ወደ ከፍተኛው ሊግ የወረደው ኢትዮ ኤሌክትሪክ አሰልጣኞችን እና ቴክኒክ ዳይሪክተሮችን በመምረጥ እስከ ነገ ድረስ ሪፖርት እንዲያደርጉ አሳስቧል።
በሁለቱም ፆታዎች በውድድር ላይ የነበሩት ቡድኖቹ በሙሉ ዝቅተኛ ውጤት ያስመዘገቡበት እንዲሁም ዋናዎቹ ቡድኖቹ ከመጀመሪያዎቹ ሊጎች የወረዱበት ኢትዮ ኤሌክትሪክ የማሻሻያ እርምጃዎችን እየወሰደ ነው። ከዚህም ውስጥ አመራሩን እንደ አዲስ በማዋቀር የቦርድ አባላትን መሰየሙ የሚታወስ ነው። ከአመራሮቹ ባለፈም ከዋናዎቹ ቡድኖቹ ጀምሮ እስከ 15 ዓመት በታች ቡድኖቹ ድረስ ይዘው የሚቀጥሉ በክለቡ ውስጥ ተጫውተው እንዲሁም የተለያዩ ኃላፊነቶችን ተወጥተው ያለፉ ግለሰቦችን ወደ አሰልጣኝነቱ አምጥቷል።
የቀድሞው የክለቡ ታሪካዊ ተጫዋች እና በ1990 የፕሪምየር ሊግ ኮከብ ተጫዋች የነበረው አንዋር ያሲን የክለቡ ዋና አሰልጣኝ ሆኖ ተሹሟል። በቅርብ ዓመታት ወደ አሰልጣኝነት ብቅ ያለው አንዋር በኢትዮጵያ ቡና እና አአ ከተማ ረዳት አሰልጣኝ ሆኖ ሰርቷል።
እየሩሳሌም ነጋሽ የሴቶች ቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ሆናለች። እየሩሳሌም እስከ ዓመቱ መጨረሻ ድረስ ኢትዮጵያ ቡናን ስታሰለጥን መቆየቷ ይታወሳል። መስፍን ሺበሺ እና ለማ ደበሌ የወንዶቹ ቡድን ምክትሎች ተደርገው ሲመረጡ አቶ ተስፋዬ ዘርጋው እና ጉልላት ፍርዴ በቴክኒክ ዳይሪክተርነት ሾሟል።
ክለቡ ከ20 ዓመት ፣ ከ17 ዓመት ፣ እና ከ15 ዓመት በታች ቡድኖቹንም አዲስ አሰልጣኝ የሾመላቸው ሲሆን ኃይሉ አድማሱ (ቻይና)፣ ዳንኤል የሻው እና ናርዶስ ደምሴ በቅደም ተከተል የክለቦቹ አሰልጣኝ ሆነዋል።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ ዛሬ በለጠፈው ማስታወቂያ ባለሙያዎቹ እስከ ነገ ድረስ በክለቡ ፅህፈት ቤት ተገኝተው ሪፖርት እንዲያደርጉ አሳስቧል። በቀጣይም በዚህ ሳምንት መጨረሻ ተሿሚዎቹ ከደጋፊው ጋር የሚተዋወቁበት ሥነ ስርዓት እንደሚካሄድ ይጠበቃል።