ኢትዮጵያ መድን ከ17 ዓመት ብሔራዊ ቡድኑን ለመረከብ ጠየቀ

ወደ አፍሪካ ዋንጫው ማለፍ ባይችሉም ጥሩ ጉዞ አድርገው የተመለሱት ቀይ ቀበሮዎቹ ዕጣ ፈንታ ምን ሊሆን ይችላል ? ለሚለው ጥያቄ ኢትዮጵያ መድን መልስ አለኝ ይላል።

ከነሃሴ 5-20 በታንዛንያ ሲካሄድ በነበረው የሴካፋ ዞን ከ17 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ተሳትፎ የነበረው እና በፍፃሜው ጨዋታ በዩጋንዳ 3-1 ተረቶ ውድድሩ ላይ የመድረስ አላማን ያጣው የኢትዮጽያ ከ17 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን ከትላንት በስቲያ አዲስ አበባ መግባቱ ይታወሳል። ቀይ ቀበሮዎቹ ወደ ሀገራቸው ከተመለሱ በኋላ በእግር ኳስ ፌደሬሽኑ መልካም አቀባበል የተደረገላቸው ሲሆን የማበረታቻ ሽልማትም ተበርክቶላቸዋል። በሽልማቱ ወቅት ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ጂራ የታዳጊዎቹን ተስፋ ለማስቀጠል ፌደሬሽኑ የቤት ስራዎች እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

ይህንን ንግግር የሰሙ የሚመስሉት የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ስፖርት ክለብ አመራሮች ሙሉ የቡድኑን ተጨዋቾች ወደ ክለባቸው በሃላፊነት ለማስገባት እና የተጨዋቾቹን ተስፋ ለማስቀጠል ለፌደሬሽኑ ጥያቄ ማስገባታቸው ተሰምቷል። ይህንን ተከትሎም የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ስፖርት ክለብ ስራ አስኪያጅ አቶ አበባው ጉዳዩን እንዴት እንዳሰቡበት በተለይም ለሶከር ኢትዮጵያ ያስረዱ ” ይህንን ያሰብነው በቅንነት ነው።ሀገራዊ ግዴታ አለብን። እነዚህ ልጆች ስኬታማ ጊዜ አሳልፈው ነው የመጡት ነገር ግን ይህንን ስኬታማ ነገር እንደ ሀገር ማስቀጠል ይኖርብናል። ስለዚህ እንደ ክለብ ግዴታችንን ለመወጣት ነው ይህንን ያሰብነው። አሁን ያሉት ልጆች ወደ ተለያዩ ቦታዎች መበተን የለባቸውም ቢቻል በአንድ ቦታ ሆነው ስራዎች መስራት ይኖርባቸዋል ብለን እናምናለን። ያሰብነውም ተጨዋቾቹ ለተስፋ ቡድናችን እንደ ግብዓት እንዲሆኑ ነው። ነገር ግን ዋና ዓላማችን የተጨዋቾቹን ተስፋ ማስቀጠል ላይ ነው።”ብለዋል። ስራ አስኪያጁ ክለቡ ተጨዋቾቹን ሲረከብ ምን ዓይነት ነገሮችን እንዳዘጋጀ ተጠይቀው ሲመልሱ ተጨዋቾቹ በቂ ክፍያ እንደሚያገኙ ከተናገሩ በኋላ ” ወደ እኛ ከመጡ በኋላ ምቹ ሁኔታዎችን እንዲያገኙ ስራዎችን እንሰራለን። ለልጆቹ በቂ የማደሪያ ስፍራ እናዘጋጃለን በተጨማሪም ከቤተሰብ ርቀው እንደመምጣታቸው የምግብ እና የትምህርት ወጪያቸውን ድርጅቱ እንዲሸፍን እናደርጋለን።” በማለት አስረድተዋል።

የክለቡ መልካም ሀሳብ እንዳለ ሆኖ ሁሉም ተጨዋቾች በተለያዩ ክለቦች ስር በመሆናቸው ክለቡ የእነረከባቸው ጥያቄውን ለፌዴሬሽኑ ማቅረቡ እንዲሁም ተጨዋቾቹን በራሱ የምልመላ መንገድ ለማምጣት አለማሰቡ አነጋጋሪ ሆኗል። ሆኖም አቶ አበባው  ክለባቸው ሁለቱን ነጥቦች በምን መልኩ እንደሚመለከታቸው እንዲህ በማለት ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተዋል። ” ተጨዋቾቹ የክለቦች ንብረቶች እንደሆኑ እናውቃለን። ነገር ግን ለዘለቄታዊ የሃገር ጥቅም ሲባል አንድ ላይ ቢሆኑ እና ልምምዶችን ቢሰሩ መልካም ነው። ይህንን ደግሞ ለማድረግ ፌደሬሽኑ በቀጣይ በሚያስቀምጠው አቅጣጫ ነገሮችን ለማከናወን እንሞክራለን። በአሁኑ ሰዓት የራሳችን የሆነ የተስፋ ቡድን አለን ነገር ግን እነዚህን ልጆች ለመያዝ ያሰብነው ያለንን ቡድን ከእነዚህ ታዳጊዎች ጋር በማጣመር ጥሩ የተስፋ ቡድን ለመፍጠር ነው። ታዳጊዎችንም መመልመል አሁንም አላቆምንም። እየመለመልን ነው። ጥሩ ልጆችንም አግኝተናል። ነገር ግን በታዳጊዎች ላይ ሰፋፊ ስራዎችን ለመስራት ስላሰብን ዕይታችንን ማስፋት እንዳለብን በማመናችን ነው ሀሳቡን ያመጣነው።” ብለዋል።

ያጋሩ