ድሬዳዋ ከተማ የተጫዋቾችን ውል ሲያድስ የሙከራ ዕድልንም አመቻችቷል

የክረምት የዝውውር እንቅስቃሴውን በፍቃዱ ደነቀ ጀምሮ ትላንት ግብ ጠባቂው ፍሬው ጌታሁንን ያስፈረመው እንዲሁም አራት ተጫዋቾችን ከ20 ዓመት ቡድኑ ያሳደገው ድሬዳዋ ከተማ ዛሬ ደግሞ የሶስት ተጫዋቾች ውል ሲያድስ ለ7 ተጫዋቾች የሙከራ ዕድልን እንደሚሰጥ ታውቋል።

በግራ መስመር ተከላካይ እና አማካይ ስፍራ ላይ የሚሰለፈው ወሰኑ ማዜ፣ በመጨረሻው ጨዋታ ሁለት ግቦች አስቆጥሮ ክለቡ በሊጉ እንዲቆይ የረዳው ዳኛቸው በቀለ እና ለረጅም ጊዜያት በምስራቁ ክለብ የቆየው ረመዳን ናስር ለተጨማሪ ሁለት ዓመታት በድሬዳዋ ለመቆየት ውላቸውን ያራዘሙ ተጫዋቾች ሆነዋል። ድሬዎች ከዚህ ቀደም የተከላካይ መስመር ተጫዋቹ በረከት ሳሙኤልን ውል ማራዘሙ ይታወሳል።

በተያያዘ ድሬዳዋ በቀጣይ ወደ ዝግጅት ሲገባ ለአራት የውጭ እና ለሶስት የሀገር ውስጥ በድምሩ ለ7 ተጫዋቾች የሙከራ ጊዜን እንዳመቻቸ ክለቡ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልጿል፡፡

አሰልጣኝ ዮሀንስ ሳህሌ ከአዲሱ የክለቡ ፕሬዝዳንት አቶ ሻኪር እና የከተማው ከንቲባ አቶ ኢብራሒም ዑስማን ጋር ትላንት ትውውቅ ያደረጉ ሲሆን ተጨማሪ አዳዲስ ተጫዋች ወደ ክለቡ ለመቀላቀል ማሰቡም ጭምር ተነግሯል።