የቀይ ቀበሮዎቹ ጉዞ በዩጋንዳ ተገትቷል

በካፍ የማጣርያ አሰራር ለውጥ ምክንያት ከዘንድሮ ጀምሮ በዞን ተከፋፍሎ እየተካሄደ የሚገኘው የአፍሪካ ከ17 ዓመት በታች ዋንጫ የማጣርያ ውድድር የሴካፋ ዞን በዛሬው ዕለት ፍፃሜውን ሲያገኝ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ያመራው ቡድንም ተለይቷል።

በአንድ ምድብ የነበሩት ኢትዮጵያ እና ዩጋንዳን ያገናኘው ጨዋታ በምድቡ ግንኙነታቸው ኢትዮጵያ 1-0 ማሸነፏ እና ያለሽንፈት ለፍፃሜ መድረሷን ተከትሎ ቀይ ቀበሮዎቹ የማሸነፍ ግምት ቢያገኙም 3-1 በሆነ ውጤት ተሸንፈዋል።

የመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ እንቅስቃሴ በአብዛኛው የዩጋንዳዎች የበላይነት የታየበት ነበር። በ2ኛው ደቂቃ ወንድምአገኝ ያገኘውን ጥሩ ዕድል ሳይጠቀምበት ከቀረ በኋላ ዩጋንዳዎች ቀስ በቀስ በቀይ ቀበሮዎቹ ላይ ጫና መፍጠር ችለዋል። በዚህ ሂደት ውስጥ ተደጋጋሚ የማዕዘን ምቶችን ማግኘት የቻሉት ዩጋንዳዎች 15ኛው ደቂቃ ላይ ቀንቷቸዋል። ሁለተኛው የግብ ቋሚ ላይ የተጣለችውን የማዕዘን ምት ሳምሶን ካሶዚ ነበር ወደ ግብነት መቀየር የቻለው። ከግቡ መቆጠር በኋላ ኢትዮጵያዎች በቀኝ መስመር ባድላ እንቅስቅሴ ኳስ መስርተው ለመውጣት ጥረት ሲያደርጉ ቢታይም በብዛት የዩጋንዳ የአማካይ መስመር ተጨዋቾች የቅብብል መስመሮቻቸውን ሲያቋርጡ ቆይተዋል። ዩጋንዳዎች የኢትዮጵያ የማጣቃት እንቅስቃሴ በሚሰነዘሩባቸው የሜዳ ክፍሎች ላይ በቁጥር ተበራክተው በመከላከሉም ስኬታማ ነበሩ።

ቀይ ቀበሮዎቹ በሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ተበታትነው በታዩባቸው ቀጣይ ደቂቃዎች ዩጋንዳዎች በተደጋጋሚ ወደ ሶስተኛው የሜዳ ክልል ይደርሱ ነበር። በኢትዮጵያ በኩል 20ኛው ደቂቃ ላይ ወንድምአገኝ ከሳጥን ውጪ ተከላካዮችን አታሎ የሞከረው እና የተደረቡበት ኳስ ተጠቃሽ ነበር።  የተከላካይ መስመራቸውን ወደ ፊት ገፍተው የኳስ ቁጥጥር የበላይነትን በመያዝ ወደ ዩጋንዳ የሜዳ አጋማሽ ለመግባት የሚያደርጉት ጥረት በተደጋጋሚ የከሸፈባቸው ኢትዮጵያዊያኑ ለመልሶ መጠቃት የተጋለጡባቸው አጋጣሚዎች ይበልጥ አስፈሪ ነበሩ። በተለይም 36ኛው ደቂቃ ላይ ምንተስኖት በቀኝ መስመር ሰብሮ ገብቶ መሬት ለመሬት ወደ ግብ የላካት ኳስ ግብ ጠባቂውን ካለፈች በኋላ መልካም የማግባት ዕድል ቢፈጠርም በብዙ ርብርብ ኳሷ መክናለች። የመጀመሪያው አጋማሽ በዚህ መልኩ የዩጋንዳዎችን የበላይነት አስመልክቶን የተጠናቀቀ ነበር።


በሁለተኛው አጋማሽ ኢትዮጵያ የተሻሻለ ቡድን ይዛ እንደምትቀርብ ብትጠበቅም እንደመጀመርያው ሁሉ በዩጋንዳ ብልጫ ተወስዶባታል። በ62ኛው ደቂቃ በኢትዮጵያ በኩል በአግባቡ ያልተሻማ የቅጣት ምት ሲመለስ ዩጋንዳዎች በጥሩ የመልሶ ማጥቃት በፍጥነት የኢትዮጵያ የግብ ክልል ደርሰው ኢዲ አብዲል ወደግብነት ቀይሮ ልዪነቱን ወደ ሁለት አስፍቷል። ኢዲ በ85ኛው ደቂቃ ላይም በድጋሚ አስቆጥሮ የዩጋንዳን መሪነት ወደ ሶስት ከፍ አድርጓል። ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሲቃረብ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ምንተስኖት እንድርያስ ወደ ግብነት በመቀየር በውድድሩ እያንዳንዱ ጨዋታዎች ላይ ጎል ያስቆጠረ ብቸኛው ተጫዋች መሆን ችሏል።
ዩጋንዳ ጨዋታውን 3-1 ማሸነፏን ተከትሎ የሴካፋ ዞን የአፍሪካ ከ17 ዓመት በታች ዋንጫ ቻምፒዮን በመሆን ወ አፍሪካ ዋንጫው አምርታለች። በአዲሱ የካፍ የውድድር አሰራር መሰረትም የሴካፋ ዞን በአስተናጋጇ ታንዛንያ እና በቻምፒዮኗ ዩጋንዳ የሚወከል ይሆናል።

የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ለመጨረሻ ጊዜ በውድድሩ የተሳተፈው በቀድሞ መጠርያው የአፍሪካ ታዳጊዎች ዋንጫ ላይ በ1997 ነበር።