አሰልጣኝ ውበቱ አባተን ከአራት አመት የሃዋሳ ቆይታ በኃላ ወደ ቡድናቸው ያመጡት ፋሲል ከነማዎች በተጨዋች ዝውውር እና በአሰልጣኝ ቅጥር ክረምቱን ተጠምደው እያሳለፉ እንደሚገኝ ይታወቃል።
ዛሬ ረፋድ ክለቡ በይፋዊ ገፁ እንደገለፀው አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ የአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ሁለተኛ ምክትል ሆነው ፊርማቸውን እንዳኖሩ አስታውቋል። የቀድሞው የአዳማ ከተማ አምበል እና በክለቡ በውበቱ አባተ ስር ተጫዋች የነበረው አሰልጣኝ ይታገሱ ከዚህ ቀደም የአዳማ ከተማን ከ17 አመት በታች ቡድን እና ተስፋ ቡድንን ሲያሰለጥን ሶስት አመታትን ያሳለፈ ሲሆን ለቀጣዮቹ ሁለት አመታት ከአፄዎቹ ጋር ቆይታ ለማድረግ ፊርማውን እንዳኖረ ተገልጿል።
ከዚህ ቀደም አሰልጣኝ ውበቱ አባተ አንደኛ ምክትል አሰልጣኝ አድርጎ አሰልጣኝ ኃይሉ ነጋሽን ወደ ክለቡ ማምጣታቸው ሲታወስ ከዚህም በኃላ የአካል ብቃት አሰልጣኝ ወደ ክለቡ ለማምጣት እና የአሰልጣኝ ቡድን አባላቱን ለማስፋት እቅዶች እንዳሉ ተገልጿል። በተያያዘ ዜና ወደ ባህር ዳር ከተማ የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን ለማድረግ ያመሩት አፄዎቹ ከታዳጊው ቡድን የአጥቂ፣ የአማካይ እና የተከላካይ በአጠቃላይ አራት ተጨዋቾችን ወደ ዋናው ቡድን ለመቀላቀል ለተጨዋቾቹ ጥሪ መቅረቡ ተሰምቷል።