የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን በግንቦት ወር አዲስ የፕሬዝዳንታዊ እና የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ምርጫ በአፋር ከተማ ሰመራ ላይ ማከናወኑ ይታወሳል። ይህን ተከትሎም ኮሚቴዎችን በማደራጀት አዳዲስ የኮሚቴ ሰብሳቢዎች መሾሙን ፌደሬሽኑ ከወር በፊት የገለፀ ሲሆን በአዲስ መንፈስ ለውጥ ለማምጣት ስራዎችን እንደሚሰራም ማስታወቁ ይታወሳል።
ከፌዴሬሽኑ ቋሚ ኮሚቴዎች አንዱ የሆነው የዳኞች ኮሚቴ በአቶ ዮሴፍ ተስፋዬ የሚመራ ሲሆን ነገ እና ከነገ በስትያ ስለሚደረገው የአካል ብቃት ፈተና ለመጀመሪያ ጊዜ ለተፈታኞች ማብራሪያ ሰጥቷል። ዛሬ አመሻሽ በኢትዮጵያ ሆቴል በተከናወነው ፕሮግራም የኢትዮጵያ ዳኞች ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ዮሴፍ ተስፋዬ፣ የአካል ብቃት ኢንስትራክተር አቶ ቸርነት አሰፋ እና ሳራ ሰዒድ ተፈታኞች በፈተናው ወቅት ምን ማድረግ እንዳለባቸው እና ስለ ፈተናው ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ሁለት ሰዓት የፈጀውን ይህን ፕሮግራም በንግግር የከፈቱት አቶ ዮሴፍ ተስፋዬ ዳኞቹ ጥሪያቸውን አክብረው በመምጣታቸው ምስጋና በማቅረብ ወደ ማብራሪያቸው ገብተዋል። “በመጀመሪያ ጥሪያችንን አክብራችሁ እዚህ በመምጣታችሁ በዳኞች ኮሚቴ ስም ሁላችሁንም አመሰግናለው። ይህ ፕሮግራም የተዘጋጀበት ዋና አላማ ነገ እና ከነገ በስቲያ የሚደረገውን የአካል ብቃት ፈተናን (fitness test) አስመልክቶ ሲሆን ስለ ፈተናው እና ተያያዥ ጉዳዮች ማብራሪያ ለመስጠት ነው” ብለዋል።
አቶ ዮሴፍ ቀጥለው የቀደመውን አሰራር ስለመተው እና በአዲስ መንፈስ ቀጣይ ስራዎችን ስለመስራት ተናግረዋል። “አሁን ፌደሬሽኑ ለውጥ ላይ ነው ያለው። እኛም ደግሞ ይህንን ለውጥ ማገዝ አለብን። ስለዚህ የበፊቱን እና ያረጀውን አሰራር አንከተልም። ሁላችንም የበፊቱን ነገር በመተው ቀጣይ ስራዎችን እያሰብን መንቀሳቀስ አለብን።” በማለት ዳኞቹ ከዚህ በፊት እንኳን የአሰራር በደል ደርሶባቸው ቢሆን እሱን በይቅርታ በመተው በአዲስ መንፈስ መስራት እንዳለባቸው አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
ከአቶ ዮሴፍ በመቀጠል ሁለቱ የአካል ብቃት ኢንስትራክተሮች ቴክኒካዊ የሆኑ ማብራሪያዎችን በተለይ በፈተናው መደረግ ስላለባቸው ነገር ገለፃ ሰጥተዋል። በመቀጠል በቦታው የተገኙ የተለያዩ ዋና እና ረዳት ዳኞች ጥያቄ እና አስተያየት ሰጥተዋል። በአስተያየቱም በርካታ ዳኞች ለመጀመሪያ ጊዜ በተዘጋጀው መድረክ ደስተኛ መሆናቸውን እና ስለ ፈተናው ማብራሪያ ስለተሰጣቸው ተጠቃሚ እንደሚሆኑ የገለፁ ሲሆን መስተካከል አለበት ብለው በሚያስቧቸው ጉዳዬች ላይም ነጥቦችን አንስተዋል። በስተመጨረሻ ዳግም ንግግር ያደረጉት የኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ዮሴፍ ፈተናው ግልፅነት እና ተጠያቂነት ባለው መልኩ እንደሚከናውን አስረድተዋል።
ከካፍ በሚመጡ ባለሙያዎች በሚሰጠው ይህ የአካል ብቃት ፈተና (የፊትነስ ቴስት ወይም ኩፐር ቴስት) ለ22 ዋና እና ረዳት ኢንተርናሽናል ዳኞች እንዲሁም 70 ፌደራል ዳኞች እንደሚሰጥ የተነገረ ሲሆን ፈተናው ነገ እና ከነገ በስቲያ ከማለዳው 12 ሰዓት እስከ ቀኑ 6 ሰዓት በአዲስ አበባ ስታዲየም ይደረጋል ተብሏል።
በተያያዘ ዜና ይህ የዳኞች ኮሚቴ በቀጣይ ሁሉንም የሀገራችን ዳኞች በመሰብሰብ ስላሉ ችግሮች ውይይት እንደሚያደርግ የታወቀ ሲሆን ወደ ፊት በሚገለፅ ቀን የዳኞችን ችግር ለማዳመጥ እንደታሰበ እና የመፍትሄ አሳቦችን በመነጋገር ለማምጣት እንደታቀደ ለማወቅ ተችሏል።