በሚካኤል ለገሰ እና ቴዎድሮስ ታከለ
በሁለት ምድብ ተከፍሎ ሲካሄድ የቆየው የ2010 የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ውድድር የሁለቱ ምድብ የበላዮች የውድድሩን ዋንጫ ለማንሳት አዳማ ላይ ነገ ይፋለማሉ። ባህርዳር ከተማ የምድብ ሀ ደቡብ ፖሊስ ደግሞ የምድብ ለ አሸናፊ ሆነው ለፍፃሜው የደረሱ ሲሆን ሁለቱም ቡድኖች በዓመቱ ካሳዩት ወጥ እና ጠንካራ እንቅስቃሴ አንፃር የነገው ጨዋታ ይጠበቃል።
በ27ኛ ሳምንት በተደረገ ጨዋታ ባህር ዳር ከተማ ከሜዳው ውጪ ኢትዮጵያ መድንን 2ለ1 በመርታት በአጠቃላይ 65 ነጥቦችን በመሰብሰብ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሊጉ ማደጉን ሲያረጋግጥ ከስምንት የውድድር ዓመታት በኃላ ወደ ሊጉ ዳግም የተመለሰው ደቡብ ፓሊስ ደግሞ በ30ኛ ሳምንት ጨዋታ ድሬዳዋ ፖሊስን በሜዳው አስተናግዶ 3ለ0 በማሸነፍ ነው ተከታዮቹን ጅማ አባ ቡና እና ሀላባ ከተማን በ2 ነጥቦች በልጦ በአጠቃላይ በ61 ነጥቦች በመያዝ ሊጉን መቀላቀሉን ያረጋገጠው።
ሁለቱም ቡድኖች የሚከተሉት የጨዋታ ባህሪ የመመሳሰሉ ጉዳይ ጨዋታው ምን መልክ ይኖረዋል የሚለው እንዲጠበቅ የሚያደርገው ነው። በአሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው የሚመሩት ባህር ዳሮች በዓመቱ ውድድር ኳስን ተቆጣጥሮ በመጫወት እና የሜዳውን የጎንዮሽ ስፋት ለመጠቀም ሜዳውን ለጥጦ በመጫወት ውጤታማ ጊዜ አሳልፈዋል።
በስብስቡ በርካታ ተጨዋቾችን በመያዙ የተለያዩ አማራጮችን ሲጠቀም የነበረው ቡድኑ ለተጋጣሚዎቹ ተገማች አለመሆኑ በአመቱ ጥሩ ጊዜ እንዲያሳልፍ የጠቀመው የሚመስል ሲሆን በነገውም ጨዋታ ይህ ያለመገመት ባህሪው ለደቡብ ፖሊሶች አስቸጋሪ ሊሆን እንደሚችል ይታመናል።
በአሰልጣኝ ግርማ ታደሰ የሚመሩት ደቡብ ፖሊሶች ደግሞ እንደ ተጋጣሚያቸው ባህር ዳር ሁሉ ኳስ በመቆጣጠር በኩል የላቁ ሲሆኑ በተለይ ከሚጫወቱበት የሃዋሳ የሰው ሰራሽ ሜዳ አንፃር አጨዋወታቸውን የቃኙ ይመስላል። በሀምበሪቾ ከደረሰባቸው ሽንፈት እና ከሀላባ ከተማ ጋር አቻ ከተለያየበት ጨዋታ ውጪ ሁሉንም የሜዳቸው ጨዋታዎች መርታታቸው ምን ያህል ደቡብ ፖሊሶች በሜዳቸው ጠንካራ ቡድን እንደሆኑ የሚያሳይ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ቡድኑ አንጋፋ ተጫዋቾችን ከአዳዲስ እና ወጣት ተጫዋቾች ጋር አቀናጅቶ መቅረቡ ለውጤታማነቱ ቀዳሚውን ቦታ ይወስዳል ተብሎ ይታመናል። በሜዳው አልቀመስ ማለቱ የቡድኑ አስፈሪ የማጥቃት ሀይሉ እንደሆነ በተደጋጋሚ የታየ ሲሆን በሁለቱም የመስመር ኮሪደሮች እና በአጥቂ ቦታ ላይ የሚሰለፉ ተጫዋቾች የሚያደርጉት አስፈሪ እንቅስቃሴ ነገም ይጠበቃል። በርካታ ጨዋታ ላይ ተሰልፎ በመጫወት ውጤታማነቱን ከማሳየቱም በላይ በርካታ ግቦችን የሚያስቆጥረው ብሩክ ኤልያስ ላይ የተመሰረተ ቡድን የገነቡት አሰልጣኝ ግርማ ነገም አጨዋወታቸው ብሩክ በሚሰለፍበት የግራ መስመር በኩል እንደሚሆን ይገመታል። ነገር ግን ቡድኑ እንደ ብሩክ ሁሉ በቀኝ በኩል የብርሃኑ በቀለ እንቅስቃሴ አስፈሪ እንደመሆኑ እና የመሃል መስመር አጥቂው የኤሪክ ሙራንዳ አይምሬነት የማጥቃት ሀይሉ ላይ ተጨማሪ ጥንካሬ ይሰጡታል ተብሎ ይጠበቃል።
በአሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው የሚሰለጥኑት ባህርዳሮችም እንደ ፖሊሶች ሁሉ የሚከተሉት የመስመር አጨዋወት በነገው ጨዋታ ለደቡብ ፖሊሶች ፈታኝ ሊሆን ይችላል። በተለይ በዓመቱ የመስመር ተጨዋቾችን በመቀያየር የመስመር ላይ የጨዋታ ባህሪያቸውን እንደየ ተጋጣሚያቸው በመለዋወጥ ለመጫወጥ ሲጥሩ ታይቷል። በነገው ጨዋታ ለባህርዳሮች ዋነኛ የማጥቂያ መሳርያ የሚሆነው ይህ የመስመር አጨዋወት ሊሆን እንደሚችል የሚታሰብ ሲሆን አሰልጣኙ በበርካታ ጨዋታዎች ላይ ሲጠቀም እንደነበረው ወሰኑ አሊን በግራ ፍቃዱ ወርቁን በቀኝ በማድረግ እና ሙሉቀን ታሪኩ ኢላማ ያደረጉ ኳሶች በመላክ የግብ እድሎችን ለመፍጠር ይሞክራሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ሁለቱም ቡድኖች ከመስመር አጨዋታቸው በተጨማሪ በየቡድኖቻቸው አምበሎች የሚመራው የአማካኝ መስመር ስፍራውቸውም ጠንካራ እንደሆነ በአመቱ ታይቷል። ባህርዳሮች የአማካኝ ስፍራ ተጨዋቾቹ በግላቸው ጥሩ ጊዜ ማሳለፋቸው ቡድኑን የጠቀመው ይመስላል። የቡድኑ ዋና አምበል የደረጄ መንግስቱ፣ ዳንኤል ኃይሉ እና የፍቅረሚካኤል ዓለሙ በበርካታ ጨዋታዎች ቋሚ በመሆን መጫወታቸው ቦታው የተረጋጋ እንዲሆን ያደረገው ሲሆን ለተከላካዮች ሽፋን በመስጠትም ለአጥቂዎች ኳስ በማመቻቸትም የተሳካ ጊዜ ማሳለፋቸው ተስተውሏል።ይህ የተቀናጀ የመሃል ሜዳ ጥምረት በነገው ጨዋታም ሊታይ እንደሚችል የሚገመት ሲሆን በተለይ የዳንኤል ለሙሉቀን የሚልካቸው ረጃጅም ኳሶች አደጋ ሊፈጥሩ እንደሚችሉ ይጠበቃል። ፖሊሶችም በቡድኑ አምበል ቢኒያም አድማሱ፣ ሚካኤል ለማ እና አበባየሁ ዮሃንስ የሚመራው የተደራጀ የአማካይ ክፍል ያላቸው በመሆኑ ከፍተኛ ፍልሚያ የአማካይ ስፍራው ላይ እንደሚኖር ይጠበቃል።
በተከላካይ በኩል የተለያዩ ጥምረቶችን በዓመቱ ሲያስመለክቱን የነበሩት አሰልጣኝ ጳውሎስ ተስፋሁን ሸጋው፣ ወንድሜነህ ደረጄ፣ አቤል ውዱ እና ሚኪያስ ግርማን ሊጠቀሙ እንደሚችሉ ይገመታል። ምክንያቱም እነዚህ ተጨዋቾች በአንፃራዊነት በርከት ያሉ ጨዋታዎችን መጫወታቸው እና የእርስ በእርስ መግባባታቸው ጥሩ በመሆኑ ቡድኑ ግብ እንዳይቆጠርበት ሊያደርግ ይችላል ተብሎ ስለሚታመን ተመራጭ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል። በተለይ የተስፋሁን ሸጋው እና የሚኪያስ ግርማ የሚያደርጉት የመስመር ላይ ሩጫዎች በወሰኑ አሊ እና ፍቃዱ ወርቁ ይመራል ተብሎ በሚጠበቀው የክንፍ የአጥቂ መስመር ተጨማሪ ግብአት ሊሆን እንደሚችል ይታመናል።
በዚሁ የተከላካይ ቦታ በደቡብ ፖሊሶች በኩል ብርሃኑ በቀለ፣ ደስታ ጊቻሞ፣ አየለ ተስፋዬ እና ደረጄ ፍሬው ሊሰለፉ እንደሚችሉ ይጠበቃል። ነገር ግን ይህ የተከላካይ ጥምረት አስተማማኝ አለመሆኑ በአመቱ የታየ መሆኑ የማይካድ ሲሆን በተለይ በፈጣን የመልሶ ማጥቃት የሚጫወት ቡድን ሲገጥመው እንደሚፍረከረክ ታይቷል።
በግብ ጠባቂ በኩል ባህርዳሮች እንደተለመደው ዋነኛ ምርጫቸው የሆነውን ምንተስኖት አሎን ቀዳሚ ምርጫቸው በማድረግ ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ቀድሞ መናገር ቢቻልም ተጋጣሚያቸው ደቡብ ፖሊሶች ግን አንደኛ ግብ ጠባቂያቸውን በቅጣት በማጣታቸው ወደ ሁለተኛ ግብ ጠባቂያቸው ሀብቴ ከድር ፊታቸውን ያዞራሉ ተብሎ ይታሰባል።
በጥንካሬው ሁሉ በድክመትም በኩል ሁለቱም ቡድኖች የሚጋሩዋቸው ነገር እንዳለ በአመቱ ታይቷል። ሁለቱም ከሜዳቸው ውጪ የሚያደርጉዋቸውን ጨዋታዎች ለማሸነፍ ይቸገራሉ። ባህር ዳር ከተማ ካደረጋቸው ጨዋታዎች 8 አቻ ሲያስመሰግብ 5ቱ ከሜዳው ውጪ ተቸግሮ ነጥብ የተጋራበት ጨዋታዎች ናቸው። እንዲሁም ቡድኑ በአመቱ ሶስት ሽንፈቶችን (በቡራዩ ከተማ፣በገጣፎ ከተማ እና በሰበታ ከተማ) ብቻ ያስመሰገበ ሲሆን ሶስቱም ከሜዳው ውጪ በተደረጉ ጨዋታዎች ነው ተሸንፎ የወጣው።
ደቡብ ፖሊሶችም በተመሳሳይ ከሜዳቸው ውጪ የሚያደርጉትን ጨዋታ ብዙ ነጥቦችን የጣሉበት ነው። ቡድኑ ከሜዳው ውጪ መሰብሰብ ከነበረበት 45 ነጥብ 21 ብቻ የግሉ ማድረግ የቻለ ሲሆን 4 ጨዋታዎችን ተሸንፎ 6 ጨዋታዎቹን ነጥብ በመጋራት አመቱን አሳልፏል። ይህ የሚያሳየው ሁለቱም ከሜዳቸው ውጪ የሚቸገሩ መሆኑን ነው። የነገው ጨዋታ ደግሞ ለሁለቱም ገለልተኛ ተብሎ በታሰበ ሜዳ እንደመደረጉ ምን አይነት አቋም ያሳያሉ የሚለው የሚጠበቅ ነው።
ነገር ግን በአንፃራዊነት ባህር ዳር ከተማ ከደቡብ ፖሊስ በተሻለ የአንድ ሳምንት ተጨማሪ የእረፍት እና የማገገሚያ (ሪከቨሪ) ጊዜ ማግኘቱ ለቡድኑ እንደ በጎ የሚነሳ ሲሆን በተቃራኒው ለደቡብ ፖሊሶች ግን የመጨረሻኛ ሳምንት የምድብ ጨዋታቸውን ካደረጉ ከ7 ቀናት በኃላ ነው ለዚህ የፍፃሜ ጨዋታ የሚደርሱት። ይህም ጉዳይ ባህር ዳር ከተማዎችን ተጠቃሚ ሊያደርግ እንደሚችል ይገመታል።
የጉዳት ዜና በሁለቱም ቡድኖች በኩል ያልተሰማ ሲሆን በቅጣት በኩል ግን ሁለቱም አንድ አንድ ተጨዋችን በነገው ጨዋታ ያጣሉ። በ29ኛ ሳምንት ደቡብ ፖሊስ ከሀምበሪቾ ጋር ባደረጉት ጨዋታ በቀይ ካርድ ከሜዳ የተሰናበተው መኳንንት አሸናፊ ቅጣቱን ባለመጨረሱ ከነገው ጨዋታ ውጪ ነው። በባህር ዳር ከተማ በኩል ደግሞ ዳግማዊ ሙሉጌታ በተመሳሳይ በቅጣት ከዋንጫው ጨዋታ ውጪ ነው።
የነገውን ወሳኝ ጨዋታ በዋና ዳኝነት የሚመሩት ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ብሩክ የማነብርሃን ሲሆን ረዳቶቻቸው ደግሞ ይበቃል ደምሰ፣ አበራ አብርደው እና ለሜ ንጉሴ እንደሆኑ ፌደሬሽኑ አስታውቋል። ጨዋታው ነገ 9 ሰዓት አዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ላይ ይከናወናል።