በቅርቡ ለሙከራ ወደ ሰርቢያ ያመራው ከነዓን ማርክነህ የሙከራ ጊዜውን አጠናቆ ወደ ሀገሩ ስለተመለሰበት ጉዳይ ይናገራል፡፡
በሊጉ በተለይ በዘንድሮው ዓመት በአዳማ ከተማ ጥሩ የውድድር ጊዜን ያሳለፈው የአጥቂ አማካዩ ከንዓን ነሀሴ 14 ዕለተ ዕሁድ ወደ ሰርቢያ ማምራቱ ይታወሳል። አስቀድሞ በአዲስ አበባ ከተማ በኋላ ላይ ደግሞ በአዳማ ከተማ ድንቅ ብቃቱን ያሳየው ተጫዋቹ በሰርቢያው ኃያል ክለብ ሬድስታር ቤልግሬድ እህት ክለብ ዛራኮቭ ቤልግሬድ አጭር የሙከራ ጊዜን አሳልፎ ወደ ሀገሩ ተመልሷል። ምንም እንኳን ዝውውሩ የአውሮፓዊያን የዝውውር ጊዜ በመጠናቀቁ እንዲሁም ክለቡ ረጅም ጊዜ ወስዶ ተጨዋቹን መመልከት ይገባው የነበረ በመሆኑ ባይሳካም ተጨዋቹ በቀጣይ ጊዜያት ወደ አውሮፓ ሄዶ የመጫወት ህልሙ ዕውን ሊሆን እንደሚችል ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረገው ቆይታ እንዲህ ሲል ገልጿል። ” የሙከራ ጊዜዬ አጭር ቢሆንም ጥሩ ነገር አለው። ትንሽ ለሙከራ የሄድኩበት ወቅት የዝውውር ጊዜው ሊያልቅ ሁለት ቀናት ብቻ ሲቀሩት መሆኑ ክለቡ በፈለገው ሰዓት ተገኝቼሌት እንዲመለከተኝ አልሆነም። እኔም አስቤው እንደሄድኩት ሊሆንልኝ አልቻለም። የክለቡ አመራሮችም በቀጣዩ ዓመት ግማሽ ላይ መጥተህ ድጋሜ እናይሃለን አሁን ላይ ጊዜው አጭር ነው የሚል ምላሽ ሰጥተውኛል”
ከሀገራችን ተጨዋቾች በተለየ መልኩ የራሱን የጨዋታ እንቅስቃሴ በማስቀረፅ ይህን አጋጣሚ ሊያገኝ የቻለው አማካዩ በቀጣይ ግን ተረጋግቶ በማሰብ ዳግም ሙከራ ስለማድረግ ያስባል። ” ገና በጊዜ ሄጄ ቢሆን አሳካው ነበር። ቢያንስ ግን ለቀጣዩ ዓመት አስብበታለሁ ብያለሁ። እዚህ ከመጣሁ በኃላ ያለውን ነገር አስተካክዬ የቤተሰቦቼም ጉዳይ ስላለ ነገሮችን ከጨረስኩ በኃላ ተመልሼ በመሄድ ቻሌንጁን በሚገባ ተቋቁሜ ተመልሼ ህልሜን ማሳካት እፈልጋለው” በማለት ሀሳቡን አጠቃሏል። ቀሪ የውል ኮንትራት ከአዳማ ጋር ያለው ተጫዋቹ እስከ ግማሽ ዓመት ጥር ድረስ በክለቡ እየተጫወተ ከቆየ በኃላ ዳግም ለሙከራ የሚጓዝ ይሆናል።