አሰልጣኝ ግርማ ታደሰ ስለ ደቡብ ፖሊስ ወደ ፕሪምየር ሊግ ማደግ እና ቀጣይ ቆይታቸው ይናገራሉ

Read Time:2 Minute, 11 Second

ባለፈው የውድድር ዓመት መጋቢት መጀመሪያ ላይ ነበር ደቡብ ፖሊስን የተረከቡት። አስቀድመው ቡድኑን እንደያዙ ወደ ሊጉ ለመግባት ሳይሆን ቡድኑ ተፎካካሪ እንዲሆን በማድረግ በቀጣዩ ዓመት ግን በእርግጠኝነት ወደ ፕሪምየር ሊጉ እንደሚያሳድጉ ተናግረው የነበሩት አሰልጣኝ ግርማ  የተናገሩት ሰምሮላቸው ደቡብ ፖሊስን ከስምንት ዓመታት በኋላ ዳግም ወደ ፕሪምየር ሊጉ መልሰውታል። 

አሰልጣኝ ግርማ ታደሰ በ2007 ድሬዳዋ ላይ በተካሄደውና በያኔው ስያሜው የብሔራዊ ሊግ ማጠቃለያ ውድድር ላይ ሀደለያ ሆሳዕናን ይዘው ድሬ ዳዋ ከተማን ተከትሎ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ማሳደግ የቻሉ ሲሆን ዘንድሮ ደግሞ ደቡብ ፖሊስን እየመሩ ትላንት ድሬዳዋ ፖሊስን 3-0 በመርታት በ61 ነጥቦች ወደ ፕሪምየር ሊግ በማሳደግ ከአንድ ክለብ በላይ ወደ ፕሪምየር ሊግ ያሳደጉ አሰልጣኞችን ጎራ ተቀላቅለዋል። 

አሰልጣኝ ግርማ ከድሉ በኋላ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ ሲያደርጉ ስለ ውድድር ዓመቱ አስተያተት በመስጠት ጀምረዋል። “ዓመቱ እጅጉን ከባድ ነበር። ይህን ሁሉ አልፎ ለዚህ መብቃት አስደሳች ነው። የከፍተኛ ሊግ ውድድር በባህሪው እጅግ አድካሚ በመሆኑ ፅናትና ጥንካሬ ይጠይቃል። ክለቡ ላይ ምንም እንኳን በውስጡ አንዳንድ ችግሮች ቢኖሩበትም ያንን ሁሉ አልፈን እዚህ መድረሳችን ደስ ብሎኛል። በሊጉ ፈታኝ ዓመት ሊገጥመን እንደሚችል በመረዳት በጥንቃቄ ተጉዘን በሜዳችን መሸነፍ እንደሌለብን ስለተነጋገርን ሜዳችን ላይ የሰበሰብነው ነጥብ ለውጤታችን ትልቅ ቦታ አለው። ” በማለት በሜዳው ተጋጣሚዎቹን ለመርታት አለመቸገሩ ለውጤታማነታቸው ወሳኝ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ገልጸዋል። አሰልጣኙ በዘንድሮው የውድድር ዘመን ወደ ሊጉ መመለስ ቢችሉም ችግሮች እንዳሉም አልዘነጉም፡፡ “ቀላል የሚባል ውድድር የለም፤ ብዙ ነገሮችን ተቋቁመህ ነው እዚህ ልትደርስ የምትችለው። የሜዳ ጥራት ችግር፣ አንዳንድ ዳኞች የሚሰሩት ስህተት፣ ከሜዳህ ውጭ የደጋፊዎች ጫና እና በቡድኑ ውስጥ ደግሞ የፋይናንስ ችግሮች መኖራቸው በክለቡ ላይ የተጋረጡ ፈታኝ ጉዳዮች ነበሩ።”

ከአንድ በላይ ክለብን ወደ ሊጉ ከቀላቀሉ አሰልጣኞች ዝርዝር ውስጥ መግባት የቻሉት አሰልጣኝ ግርማ የተለየ ሚስጥር ይኖር ይሆን ብለን ጥያቄን አነሳን። “እኔ ይህ ነው ብዬ ማነሳው ሚስጥር የለም። እንደ አንድ አሰልጣኝ አንድ ቡድን ምን ይፈልጋል ብለን ከተነሳን ማሳካት እንችላለን። እኔም ያ ነገር ረድቶኝ እንጂ የተለየ የሚነሳ ያለ አይመስለኝም” ሲሉም መልሰዋል።

አሰልጣኙ ቡድኑን ይዘው ወደ ሊጉ ማደግ ቢችሉም ከአሁን በኋላ ፈታኝ ጊዜያት በፕሪምየር ሊጉ እንደሚጠብቃቸው አልሸሸጉም። “ፕሪምየር ሊጉ የራሱ ቅርፅ አለው። ያን ቅርፅ ጠብቆ መጓዝ የክለቡ ትልቅ ፈተና ይሆናል፡፡ እኔ በበኩሌ ኃላፊነቴን ተወጥቻለሁ፤ ከአሁን በኃላ በተለያዩ በጎደሉ ቦታዎች ላይ ተጫዋቾች ማካተት እና በሊጉ ለመቆየት ከአሁኑ ስራዎችን መስራት ጥሩ ይሆናል ብዬ አምናለሁ” ሲሉ አብራርተዋል። 

ከደቡብ ፖሊስ ጋር ውላቸው የተጠናቀቀውና ከባህር ዳር ከተማ ጋር ከሚደረገው ጨዋታ በኋላ ከክለቡ ጋር ስለሚቀጥሉበት ሁኔታ እርግጠኛ መሆን ያልቻሉት አሰልጣኝ ግርማ ስለ ቆይታቸው አጠራጣሪነት የሚከተለውን ብለዋል። “አሁን ላይ ቡድኑ እንደሌሎቹ ክለቦች በሁለት እግር እንዲቆም ፋይናንሱ በሚገባ መጠናከር አለበት። እኔ በሀዲያ ሆሳዕና እያለው በዚት ዙርያ ተጎድቻለሁ፤ ከክለቡ ስለያይም ከገንዘብ ጋር የተያያዙ ጉዳዮቹ ነበሩ። ዋናው ስራዬን በአግባቡ ከተወጣው እንደማንኛውም ባለሙያ መጠቀም አለብኝ። ቡድኑን ወደ ፕሪምየር ሊግ ማሳደግ ብችልም ልቀጥልም ላልቀጥልሞ የምችልበት ምክንያት ይኖረኛል። እስከ አሁን በውል ማራዘም ዙርያ ክለቡ ያለኝ ነገር የለም። ከአሁን በኋላ ክለቡ ምን አቅዶም እንደሆነ አልሰማሁም። በኔ ዙሪያ ምንም አልተነጋገርንም፤ እኔ ወደ ክለቡ ስመጣ በውስጥ ስምምነቶች ነበሩ። አሁን ላይ ግን ምን እንደታሰበ አላውቅም።” በማለት ቋጭተዋል።

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
ያጋሩ
error: Content is protected !!