ለ2019 የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታ ይረዳው ዘንድ ከቡሩንዲ ብሔራዊ ቡድን ጋር ዛሬ በሀዋሳ አለም አቀፍ ስታዲየም የወዳጅነት ጨዋታውን ያደረገው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን 1-1 በሆነ ውጤት አጠናቋል፡፡
በትራንስፖርት ጉዳዮች ምክንያት የብሩንዲ ብሔራዊ ቡድን በጥቅሉ 16 የልዑካን አባላትን ብቻ ይዞ ለጨዋታው የቀረበ ሲሆን ጨዋታው በተለይ የመጀመርያው አጋማሽ አሰልቺ ገፅታ የነበረው ነበር። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ኳስን ይዞ በመጫወቱ የተሻሉ ሲሆኑ ብሩንዲዎች ረጃጅም ኳስ ላይ ትኩረት አድርገው ተጫውተዋል።
ተደጋጋሚ ጉዳቶች በተስተዋሉበት በዚህ ጨዋታ ሳላሀዲን በርጊቾ ገና በ10ኛው ደቂቃ በሙጂብ ቃሲም ተቀይሮ ወጥቷል። በአማካይ እና በቡሩንዲ የሜዳ አጋማሽ ቀኝ መስመር አመዝነው መንቀሳቀስ የቻሉት ዋልያዎቹ ከእንቅስቃሴ በዘለለ ይህ ነው ሊባል የሚችል ሙከራን ማድረግ ተቸግረው ታይተዋል። 18ኛ ደቂቃ ላይ ጌታነህ ከበደ ከቅጣት ምት፣ 29ኛው ደቂቃ ላይ አህመድ ረሺድ ከግራ መስመር እየገፋ ገብቶ መሬት ለመሬት አክርሮ የላካትን ኳስ ዳዋ ሆቴሳ ሞክሮ ወደ ወጪ የወጣበት እንዲሁም 40ኛው ደቂቃ ላይ ጌታነህ ከበደ በግራ በኩል አሻምቶ ዳዋ በግንባሩ ገጭቶ የወጣበት ሊጠቀሱ የሚችሉ ሙከራዎች ናቸው። በመጀመሪያው አጋማሽ ብሩንዲዎች የሚጠቀስ ሙከራ ሳያደርጉ ያለ ግብ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
በሁለተኛው አጋማሽ የተሻሉ ሆነው መቅረብ የቻሉት ዋልያዎቹ በተለይ በጌታነህ ከበደ እና ተቀይሮ በገባው አቤል ያለው አማካኝነት እጅግ በርካታ የግብ አጋጣሚን መፍጠር ችለዋል። አቤል ሁለተኛው አጋማሽ እንደተጀመረ ከግብ ጠባቂው ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ መጠቀም ሳይችል የቀረው ኳስ ዋልያዎቹን ቀዳሚ ሊያደርግ የሚችል አጋጣሚ ነበር። 58ኛ ደቂቃ ላይ ተከላካዩ ፒስቺሚራና ዴቪድ በረጅሙ የላከለትን ኳስ በአግባቡ ተቆጣጥሮ አጥቂው ሻባኒ ሁሴን በማስቆጠር ቡሩንዲን ቀዳሚ አድርጓል። ግቧ ስትቆጠር ሻባኒ በተከላካዩ አህመድ ረሺድ ላይ ጥፋት ተፈፅሞበት የተቆጠረች ነበረች በማለት የተቃውሞ ድምፅ በስቴዲየሙ ተሰምቷል። አህመድ ረሺድም ከባድ ጉዳትን ያስተናገደ ይመስል የነበረ ቢሆንም በተደረገለት ህክምና ተነስቶ ተቀይሮ ሊወጣ ተገዷል።
የአቻነት ግብ ለማስቆጠር ተደጋጋሚ ጥቃት ሲፈፅሙ የታዩት ዋልያዎቹ በርካታ የግብ እድሎችን መፍጠር ችለዋል። 76ኛ ደቂቃ ላይም ዳዋ ሆቴሳ በአግባቡ ያሳለፈለትን ኳስ አምበሉ ጌታነህ ከበደ አስቆጥሮ ኢትዮጵያን አቻ ማድረግ ችሏል። ጨዋታውም ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠርበት 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።