ቀይ ቀበሮዎቹ ስለ ታንዛንያው ውድድር ይናገራሉ

በ2019 ታንዛኒያ ለምታስተናግደው ከ17 አመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን በአሰልጣኝ ተመስገን ዳና እየተመራ የዞኑን የማጣሪያ ጨዋታ በታንዛኒያ አከናውኖ ዛሬ ማለዳ ወደ አዲስ አበባ ሲገባ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አቀባበል ተደርጎለታል።

በውድድሩ ጥሩ ጊዜ በማሳለፍ የምድባቸው መሪ ሆነው ወደ የግማሽ ፍፃሜው ብሎም ወደ ፍፃሜ በማለፍ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ያሳዩት ቀይ ቀበሮዎቹ በብዙ የስፖርት ቤተሰብ ዘንድ ማበረታቻዎች እየተለገሳቸው ይገኛል። በግል ጥሩ ጊዜ ያሳለፉት በየነ ባንጃ፣ ምንተስኖት እንድርያስ እና ግብ ጠባቂው አላዛር ማርቆስ ስለ ውድድሩ እና ተያያዥ ጉዳዮች ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረጉት ቆይታ ማብራሪያዎችን ሰጥተዋል።

በቅድሚያ አስተያየቱን የሰጠው የቡድኑ ዋና አምበል በየነ ባንጃ ስለ ቆይታቸው ይናገራል። “ቆይታችን ጥሩ ነበር። ከዝግጅት ጊዜ ጀምሮ እስከ ፍፃሜው ጨዋታ ድረስ ጥሩ ነገሮችን ለሃገራችን ለማበርከት ተግተን ስንሰራ ቆይተናል። ሃገራችን በነበርንበት ወቅት የነበረን የዝግጅት ጊዜ በጣም አነስተኛ ነበር። ይሄ ደግሞ ያሰብነውን ነገር ተግባብተን እና እንደ ቡድን ተዋህደን እንዳናመጣ አድርጎናል። ነገር ግን በነበረችው አጭር ጊዜም ቢሆን አሰልጣኛችን ጥሩ ስልጠናዎችን በመስጠት ያለንን አቅም አውጥተን እንድንጫወት አድርጎናል።”


በውድድሩ ላይ ሐት-ትሪክ መስራት የቻለው በየነ በዝግጅት እና በውድድሩ ላይ ስለገጠሟቸው ፈተናዎች የሚከተለውን ብሏል። “እዚህ እያለን ቅድም እንዳልኩት ልምምድ በአግባቡ ሰርተናል ብዬ አላምንም። ይህ ደግሞ የሆነው በኤም አር አይ መርመራ ምክንያት ነው። ልምምዶችን እያቋረጥን ለምርመራ ከሃዋሳ ወደ አዲስ አበባ ስንመላለስ ነበር። ይሄ በዝግጅት ጊዜ የነበረው ችግር ነበር። በውድድሩ ላይ ደግሞ ስንገጥማቸው የነበሩት ቡድኖች የያዙዋቸው ተጨዋቾች የኛ እኩያ እንዳልሆኑ ያስታውቃል። ይሄ ደግሞ አግባብ በሌለው ሁኔታ በእድሜ መበለጣችን በተለይ በአካላዊ ሁኔታ ከኛ የሚበልጡ ቡድኖችን መግጠማችን አላማችንን እንዳናሳካ አድርጎናል” ብሏል። በየነ ጨምሮም በትንሹም ቢሆን ታንዛንያ እንደገቡ የአየር ፀባዩን ለመልመድ እንደተቸገሩ አስረድቷል።
ማብራሪያውን መስጠት የቀጠለው በየነ በመጨረሻም ስለ ውጤታቸው የተሰማውን ገልጿል። “እውነት ለመናገር እኛ ሁለተኝነት አይገባንም፤ ውድድሩ በትክክለኛው መንገድ ቢካሄድ ኖሮ እኛ ነበርን የውድድሩ አሸናፊ የምንሆነው፤ ነገር ግን አልሆነም። በመጣው ውጤት ብንከፋም እኛ ሁለተኛ ወጥተናል። ከኛ በኃላ የሚመጡት የቡድኑ ተጨዋቾች ደግሞ ከኛ በላይ አንደኛ ወተው ሃገራችንን በቀጣይ በአፍሪካ ዋንጫው መወከል አለባቸው” ብሏል።

በመቀጠል ቡድኑ እስከ ፍፃሜው እንዲጓዝ ግቡን በአግባቡ ሲጠብቅ የነበረው እና በውድድሩ በኮከብ ግብ ጠባቂነት ተመርጦ ሽልማቱን የወሰደው አላዛር ማርቆስ ስለውድድሩ አስተያየቱን በመስጠት ይጀምራል። “ውድድሩ ጥሩ ነበር። ሁላችንም የአቅማችንን ለሃገራችን ስኬት ለማምጣት ስንጥር ነበር። ከምድብ ጨዋታዎች ጀምሮ እስከ ፍፃሜው ድረስ በመግባባት ጥሩ ጊዜ አሳልፈናል። ነገር ግን አላማችንን ማሳካት አልቻልንም፤ በዚህ ደግሞ በጣም አዝነናል”ብሏል።

ስኬታማ ጉዞ ስለማድረጋቸው ሚስጥር በመቀጠል መልስ የሰጠው አላዛር አንድነታቸው ዋንኛ መሳርያ እንደሆነ ያምናል። “ሃገራችን በአፍሪካ ዋንጫው ላይ እንድትካፈል የምንችለውን ሁሉ ነገር አድርገን ነበር። ነገር ግን ከተጋጣሚያችን የእድሜ አለመመጣጠን ጀምሮ እስከ ዳኝነት በደሎች ድረስ ችግሮች ደርሰውብን እኛ ግን ይህንን ሁሉ በመቋቋም በአንድነት እና በመግባባት እስከ ፍፃሜው ጨዋታ ደርሰናል” ብሎ የቡድኑ ጠንካራ መንፈስ ስኬታማ ጊዜ እንዲያሳልፉ እንደረዳቸው አስረድቷል።

በውድድሩ ሁለት የፍፁም ቅጣት ምቶችን ያመከነው አላዛር ስለ ሃገራችን የግብ ጠባቂ ችግር እና መደረግ ስላለበት ነገር በስተመጨረሻ አላዛር አስተያየቱን ሰጥቷል። “በግሌ በኮከብ ግብ ጠባቂነት በመመረጤ ደስተኛ ሆኛለሁ። ምንም እንኳን ሃገሬን ለአፍሪካ ዋንጫው ማብቃት ባልችልም የኔ ብቃት አሁንም በግብ ጠባቂ ረገድ ስራዎች ከተሰሩ ሃገራችን ብዙ ግብ ጠባቂዎችን ማፍራት እንደምንችል አሳይቷል ብዬ አስባለው። ስለዚህ በግብ ጠባቂ በኩል ቀጣይነት ያላቸው ስራዎች ቢሰሩ ጥሩ ነው እላለው።”

በመጨረሻ ስምንት ግቦችን ለቡድኑ በማስቆጠር የውድድሩ ኮከብ ግብ አግቢ በመሆን ያጠናቀቀው የሃዋሳ ከተማው አጥቂ ምንተስኖት እንድርያስ ሃሳቡን አጋርቶናል። በፍፃሜው ጨዋታ ግቦችን አስቆጥሮ ሃገሩን ወደ አፍሪካ ዋንጫው ባለማሳለፉ እንዳዘነም ይናገራል። “በፍፃሜው ጨዋታ ግብ አስቆጥሬ ሃገሬን ወደ አፍሪካ ዋንጫው ባለመውሰዴ በጣም አዝኛለው። ከምድብ ጨዋታዎች ጀምሮ በተከታታይ ጎሎችን ማስቆጠሬ ደስተኛ አድርጎኝ ነበር። ነገር ግን በፍፃሜው ጨዋታ በግሌ  ውጤት እንድናመጣ ባለማድረጌ ድስታዬን አቀዝቅዞታል።” ብሏል።

በእያንዳንዱ ጨዋታ ጎል በማስቆጠር ታሪክ የሰራው ምንተስኖት እንደ ቡድን ጓደኞቹ ሁሉ ዋንጫውን ያጡበት ምክንያት በእድሜ አለመመጣጠን እንደሆነ ተመሳሳይ ሃሳብ ሲያነሳ ከዚህ በኃላ ግን ከፍተኛ ስራዎች ቀደም ብለው ተሰርተው ቡድኖች ወደ ውድድር መቅረብ እንዳለባቸው አስረድቷል።