የሀዋሳው ክለብ ደቡብ ፖሊስ ትላንት በ30ኛው ሳምንት የምድብ ለ ጨዋታ ድሬዳዋ ፖሊስን በመርታት ወደ ፕሪምየር ሊግ ማደጉን አረጋግጧል። ደቡብ ፖሊስ ቡድኑን በአንጋፋዎች እና ወጣቶች ስብጥር የመመዋቀር ከ8 ዓመታት በኋላ ወደ ፕሪምየር ሊግ ሲመለስ ባለ ልምድ ከሆኑት ተጫዋቾች መካከል አምበሉ ቢንያም አድማሱ ይጠቀሳል።
በ2002 ደቡብ ፖሊስ ወደ ብሔራዊ ሊግ ሲወርድ ክለቡን ለቆ ወደ ሀዋሳ ከተማ አምርቶ ቀጥሎም በየመን ሊግ እና ሲዳማ ቡና ያሳለፈው ቢንያም በ2009 ወደ ቀድሞ ክለቡ ተመልሶ በአምበልነት በመምራት ወደ ፕሪምየር ሊግ እንዲመለስ ረድቷል።
ቢኒያም አድማሱ ወደ ሊጉ ቡድኑ በመቀላቀሉ የተሰማውን ስሜት፣ ስለ ውድድር ዓመቱ እና ስለ ቀጣይ የክለቡ እቅድ ለሶከር ኢትዮጵያ አስተያየቱን ሰጥቷል።
ወደ ሊጉ መቀላቀላቹ ምን ተሰማህ ?
በቅድሚያ እጅግ ደስ ብሎኛል። በጣም ደስ የሚል ነው፤ ቃላቶቼም በደስታ የሚወጡ ናቸው። የዛሬውም ጨዋታ ደስታዬን እጥፍ አድርጎታል፡፡
ከረጅም ጊዜያት በኋላ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ተመልሳችኋል። የውድድር ዘመኑ ጉዟችሁ ምን ይመስላል ?
በጣም ከባድ ነው። በተለያዩ ሜዳዎች ሄደህ ብዙ ችግሮች ይገጥሙሀል። ያን ሁሉ ፈተና አልፈን ለዚህ በቀተናል። በተለይ ቡድኑ ወጣቶቹን ከአንጋፋዎቹ ጋር አቀላቅሎ የተሰራ ስለነበረ የዛ ውጤት ነው። ግን በጣም ልፋት ያለው ውድድር አካሂደን በስተመጨረሻ ተሳክቶልን ወደ ሊጉ ገብተናል፡፡
ከዚህ ቀደም በደቡብ ፖሊስ ነበርክ። ከዛም በተለያዩ ክለቦች ተጫውተሀል። ላለፉት ዓመታት ከጫፍ እየደረሰ ቆይቶ አሁን ገብቶ ስታየው ምን ፈጠረብህ ?
ከቡድኑ ከ7 ዓመት በፊት ከወጣሁ እና ወደ ሌላ ቦታ ከሄድኩ በኋላ እየደረሰ እንደሚመለስ አመራሮቹ ነግረውኝ ነበር። ከዛ አስከፊ ነገር ለመውጣት ደግሞ ያለንን ሁሉ አሟጠን ስናወጣ ነበር፤ ደርሰን መመለስ እንደሌለብን ሁላችንም ተነጋግረን ስለነበር ያ አቅም እና ትምህርት ስለሆነን ያ ንግግራችን ውጤታማ ሆኖ እዚህ አድርሰነዋል ፡፡
ደቡብ ፖሊስን እንደ አንበልነትህ እንዴት አየኸው? ጥንካሬ እና ድክመቱስ?
ቡድኑ በጣም ጥሩ ነው፤ በተለይ በሜዳችን ጥሩ ሪከርድ አለን። ከሜዳችን ውጭ ትንሽ ደከም ያለ ውጤት ነው ያለን። በቡድናችን ያሉ ወጣቶች በጣም ደስ ይላሉ፤ ከኛ አንጋፋዎቹ ጋር ያለው ስብጥርም ውጤታችንን አስጠብቀን እስከ መጨረሻው እንድንቀጥል ረድቶናል። ጥንካሬያችን ሙሉ ለሙሉ ማለት ይቻላል ከግማሽ በላይ የአጥቂ ክፍላችን በርካታ ግብ የሚያስቆጥር በመሆኑ ይህ ጠንካራ ጎናችን ነው። ከፊት ያለው ጥንካሬ ቢሸፍናቸውም ለኔ የኃላ መስመራችንም ጥሩ ነው። በአጠቃላይ ካየሁት ግን ከፊት የተሻለ ነገር ስላለን ጠንካራ የሆነ ቡድን መገንባት አስችሎናል። ያም ደግሞ የተሻሉ ነጥቦችን እንድንይዝ አድርጎታል፤ በአጠቃላይ በቡድናችን የነበረን ህብረት ለዚህ አድርሶናል።
አሁን ሊጉን ተቀላቅላችዋል። ፕሪምየር ሊጉ ደግሞ የራሱ የሆነ ባህርይ አለው። ማደግ እንዳለ መውረድ አለ፤ የሚጠብቃችሁ አጭር የዝግጅት ጊዜ ከመሆኑ አንፃር ደቡብ ፖሊስ በቀጣይ ምን ማድረግ አለበት ትላለህ ?
እኔ አሁን ላይ ውሌ ቢያልቅም፤ ጥያቄውም ለአመራሮቹ ቢሆንም አሁን ላይ በደንብ መዘጋጀት ይኖርብናል። ልምድ ያላቸው ተጨማሪ ተጫዋቾችን ማምጣት እና ከወጣቶቹ ጋር ማቀናጀት ያስፈልጋል። ፕሪምየር ሊጉ በጣም ይከብዳል፤ ወጣቶችን እና ከታች የመጣውን ቡድን ብቻ ይዘህ የምትራመድበት አይደለም። በፕሪምየር ሊጉ ላይ ለመቆየት የግድ የተወሰኑ ተጫዋቾች መጨመር ይኖርባቸዋል።