በዝውውር መስኮቱ ላይ ከቀደመ አካሄዱ በተለየ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው ደደቢት ሁለት ተጨማሪ ተጨዋቾችን ወደ ቡድኑ ቀላቅሏል።
በደሴ ከተማ በተከላካይ አማካይ ስፍራ ላይ የሚጫወተው ኩማ ደምሴ ሰማያዊዎቹን ተቀላቅሏል። ኩማ የእግር ኳስ ህይወቱን በመድን ተስፋ ቡድን ጀምሮ በ2009 በባህርዳር ያሳለፈ ሲሆን 2010 የውድድር ዓመትን በደሴ ከተማ አሳልፏል።
በአማራ ውሃ ስራ በቀኝ ተከላካይ ስፍራ የሚጫወተው አብዱላዚዝ አብደላ ሌላኛው የደደቢት ፈራሚ ነው። በወሎ ኮምቦልቻ የእግርኳስ ህይወቱን የጀመረው አብዱላዚዝ በ2008 ለመቐለ የተጫወተ ሲሆን በ2009 ወደ አውስኮድ አምርቶ ለሁለት ዓመታት ተጫውቷል።
ደደቢት ካስፈረማቸው ተጫዋቾች በተጨማሪ ግብ ጠባቂው ምንተስኖት የግሌ ውል ያደሰው ደደቢት ከዚህ ቀደም ከባህርዳር እንዳለ ከበደን እንዲሁም ከሺንሺቾ ሶስት ተጫዋቾችን ማስፈረሙ ይታወቃል።
በተያያዘ የደደቢት ዜና 9 የውጭ ተጫዋቾችን ለሙከራ ማስመጣቱ ታውቋል። ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ ያደረጉት ስራ አስኪያጁ አቶ ሚኪኤል አምደመስቀል ” ውጭ ሀገር ተጫዋቾች ከማምጣታችን በፊት የተጫዋችን ደሞዝ በጥልቀት ተመልከተናል። ከጥናቱም ተነስተን በወርሀዊ ደሞዝ 800 ዶላር በመክፈል የውጭ ተጫዋቾችን ለማዛወር እንቅስቃሴ ጀምረናል። በአሁኑ ሰዓት አራት ተጫዋቾችን ወደ ሀገር ውስጥ ያስገባን ሲሆን የሙከራ ጊዜያቸውን እንዳጠናቀቁ በቀጣይ የሚመጡትን እንለያለን ” ብለዋል።