ሁለት የሴራሊዮን ወሳኝ ተጫዋቾች በጉዳት ከቡድኑ ውጪ ሆነዋል

የሴራሊዮን ብሔራዊ ቡድን በ2019ኙ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ከኢትዮጵያ ጋር ላለበት ቀጣይ ጨዋታ ዝግጅት እያደረገ ይገኛል። አሠልጣኝ ጆን ኪስተር ለ35 ተጫዋቾች ጥሪ አድርገው በመገምገም በመጨረሻም ወደ ሐዋሳ ይዘው የሚጓዙትን 23 ተጫዋቾች ይፋ አድርገው ነበር። ነገር ግን ጥሪ የደረሳቸው 2 ተጫዋቾች በጉዳት ምክኒያት ራሳቸውን ከቡድኑ ሲያገልሉ የአምበሉ ኡማሩ ባንጉራ መሰለፍም አጠራጣሪ ሆኗል።

ከቡድኑ ውጪ የሆኑት ተጫዋቾች ለእንግሊዙ ኮቨንትሪ ሲቲ የሚጫወተው አጥቂ አማዱ ባካዮኮ እና የኢንዶኔዥያው ፒኤስአይኤስ አማካይ ኢብራሂም ኮንቴህ ናቸው። አሠልጣኙ ከዚህ ቀደም በቡድኑ ተካተው የተቀነሱ ተጫዋቾችን በመጥራት በሁለቱ ተጫዋቾች ጉዳት ምክንያት የተፈጠረውን ክፍተት ለመሙላት እንደሚሞክሩ ሲጠበቅ ምናልባትም ለዴንማርኩ ኤጂኤፍ አረስ የሚጫወተው ሙስጣፋ ቡንዱ ለመጀመሪያ ጊዜ በቡድኑ ውስጥ ሊካተት ይችላል ተብሏል።

የአምበሉ ኡማሩ ባንጉራ የጤንነት ሁኔታ ደግሞ ለሴራሊዮን ብሔራዊ ቡድን ሌላ ራስ ምታት ሆኗል። ለስዊዘርላንዱ ኤፍሲ ዙሪክ የሚጫወተው የ30 ዓመት አማካይ ከጉዳት መልስ ቡድኑ ከባሴል ጋር አቻ በተለያየበት ጨዋታ ሙሉ 90 ደቂቃ ተሰልፎ የተጫወተ ሲሆን ይህም ጉዳቱ እንዲያገረሽ እንዳደረገበት እና የክለቡ የህክምና ቡድንም ለብሔራዊ ቡድኑ እንዲጫወት እንደማይፈቅድለት ገልጿል።

“ወደ ኢትዮጵያ እንደምሄድ እርግጠኛ አይደለሁም። ከጉዳት መልስ ከባሴል ጋር ከተጫወትኩኝ በኋላበቀጣዩ ቀን ቀኝ እግሬ ላይ ህመም ተሰምቶኛል፤ በዚህም ምክንያት የሊግ ጨዋታ አምልጦኛል። አሁንም በክለቡ የህክምና ቡድን ክትትል እየተደረገልኝ ነው፤” ሲል የጉዳቱን ሁኔታ ለፉትቦል ሴራሊዮን ተናግሯል።

የ2019 አፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ምድብ 6 ሁለተኛ ጨዋታዎች ጳጉሜ 4 ቀን ሲደረጉ ኢትዮጵያ ሴራሊዮንን፣ ኬንያ ደግሞ ጋናን ያስተናግዳሉ። ምድቡን ጋና በ3 ነጥብ እና 5 የግብ ክፍያ ስትመራ ሴራሊዮን በተመሳሳይ ነጥብ በግብ ክፍያ ተበልጣ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። ኬንያ ያለምንም ነጥብ በአንድ የግብ ዕዳ ሶስተኛ፤ ዋሊያዎቹ ደግሞ ያለ ነጥብ በ5 የግብ ዕዳ የምድቡ ግርጌ ላይ ይገኛሉ።