ከሀዋሳ ከተማ አንስቶ በደደቢት እና ብሔራዊ ቡድን በግብ አስቆጣሪነት ስሟ ቀድሞ የሚነሳው አጥቂዋ ሎዛ አበራ እና የቀድሞዋ የብሔራዊ ቡድን አምበል እንዲሁም በዳሽን ቢራ፣ አአ ከተማ እና በቅዱስ ጊዮርጊስ የምናውቃት አማካዩዋ ቱቱ በላይ ወደ ስዊድን ካመሩ ሁለት ወራት ሊያስቆጥሩ ተቃርበዋል። በወኪላቸው አማካኝነት በተመቻቸላቸው ዕድል ምክንያት ሰኔ 25 ወደ ስዊድን አቅንተው በትልልቆቹ ክለቦች ፒቲያ እና ሮስጋርድ የሙከራ ጊዜ እንደሚኖራቸው የተነገረ ቢሆንም ያ ሳይሆን በመቅረቱ የሁለተኛ ዲቪዚዮን ቡድን በሆነው ከንግስባካ ኤፍሲ የሙከራ ጊዜን በማሳለፍ ላይ ይገኛሉ።
ክለቡ ሁለቱን ተጫዋቾች ባሳዩት እንቅስቃሴ መነሻነት ለማስፈረም ጥረት ቢያደርግም የአውሮፓዊያን የዝውውር መስኮት በመጠናቀቁ ሎዛ እና ቱቱ እስከ ጥቅምት ወር በዛው ይቆያሉ ተብሏል። እስከዛው ድረስ በዋናው ከንግስባካ ቡድን የነጥብ ጨዋታ ማድረግ የማይችሉ በመሆኑ ከ19 ዓመት ቡድኑ ውስጥ ተካተው መጫወት ጀምረዋል። የክለቡ ከ19 አመት ቡድን የውድድር ዘመኑ ከተጀመረ ወዲህ ሁለት ጨዋታዎችን ያደረገ ሲሆን አንዱን 4-0 ሲያሸንፉ ሁለተኛውን ጨዋታ ደግሞ 4-2 ተሸንፎ በሁለተኛነት ደረጃ ላይ ይገኛል። በነዚህ ጨዋታ ላይ ሁለቱም ተጫዋቾች ተሰልፈው መጫወት የቻሉ ሲሆን በመጀመሪያው ጨዋታ አንድ አንድ ጎል አስቆጥረዋል። በሁለተኛው (4-2 በተሸነፉበት) ጨዋታ ደግሞ ሁለቱንም ጎሎች ሎዛ አበራ ከመረብ አሳርፋለች ፡፡
ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ ያደረጉት ሁለቱ ተጫዋቾች እሰከ አሁን በሙከራ ላይ እንጂ በክለቡ በይፋ አለመፈረማቸው እና በክለቡ የክፍያ አገልግሎት እንዳልጀመሩ በኤጀንታቸው በኩል በሚደረግላቸው ድጋፍ በስዊድን እያሳለፉ እንደሚገኙ ገልፀዋል፡፡ እስከ ጥቅምት ወር ድረስ በክለቡ እስከሚፈረሙ ድረስ በክለቡ ከመጫወት ውጭ ጥቅሞችን በተፈለገው ልክ ባያገኙም በክለቡ እያሳለፉ ያለው ሙከራ እጅግ ደስተኛ መሆናቸውን በተለይ ሎዛ አበራ ገልፃለች፡፡
የከንግስባካ ዋናው ቡድን ሊጠናቀቅ 9 ሳምንታት በቀሩት የስዊድን ኤሊቴታን (ሁለተኛ ዲቪዝየን) ሁለተኛ ደረጀ ላይ የሚገኝ ሲሆን ደረጃውን አስጠብቆ ከጨረሰ በ2019 ወደ ዳማስቬሊስካን (ዋናው ሊግ) የሚያድግ ይሆናል። ቱቱ እና ሎዛ በጥቅምት ወር የሚፈርሙ ከሆነም ከአለማችን ታላላቅ የሴት ሊጎች አንዱ በሆነው የስዊድን ሊግ ልንመለከታቸው እንችላለን።