ለ2019 የካሜሩን የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ጨዋታዎች ዝግጅት በማድረግ ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ነሀሴ 27 በሀዋሳ ከብሩንዲ አቻው ጋር የወዳጅነት ጨዋታን ያደርጋል፡፡
በአፍሪካ ዋንጫ የ2019 ካሜሩን ለምታስተናግደው ውድድር ከጋና ሴራሊዮን እና ኬኒያ ጋር የተደለደሉት ዋልያዎቹ በመጀመሪያው የማጣሪያ ጨዋታ ጋና ላይ በአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ እየተመሩ 5-0 በሆነ ውጤት መሸነፋቸው ይታወሳል። ቡድኑ ጳጉሜ 4 ለሚያደርገው ሁለተኛው የምድቡ የማጣሪያ የሴራሊዮን ጨዋታ ከመድረሱ አስቀድሞ የወዳጅነት ጨዋታን እንደሚያደርግ ተሰምቷል፡፡ ያለፉትን 15 ቀናት ዕርስ በዕርስ ከሚደርጉ የሜዳ ላይ ጨዋታዎች በተጨማሪ ከኤርትራ ብሔራዊ ቡድን ጋር የወዳጅነት ጨዋታ ያደርጋል ተብሎ የነበረ ቢሆንም የኤርትራ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ምላሽ ባለመስጠቱ ምክንያት ጨዋታው ተሰርዟል።
ይሁንና ብሔራዊ ቡድኑ ለካሜሩን ብሔራዊ ቡድን እና ለብሩንዲ ብሔራዊ ቡድን በአሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ እና በፌድሬሽኑ በኩል በተደረገ ጥረት የቡሩንዲ ብሔራዊ ቡድንን ፍቃደኝነት አግኝቷል። በዚህም መሰረት የፊታችን ሳምንት ዕሁድ ነሀሴ 27 ዋልያዎቹ ከቡሩንዲ ብሔራዊ ቡድን ጋር የወዳጅነት ጨዋታቸውን በሀዋሳ አለም አቀፍ ስታዲየም እንደሚያደርጉ አቶ ሰለሞን ገ/ስላሴ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡ አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱም ከነጥብ ጨዋታው በአንድ ሳምንት የሚቀድመው ይህ የወዳጅነት ጨዋታ የመጨረሻ ቡድናቸውን ለመለየት እንደሚረዳቸው ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል።
በብሔራዊ ቡድኑ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙርያ የተዘጋጀ ፅሁፍ ከቆየና በኋላ ይጠብቁን።