ወደ ፕሪምየር ሊግ ያደጉ ሁለት ቡድኖችን የለየው የ2010 የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ውድድር ቀጣዩን አዳጊ ክለብ ለመለየት በሁለቱ ምድቦች ሁለተኛ ሆነው ያጠናቀቁት ቡድኖችን ያፋጥጣል። ሽረ እንዳሥላሴ የምድብ ሀ፣ ጅማ አባቡና ደግሞ የምድብ ለ ሁለተኛ ሆነው ለመለያ ጨዋታ የደረሱ ክለቦች ናቸው።
እንደ አምናው ሁሉ እስከመጨረሻው ሳምንት ድረስ በትንቅንቅ የተሞላው ምድብ ለ እስከ 30ኛው ሳምንት ወደ ፕሪምየር ሊግ የሚያድገውም ሆነ ሁለተኛ ደረጃን የሚይዘውን ቡድን ያለየ ነበር። በመጨረሻው ሳምንት በተደረጉት ጨዋታዎች ግን ሶስቱም ተፎካካሩ ቡድኖች ማሸነፋቸውን ተከትሎ ጅማ አባ ቡና በግብ ልዩነት ሀላባን በልጦ ከደቡብ ፖሊስ በሁለት ነጥቦች ዝቅ በማለት ሁለተኛ ደረጃ ይዞ ማጠናቀቅ ችሏል። አምና ወደ ከፕሪምየር ሊጉ የወረደው አባ ቡና ለብዙዎች ፈተና የሆነው በድጋሚ መመለስን ለማሳካት አንድ ጨዋታ ብቻ ቀርቶታል። በምድብ ሀ የሚገኘው ሽረ እንዳስላሴ አምና ወደ ሊጉ ከተቀላቀለ ጀምሮ እድገቱን ጠብቆ በመጓዝ ዘንድሮም ወደ ፕሪምየር ሊግ ለመግባት ከጫፍ ደርሷል። ሽረ በውድድር ዘመኑ በተለይ ከአዲስ አበባ እና ከሰበታ ብርቱ ፍክክር ቢገጥመውም በመጨረሻዎቹ አምስት ሳምንታት ተከታዩቹ ተደጋጋሚ ነጥብ መጣላቸውን ተከትሎ በ28ኛው ሳምንት ነበር ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁ የተረጋገጠው።
የሁለቱ ቡድኖችን የውድድር ዓመት በቁጥሮች ስንመለከት ጅማ አባ ቡናዎች ከሜዳቸው ውጭ ካደረጉት አስራ አምስት ጨዋታዋች 5 ተሸንፈው 2 አቻ ወጥተው 8ቱን ማሸነፍ ችለዋል። በተቃራኒው 20 ጨዋታ (ገለልተኛ ጨዋታ ጨምሮ) ከሜዳው ውጭ በመጫወት አመቱን ያሳለፈው ሽረ እንደሰላሴ ከሜዳው ውጭ 10 ያህል ጨዋታ አድርጎ 4 ተሸንፎ በ 3 አቻ እንዲሁም በ3ቱ አሸንፏል። በገለልተኛ ሜዳ በተደረገ ጨዋታ 2 ተሸንፎ በ3ቱ አቻ ተለያይቶ 5ቱን ማሸነፍ ችሏል። ሁለቱ ቡድኖች በሜዳቸው ባደደረጓቸው ጨዋታዎች ሽንፈት ያልገጠማቸው ሲሆን ጅማ አባቡና 9 አሸንፎ በ6 አቻ ተለያይቷል። ሽረ ደግሞ ከ10 ጨዋታ በ7 ሲያሸንፍ 3ቱን ተለያይቷል።
ሁለቱ ቡድኖች በተለያየ ምድብ ውስጥ የሚገኙ እና የተለያየ ታሪክ ያላቸው እንደመሆኑ አጨዋወታቸው ከዚህ አንፃር የተቃኘ ነው። በአሰልጣኝ ዳንኤል ፀሀዬ የሚመራው ቡድን በመስመር በኩል በሚደረጉ ፈጣን ሽግግሮች የማጥቃት እንቅስቃሴውን የመሰረተ ሲሆን በአንዳንድ ጨዋታዎች ከግብ ክልላቸው ጀምሮ ኳስን በመመስረት የማጥቃት እንቅስቃሴ ለማድረግ የሚያደርጉት ጥረት በሜዳ ላይ የሚታይ ነው። የተረጋጋ ስብስብ ያለው መሆኑ፣ እና እንደ ቡድን መጫወት መቻሉ በተጫዋቾች አቋም ላይ ያልተንጠለጠለ ቡድን እንዲሆን አድርጎታል። ይህ ማለት ግን በግላቸው ከፍተኛ ሚና የተወጡ ተጫዋቾች የሉትም ማለት አይደለም። በአጥቂው ክፍል ለተቃራኒ ቡድን ፈተና የሆኑት ጅላሎ ሻፊ ፤ ንስሃ ታፈሰ፣ ሰዒድ ሁሴን እና ልደቱ ለማ እንዲሁም የመሀለኛውን ስፍራ ይዘው የሚጫወቱት አሸናፊ እንዳለ ፤ ሳሙኤል እና ዮናስ አርዓያ በርካታ ጨዋታዋች ላይ አብረው መሰለፋቸው ቦታው የተረጋጋ እንዲሆን አድርጎታል።
ጅማ አባ ቡና በበኩሉ ስብስቡ በአንፃራዊነት የፕሪምየር ሊግ ልምድ ያለውና በከፍተኛ ሊጉ ደረጃ ከፍተኛ የሚባል የጥራት ደረጃ ያለው ነው። በውድድር ዓመቱ ተደጋጋሚ የአስተዳደራዊ እና የፋይናንስ ችግሮችን ተቋቁሞ እዚህ የደረሰውም በስብስበ ጥራቱ ምክንያት ይመስላል። በአንተነህ አበራ የሚመራው ጅማ አባቡና 4-4-2 አሰላለፍን በመጠቀም ኳስን በመቆጣጠርና እንደ ጨዋታው ሁኔታ በመልሶ ማጥቃት በመጠቀም በርካታ ጎሎችን ለማስቆጠር የማይቸገር ቡድን ነው። በተለይ ሁለቱ የፊት መስመር ተጫዋቾች ብዙዓየሁ እንደሻሁ እና ቴዎድሮስ ታደሰ በድምሩ 31 ግቦችን በማስቆጠር የከፍተኛ ሊጉ ምርጥ ተጣማሪዎች ሲሆኑ፣ ሱራፌል ጌታቸው፣ ሀይደር ሸረፋ እና ኃይለየሱስ ብርሀኑን የያዘው የአማካይ ክፍል ጥምረትም ቡድኑ ምን ያህል በተጫዋቾች ደረጃ የተሻለ እንደሆነ የሚያሳይ ነው።
በሁለቱም ቡድኖች በአንፃራዊነት እንደ ድክመት የሚቆጠረው የተከላካይ መስመሩ ነው። የጅማ አባ ቡና የተከላካይ ክፍል ወደ መሐል ሜዳው በመጠጋት በተጋጣሚ ላይ ላይ የበላይነት ለመውሰድ የሚያደርገው ጥረት በተደጋጋሚ ለመልሶ ማጥቃት አደጋ ሲያልጠው ተስተውሏል። ሽረ እንዳስላሴም ተመሳሳይ የመከላከል ድክመት ያለበት ሲሆን የተጋጣሚው አጥቂዎች አስፈሪ ጥምረት እና ድንገተኛመልሶ ማጥቃት ደግሞ ይበልጥ ነገሮችን አስቸጋሪ ሊያደርግባቸው ይችላል። የመጀመርያ ምርጫ ግብ ጠባቂያቸው ሙሴ ዮሀንስ በጉዳት የመሰለፉ ነገር አጠራጣሪ መሆንም ተጨማሪ ራስ ምታት ሊሆን ይችላል።
በሃዋሳ ሰው ሰራሽ ስታድየም በ9:00 የሚከናወነውን ጨዋታ ኢንተርናሽናል ዳኛ ባምላክ ተሰማ በዋና ዳኝነት የሚመራው ሲሆን ረዳቶቹ ኢንተርናሽናል ዳኛ ተመስገን ሳሙኤል እና ኢንተርናሽናል ዳኛ ክንፈ ይልማ መሆናቸው ታውቋል። ባምላክ እና ተመስገን ይህን ጨዋታ ካከናወኑ በኋላ በ2019 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ቱኒዚያ ከስዋዚላንድ የሚያደርጉትን ጨዋታ ለመምራት ወደ ስፍራው የሚያቀኑ ይሆናል።