የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ትላንት በተደረጉ የመለያ እና የዋንጫ ጨዋታዎች ወደ ፕሪምየር ሊግ ያደጉትን ክለቦች ሙሉ ለሙሉ አሳውቆ አጠቃላይ አሸናፊውን ቢለይም በተለያየ ምክንያት ያልተደረጉ የምድብ ለ ጨዋታዎች መካሄዳቸውን እንደቀጠሉ ናቸው። በዛሬው እለትም አራት ጨዋታዎች ተከናውነው ሶስተኛው ወራጅ ቡድን ታውቋል።
በ28ኛ ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታ ወደ ሚዛን አማን ያመራው ድሬዳዋ ፖሊስ በቤንች ማጂ ቡና 2-0 ተሸንፏል። ወደ ዲላ ያመራው ነጌሌ ከተማ ዛሬ ዲላ ከተማን ገጥሞ 1-0 ማሸነፉን ተከትሎም ድሬዳዋ ፖሊስ ወደ አንደኛ ሊግ መውረዱን አረጋግጧል። ድሬዳዋ ፖሊስ ከፍተኛ ሊጉ በ2008 ከተጀመረ ወዲህ በሁለት ዓመታት ላለመውረድ ታግሎ በመጨረሻ ሲተርፍ ቆይቶ በዚህ ዓመት ግን መውረዱ እርግጥ ሆኗል።
በ27ኛ ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታ ናሽናል ሴሜንት በቡታጅራ ከተማ ቢሸነፍም ሳይወርድ ቀርቷል። ባለፈው ሳምንት መውረዱን ያረጋገጠው ሻሸመኔ ከተማ ደግሞ ስልጤ ወራቤን 1-0 አሸንፏል።
ከፍተኛ ሊጉ ሙሉ ለሙሉ ሊጠናቀቅ ሁለት የተቋረጡ ጨዋታዎች የሚቀሩ ሲሆን ከተቋረጠ ወራትን ያስቆጠረው የወልቂጤ እና ካፋ ቡና ጨዋታ ውሳኔ እንዲሁም ባለፈው ሳምንት የተቋረጠው የቤንች ማጂ ቡና እና ናሽናል ሴሜንት ጨዋታም ውሳኔ የሚጠብቅ ነው።
በምድብ ሀ እስካሁን ምላሽ ያላገኘው የፌዴራል ፖሊስ ክስ እንዳለ ሆኖ ሱሉልታ ከተማ፣ ወሎ ኮምቦልቻ እና ፌዴራል ፖሊስ ወደ አንደኛ ሊግ የወረዱ ሲሆን በምድብ ለ መቂ ከተማ፣ ድሬዳዋ ፖሊስ እና ሻሸመኔ ከተማ በቀጣዩ ዓመት በአንደኛ ሊግ የሚወዳደሩ ክለቦች ናቸው።
ከአንደኛ ሊጉ አዳማ ላይ በተከናወነ የማጠቃለያ ውድድር አቃቂ ቃሊቲ፣ ገላን ከተማ፣ ከምባታ ሺንሺቾ፣ ቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ፣ ሶዶ ከተማ እና አርሲ ነጌሌ ወደ 2011 ከፍተኛ ሊግ ማደጋቸው የሚታወስ ነው።