ ያለ ነው፡፡ ቡና በጣም ትልቅ ክለብ ነው፡፡ በጣም ብዙ ደጋፊ ያለው ክለብ ነው፡፡ የቡና ሃብቱ ደጋፊው ነው፡፡ ስለዚህ የተሻለ ማርኬቲንግ ሰርተን ሳቢ ክለብ መሆን አለብን፡፡ ዛሬ ቡናን ተጫዋቾች አልመረጡንም ነገ ግን ተመራጭ መሆን ማድረግ እንችላለን፡፡ ቡናን በኢትዮጵያና ባደጉ ሃገራት ክለቦች መካከል ድልድይ እንዲሆን ማድረግ እንችላለን ፤ አውሮፓ፣ ደቡብ አፍሪካ ወዘተ፡፡ ልጆች እያሳደግን አንድ ዓመት ሁለት ዓመት እየተጠቀምን ወደ ታላላቅ ክለቦች ብንልክ ለቡና የተሻለ የገቢ ምንጭ መፍጠር እንችላለን፡፡ ታዳጊዎችም ለወደፊት ህይወታቸው ሲሉ የሚመርጡት ክለብ መሆን ይችላል፡፡ ጌታነህ ቡናን አልመረጠም ብዬ አላዝንም ፤ የሱ ምርጫ ነው፡፡ ነገር ግን ጌታነህ እንዲመርጠን ይህን ያህል ከመክፈል እኔ ይልቅ ሁለት ሦስት ታዳጊዎች ከታች አምጥተን እዚህ የመጣኸው ሻምፒዮን ለመሆን ነው፡፡ ሻምፒዮን ከሆንን በኋላ ግን ባለን ግንኙነት አውሮፓ ወይም ደቡብ አፍሪካ የምትሄድበት ዕድል አለ ብንላቸው ለራሳቸው ሲሉ ይመርጡናል፡፡
አምና በኃይሌ በሚኪ ሁላችንም እንደተደሰትን ዘንድሮ ወይም በሚቀጥው ዓመት ኃይሌ፣ ሚኪያስ ወይም ሌላ ተጫዋች አውሮፓ የመሄድ ዕድል ቢገጥመው በቡና የሰለጠነ ታዳጊ በታላቅ ክለብ ውስጥ ማንንም ነው ደስ የሚለው፡፡ እኛ ነን ብር የለንም ይሁና፡፡ ምንም ችግር የለውም አንድ ታዳጊ አምጥተን በቀን አስር ሰዓት ወይም ከዛ በላይ ብንሰራበት ከጌታነህ የተሻለ አጥቂ ማግኘት አንችልም እንዴ ? የዛሬ ዓመት በዚህ ሰዓት ኃይሌ ሚኪ የዚህን ያህል ይሆናሉ ብሎ ያሰበ አለ እንዴ ? ስለዚህ ቡና ይህን ያህል ገንዘብ ለጌታነህ መክፈል አለበት ብዬ አላስብም የቡና አሰልጣኝ በመሆኔ ኩራት ነው የሚሰማኝ፡፡
የቅድመ-ውድድር ዝግጅታችሁ ምን ይመስላል፤ የመጪው ዓመት የቡና ዕቅድስ ምን ይሆን?
ዝግጅት በዚህ ሳምንት ጀምረናል። ለውድድር ከአንድ ወር በላይ ጊዜ አለን። የኢትዮጵያ ዋንጫ ግማሽ ፍጻሜ አለ፡፡ በርግጥ ቡድኑ አልተሟላም ብሔራዊ ቡድን የሄዱ ልጆች አሉ፣ ገና ያልፈረሙ አሉ፣ ፈርመው ቡድኑን ያልተቀላቀሉም አሉ፡፡ የቅድመ-ውድድር ዝግጅታችንን የምናደርገው በባህርዳር ነው፡፡ እሁድ እንሄዳለን ብዬ አስባለው፡፡ በባህርዳር እንዲሆን የፈለኩበት ምክንያት ነገሮችን መቀየር ስለፈለግኩ ነው፡፡ አምና ሃዋሳ እንደነበሩ ሰምቼያለው ስለዚህ ዘንድሮ ከለመዱት ውጭ አዲስ አካባቢ መሆኑ ጥሩ ነው፡፡ አዲስ አስተሳሰብ፣ ከለመዱት ውጭ የሆነ እይታ ለማምጣት ይረዳል፡፡ እኔ ወደ ቡና የመጣሁት ሻምፒዮን ለመሆን ነው፡፡ ቡና ከመጣው በኋላ ሁለት ሦስት ሥራ አግኝቼ ቡና ያልጨረስኩት ሥራ ስላለኝ ሳልቀበል ቀርቼያለው ሁሌም እንደምለው ከቡና ጋር ሻምፒዮን መሆን እፈልጋለው፡፡ ይሄን ዓመት ደጋፊው ታግሶናል፣ ዕድል ሰጥቶናል ለሚቀጥለው ዓመት ግን ከማሸነፍ ውጭ ዕድል የለንም፡፡ ቡና ውስጥ ሁለተኛ መውጣት አይቻልም፡፡ ያለን ዕድል ማሸነፍ ብቻ ነው፡፡ እኔ ሻምፒዮን መሆን ብቻ አይደለም የምፈልገው፤ ምክንያቱም ቡና ዋንጫ አሸንፎ ያውቃል ነገር ግን ዋንጫውን ደግሞ ማሸነፍ ነው ዕቅዳችን፡፡ ዘንድሮ የጥሎ ማለፉን ውድድር ማሸነፍ አለብን፣ የዓመቱ ሻምፒዮን መሆንም ምርጫ ሳይሆን ግዴታችን ነው፡፡ ስለዚህ ዘንድሮ ለቡና የተለየ ጊዜ ነው፡፡ ሁለቱንም ውድድር ለማሸነፍ ነው ዕቅዳችን፡፡ ፕሬዝዳንታችን፣ የቡና አስተዳደር ቦርድ፣ የቡና ደጋፊዎች ሁላችሁም እምነታችሁን ስለጣላችሁብኝ ከልብ አመሰግናለው፣ ዘንድሮ ታሪክ እንደምንጽፍ ተስፋ አለኝ በልልኝ፡፡ ሶከር ኢትዮጵያንም አመሰግናለው፡፡