ከ20 አመት ሴቶች ብሄራዊ ቡድን ዝግጅቱን እያደረገ ነው

የኢትዮጵያ ከ20 አመት በታች ብሄራዊ ቡድን ከቡርኪና ፋሶ አቻቸው ጋር ለዓለም ከ20 አመት በታች ዋንጫ 2ኛ ዙር ማጣርያ የሚያደርጉትን ዝግጅት በባህርዳር ማድረጋቸውን ቀጥለዋል፡፡
ቡድኑ ከአነጋጋሪው የበረራ ችግር በኋላ ባህርዳር ላይ ካሜሩንን 2-1 በማሸነፍ በድምር የ2-1 ውጤት ወደ ተከታዩ የማጣርያ ዙር ካለፈ በኋላ የአንድ ወር እረፍት ተሰጥቶት የቆየ ሲሆን ከእረፍት መልስ ለአንድ ወር ለሚጠጋ ጊዜ በባህርዳር ዝግጅቱን ሲያደርግ ቆይቷል፡፡
በቀድሞው የደደቢት ሴቶች ቡድን አሰልጣኝ አስራት አባተ የሚመራው ከ20 አመት በታች ቡድኑ ለቡርኪናፋሶው ጨዋታ ዝግጅት በቀን 2 ጊዜ ጠንከራ ልምድ ሲያደርግ ቆይቶ ያለፉትን ጥቂት ቀናት በቀን አንድ ጊዜ ልምምድ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡
ከትላንት በስትያ በቡርኪናፋሶው ጨዋታ ቋሚ ተሰላፊ ይሆናሉ ተብለው የሚጠበቁት እና ተጠባባቂ እንደሚሆኑ የሚጠበቁት እርስ በእርስ ጨዋታ አድርገው ተጠባባቂ ይሆናሉ የተባሉት 5-3 አሸንፈዋል፡፡ በተከላካይ መስመሩ ላይ ድክመቶች ያስተዋሉት አሰልጣኝ አስራት አባተም ያላቸውን ጊዜ ተጠቅመው የማስተካከል ስራ እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡
ከ20 አመት በታች ቡድኑ የባህርዳር ዝግጅቱን አጠናቆ ሰኞ ወደ አዲስ አበባ የሚመጡ ሲሆን ወደ ኡጋዱጉ የሚጓዙበትን ቀን ያማከለ ልምምድ በአዲስ አበባ እንደሚሰሩ አሰልጣኝ አስራት አባተ ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል፡፡‹‹ በተጫዋቾቼ ውስጥ ያለው የማሸነፍ ፍላጎት እና በመካከላቸው ያለው የቡድን መንፈስ ጥሩ ነው፡፡ ጨዋታውን አሸንፈን ለመመለስ እየተዘጋጀን ነው፡፡እስካሁን ባለው ሁኔታ በበድኔ ውስጥ ጉዳት ያጋጠመው ተጫዋች የለም፡፡ ሰኞ በባህርዳር ቀላል ልምድ ሰርተን አመሻሹ ላይ አዲስ አበባ እገባለን ወደ ቡርኪና ፋሶ እሮብ ወይም ሀሙስ ጉዞ እናደርጋለን፡፡ ሀሙስ የምንጓዝ ከሆነ ማክሰኞ እና ረቡእ በአበበ ቢቂላ ስታድየም ቀላል ልምምድ እንሰራለን፡፡ ›› ብለዋል፡፡የአጭር ጊዜ የብሄራዊ ቡድን ኮንትራታቸው የተጠናቀቀው አሰልጣኝ አስራት አባተ በቀጣይ ቀናት ተጨማሪ ኮንትራት እንደሚቀርብላቸው ተስፋ አድርገዋል፡፡

‹‹ ከ20 አመት በታች ቡድኑ ጋር የገባሁት ውል የተጠናቀቀው ነሃሴ 30 ቢሆንም ያለፉትን ቀናት ካለኮንትራት በታማኝነት ሰርቻለው፡፡ ምናልባትም ለልምምድ ባህርዳር በመሰንበታችን ለድርድር አመቺ ሳይሆን ቀርቶ ሊሆን ይችላል፡፡ ሰኞ አዲስ አበባ ከገባው በኋላ ፌዴሬሽኑ ውሌን ያድሳል ብዬ እጠብቃለሁ፡፡ ››

የኢትዮጵያ ከ20 አመት በታች ሴቶች ብሄራዊ ቡድን ከቡርኪናፋሶ ከ20 አመት ሴቶች ብሄራዊ ቡድን ጋር የሚያደርጉት ጨዋታ ልክ የዛሬ ሳምንት መስከረም 15 ቀን 2008 ይደረጋል፡፡

ያጋሩ