ከነሀሴ 6 ጀምሮ በሀዋሳ ከተማ ሲደረግ የቆየው የኢትዮጵያ ክልል ክለቦች ሻምፒዮና በዛሬው እለት በአሰላ ከተማ ሻምፒዮንነት ተጠናቋል።
ከመላ ሀገሪቱ በተውጣጡ 31 ክለቦች መካከል ሲደረግ ቆይቶ ስምንት ክለቦችን ወደ አንደኛ ሊግ አሳድጎ ዛሬ ደግሞ የፍፃሜ ጨወታወች ለደረጃ እና ለፍፃሜ ተደርገው ውድድሩ ሲጠናቀቅ አስቀድሞ ለደረጃ 3፡00 ላይ በሀዋሳ ግብርና ኮሌጅ በተደረገ ጨወታ አረካ ከተማ ከአዲስ አበባ ውሀ እና ፍሳሽ ተገናኝተው አረካዎች በመጀመሪያው አጋማሽ ባስቆጠሩት ብቸኛ ግብ 1-0 በማሸነፍ ሶስተኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል፡፡
9፡00 ላይ ለዋንጫ ሀዋሳ ሰው ሰራሽ ሜዳ ላይ አሰላ ከተማን ከቄራ አንበሳ አገናኝቶ አሰላ 1-0 በማሸነፍ የዋንጫ ባለቤት ሆኗል። በጨዋታው ሁለቱም ክለቦች እልህ አስጨራሽ የሆነ የሜዳ ላይ የፉክክር መንፈስን ለመመልከት አስችለውናል። ነገር ግን እንደ እንቅስቃሴያቸው ግን ይህ ነው የሚባሉ የግብ አጋጣሚዎችን መመልከት አልቻልንም። 69ኛው ደቂቃ ግን ሀብታሙ ገመቹ ከመስመር የተሻገረለትን ኳስ ወደግብነት ለውጧት አሰላ ከተማን የ2010 የኢትዮጵያ ክልል ክለቦች ሻምፒዮን እንዲሆን አድርጎታል ፡፡
ከፍፃሜው ጨዋታ በኃላ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን የስራ አስፈፃሚ አባል አቶ አብዱራዛቅ ሁሴን እንዲሁም የደቡብ ክልል እግር ኳስ ፌድሬሽን ም/ፕሬዝዳንት አቶ ደመላሽ ይትባረክ፣ የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ እንዲሁም ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በስነ ስርአቱ ላይ በመገኘት ለቡድኖች በየደረጃው አሸናፊ ለሆኑት እና ልዩ ልዩ ሽልማቶችን አበርክተዋል፡፡
ከአንድ እስከ ሶስተኛ የወጡ ክለቦች ሽልማት
1 አሰላ ከተማ – 30ሺህ ብር
2 የቄራ አንበሳ – 20 ሺህ ብር
3 አረካ ከተማ – 10 ሺህ ብር
ምስጉን ዳኛ
1 ፌ/ልዋና ዳኛ አባድር መሀመድ – 3 ሺህ ብር
2 ፌ/ል ረዳት ዳኛ ሀብታሙ ተሰማ – 3 ሺህ ብር
የኮከብነት ሽልማት
ኮከብ ግብ ጠባቂ – ተመስገን ግርማ -ከአሰላ
ኮከብ ተጫዋች – ረድዔት እንግዳ – ከቄራ አንበሳ
ኮከብ ግብ አግቢ – አህመድ ሁሴን -ከአሰላ 5 ጎል
እያንዳንዱ የ3 ሺህ ብር ተሸላሚ
ኮከብ አሰልጣኝ -አስራት ሂርጶ – ከአሰላ 4 ሺህ ብር
የፀባይ ዋንጫ -የአዲስ አበባ ውሀና ፍሳሽ
ሀዋሳ ከተማ በመልካም መስተንግዶ የዋንጫ ተሸላሚ