“ በክለባችን ተጫውተው ያሳለፉ ውድ ልጆቻችን ወደ ክለባቸው እንዲመለሱ አድርገናል “ አቶ ኢሳይያስ ደንድር

በ1953 የተመሰረተው የኢትዮ ኤሌክትሪክ ስፖርት ክለብ በሀገሪቱ ስፖርት ላይ የጎላ አሻራቸውን ማስቀመጥ ከቻሉ ታሪካዊ ክለቦች መካከል አንዱ ነው፡፡ በተለይ በእግር ኳሱ ደግሞ ፕሪምየር ሊጉ በአዲስ መልክ ከተጀመረ ጀምሮ ሁለት ጊዜ ቻምፒዮን ከመሆን ባለፈ በወጣቶች ላይ ተመስርቶ ቡድኑን በመገንባት ለሌሎች ክለቦች እና ለዋናው ብሔራዊ ቡድንም በርካታ ተጨዋቾችን አበርክቷል፡፡ ሆኖም ከሚሌንየሙ መግባት በኋላ ክለቡ በውጤቱ እጅግ አሽቆልቁሎ ለዓመታት በመውረድ ስጋት ውስጥ ሲንከባለል ቆይቶ በመጨረሻም ዘንድሮ ወደ ከፍተኛ ሊጉ ለመውረድ ተገደዷል፡፡ ከመውረድ ባለፈም ባለፉት ወራት የክለቡ ህልውና በራሱ ጥያቄ ውስጥ ገብቶ የነበረ ቢሆንም በተቃራኒው ዳግም በማንሰራራት ራሱን መልሶ ለማግኘት ጉዞ ጀምሯል፡፡ ሶከር ኢትዮጵያም በዚህ ሂደት ውስጥ  ቁልፍ ሚና ካላቸው የወቅቱ የክለቡ ቦርድ ሰበሳቢ አቶ ኢሳይያስ ደንድር ጋር በክለቡ ወቅታዊ ጉዳዮች እና ቀጣይ ተስፋዎች ዙሪያ ቆይታ አድርጋለች፡፡ 


ኢትዮ ኤሌክትሪክ መውረዱን ተከትሎ ሊፈርስ መቃረቡ ሲነገር ቢቆይም ጠቅላላ ጉባዓው ክለቡ እንዲቀጥል ወስኗል። ክለቡን የማስቀጠል ውሳኔ ሂደት ምን ይመስል ነበር ? 

 

ከክለቡ ህልውና (ቀጣይነት) ጋር በተያያዘ በተለያየ ሁኔታ የሚነሱ ጉዳዮች እንደነበሩ እኔም እሰማ ነበር፡፡ ይህ ደግሞ የክለቡን ማህበረሰብና ስፖርት ወዳዱን ህብረተሰብ በሙሉ ያሳሰበ ነበር፡፡ ከአንድ ወር ከአስራ አምስት ቀን በፊት የክለባችን አምበል ” ተጫዋቾች የክለቡን ህልውና በተመለከተ ጥያቄ አላቸው ክለቡ ከወረደ ይፈርሳል ስለተባለ ያለውን ሁኔታ ማወቅ ይፈልጋሉ።” ብሎ ቢሮ መጥቶ ጠየቀኝ። በወቅቱ እንደዛ ያለው አካል ምክንያቱ ምን እንደሆነ ባላውቅም እኛ ግን ተነሳሽነት ለመፍጠርና ክለቡ እንዳይወርድ ጠንክራችሁ እንድትጫወቱ ለማበረታታት ነው በሚል እንውሰደው፤ እኔ እስከማውቀው ድረስ ክለቡ ታላቅ ታሪክና በርካታ ባለቤቶች ያሉት በመሆኑ እንደዚህ በቀላሉ የሚፈርስ አይደለም፤ መገንባት ነው እንጂ ማፍረስ መች ይከብዳል የሚል አባባል አለ። ለእኛ ክለብ ግን በተቃራኒው ነው ማፍረስ በጣም ይከብዳል መገንባት ግን ጠንካራ ጎኖችን ይዞ ክፍተቶችን ማስተካል ስለሆነ ጥረት ቢጠይቅም ቀላል ነው ብዬ መለስኩለት፡፡ በጠቅላላ ጉባኤው የመጀመሪያ ቀን ሰፊ ውይይት ተደርጓል ክለቡ በመንግስት ተቋማት ስር የሚተዳደር እንደሆነ በስፖርት መስክ መሳተፍ ማህበራዊ ኃላፊነትን ከመወጣት አኳያ መወሰድ እንዳለበት የተነሳበት ሁኔታ ነበር፡፡ ማህበራዊ ኃላፊነትን ለመወጣት ሌሎች የተለያዩ አማራጮችን እየተጠቀሙ እንደሆነም ተነስቷል። ለምሳሌ ጤና ጣቢያ/ክሊኒክ መገንባትና ለህብረተሰብ አገልግሎት እንዲሰጥ ማድረግ፣ ይህ መልካምና አስፈላጊ ነገር ነው ግን ጤና ጣቢያ/ክሊኒክ ለታመሙ ሰዎች እርዳታ የሚሰጥ ሲሆን ስፖርት ደግሞ እንዳይታመሙ የበኩሉን አስተዋጽኦ የሚያደርግ ነው፡፡ በውይይቱ ማጠቃለያ የተቋሙ ዋና ስራ አስፈጻሚና የጠቅላላ ጉባኤው ሰብሳቢ የሰጡት አቅጣጫ ክለቡ የነበረበትን ችግር በመቅረፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ሲሆን በዚሁ መሰረት በሚቀጥለው ስብሰባ አዲስ የስራ አመራድ ቦርድ ለመሰየም ከስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ በዚህ አጋጣሚ ለእሳቸው ያለኝን ምስጋና ለማቅረብ እወዳለሁ፡፡ 


ለክለባችሁ ከፕሪምየር ሊግ መውረድ የተለያዩ ምክንያቶች እንዳሉ ሆነው ለእርስዎ የቱ ምክነያት ሚዛን ይደፋል ? 

  

የተለያዩ ምክንያቶች ድምር ውጤት ሊሆን ይችላል፡፡ ለእኔ ግን ዋነኛው ምክንያት እዛ አካባቢ መገኘታችን ነው፤ አግኝተኸኝ ከሆነ ወራጅ ቀጠና አካባቢ ማለቴ ነው። ይህ ደግሞ ለተከታታይ ዓመታት የነበርንበት ነው፡፡ እዚህ አካባቢ ባንገኝ ኖሮ ወደ ማማትም ሆነ መታማት አንገባም ነበር፡፡ 


ክለቡ በአዲስ መልክ ቦርዱን ማዋቀሩ ይታወሳል። ያለፈው ቦርድ አባላት ከስፖርቱ ዕውቀት የራቁ መሆን እና በተቋሙ ሌሎች ኃላፊነቶች ላይ ደርበው በመስራታቸው እንዲሁም ለሁለት ተቋማት በመከፈላቸው ምክንያት የውጤት መጥፋቱ እንደመጣ ይነገራል። ከዚህ አንፃር አዲሱ ቦርድ በምን ይለያል? 

 

የቀድሞውን ስራ አመራር ቦርድ አባላት በተመለከተ ከሁለቱ ተቋማት (ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልና ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት) የተወጣጡ ሰባት አባላት የነበሩት ቢሆንም ሲሳተፉ የቆዩት ጥቂት አባላት በተለይ ደግሞ ሰብሳቢው ብቻ እንደነበሩ በጠቅላላ ጉባዔው ስብሰባ ላይ ለመረዳት ተችሏል፡፡ ክለባችን ውጤት ያጣው ከ 2001 ዓ.ም ጀምሮ ነው ከ2001 በኋላ የተሻለ ውጤት ተብሎ ሊወሰድ የሚችለው በ2004 እና 2006 የተገኘው ውጤት ብቻ ነው፡፡ በሌሎቹ ዓመታት የነበረው ውጤት 11ኛ እና ከዚያ በታች ነው፡፡ ክለቡ ውጤታማ እንዲሆን ለማድረግ የስራ አመራር ቦርዱ እገዛና ክትትል አስፈላጊ ቢሆንም በዋነኝነት ተዋናዮቹ ከስራ አመራር ቦርዱ ስር ያሉ አካላት ናቸው በተለይ አሰልጣኞችና ተጫዋቾች በዚህ ረገድ የነበረው የግንኙነት ክፍተትም ለውጤቱ መጥፋት አሉታዊ አስተዋጽኦ ያሳደረ ይመስለኛል፡፡ ቀደም ሲል የነበሩት የስራ አመራር ቦርድ አባላትም ሆነ አሁን የተሰየመው ቦርድ አባላት በሁለቱ ተቋማት የተለያየ የስራ ኃላፊነት ያለን ሰዎች ነን፡፡ ነገር ግን አዲሱ የስራ አመራር ቦርድ ለስፖርቱ ከፍተኛ ፍቅርና ፍላጎት ያላቸው አባላት የተሰባሰቡበት ነው፡፡ 


ምን የተለዩ አካሄዶች እና አሰራሮችን እንጠብቅ ? ዕቅዳችሁን በአጭሩ… 

 

የስራ አመራር ቦርዱ በተሰየመ ማግስት ሰፊ ውይይት አድርገናል፡፡ የዚህን ታላቅ ክለብ ስምና ዝና ለመመለስ የተቻለንን ሁሉ ለማድረግም ተስማምተናል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ወደ ስፖርት አመራርነት መምጣት የሚፈለግ ባይሆንም ካለን የስፖርት ፍቅር አኳያ ክለቡ ከስጋት ተላቆ ራዕይ ያለው እንዲሆን መሰረት መጣል አለብን በሚል ስራ ጀምረናል፡፡ ወደ ስራ ከመግባታችን በፊት ያለውን አጠቃላይ ሁኔታ መሰረት በማድረግ በአጭር፣ በመካከለኛና በረዥም ጊዜ ዕቅድ መሰራት ያለባቸውን ስራዎች የለየን ሲሆን የአጭር ጊዜ ዕቅዱን ደግሞ በሌሎች ሶስት ምዕራፎች ከፍለነዋል፡፡ በመጀመሪያው ምዕራፍ ከተቀመጡት መካከል ከባለድርሻ አካላት ጋር  ምክክር ማድረግ፣ ስፖርት ክለቡን ማዋቀርና ማደራጀት፣ ከስፖርት ክለቡ አካላት (አሰልጣኞች እና ተጫዋቾች) ለተነሱና ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት የሚገኙበት ሲሆን በሁለተኛው ምዕራፍ ለስፖርት ክለቡ አስፈላጊ ግብዐቶችን ከማሟላት ጋር በተያያዘ የመጫወቻ ሜዳውንና በዙሪያው ሊኖሩ የሚገባቸውን አገልግሎቶች በሚፈለገው ሁኔታ ማስተካከል፣ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ አውቶብሶችን መግዛት፣ የክለቡን አሰልጣኞችና የቡድን መሪዎች አቅም የማጎልበት ስራዎችን መስራት፣ ክለቡ በተወሰነ መልኩ ወጪውን የሚሸፍንበትን ገቢ ማስገኛ ስራዎች መስራት (ጎፋ ሜዳ በዋናው መንገድ ላይ የሚገኝ በመሆኑ የተለያዩ ለኪራይ አገልግሎት የሚውሉ ክፍሎችን ማሰራትና በጀርባው ደግሞ መቀየሪያ፣ ማስተማሪያ፣ ማረፊያ፣ መታጠቢያና ሌሎች አገልግሎቶችን የሚሰጡ ክፍሎችን ማሰራት)፣ ከተቋሞቻችን ጋር ከሚሰሩ አካላት ጋር ግንኙነት በማድረግ የተለያዩ እገዛዎችን ማግኘት (የትጥቅ፣ የስልጠናና ሌሎችንም እገዛዎችን) ማግኘት ይገኙበታል፡፡ በምንገዛቸው አውቶቡሶች ላይ የክለቡ ባለውለታዎች ፎቶ የሚለጠፍ ይሆናል። ከምስረታው ጀምሮ በተጫዋችነት፣ በአሰልጣኝነትና በተለያየ ዘርፍ አስተዋጽኦ ያበረከቱ  የእነ ጋሽ ሀጎስ ደስታ፣ የእነ ሼኪና የሌሎችም…


ወደ ኃላፊነት ከመጣችሁ በኋላ የቀድሞው ተጨዋቾችን እና ደጋፊዎችን አነጋግራችኋል። ይህ ከምን አንፃር ነው ቀጣይነትስ ይኖረዋል ወይ ? 

 

በአጭር ጊዜ ዕቅዳችን ውስጥ መጀመሪያ ከተቀመጡት ተግባራት አንዱና ዋነኛው ስለነበረ ነው ያንን የምክክር መድረክ ያዘጋጀነው። በነገራችን ላይ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ነው የጠራነው በተለያየ መልኩ በክለባችን ተሳትፎ የነበራቸውን አካላት በሙሉ፤ ዓላማው ከክለቡ ባለድርሻ አካላት ጋር ክለባችንን እንዴት እናጠናክረው በሚለው ጉዳይ ላይ ለመወያየትና ለመስራት ያሰብናቸውን ስራዎች ዕቅድ አቅርበን ግብዐት ለማግኘት ነው፡፡ ቀጣይነቱን በተመለከተ በየሶስት ወሩ በመደበኛነት የሚደረግ ሲሆን ክለባችን እንደ አዲስ በመደራጀት ላይ በመሆኑ በማደራጀትና ወደ ውድድር በመግባት ሂደት ግን ተጨማሪ መድረኮች ይኖሩናል፡፡ 


በሁሉም እርከን ላይ አሰልጣኞችን መምረጣችሁን አስታውቃችኋል። የአመራረጥ ሂደቱና አካሄዱ እንዴት ነበር ? 

 

አሁን ባለው ሁኔታ ክለባችንን ለማደራጀት ያለን ጊዜ በጣም አጭር ነው፡፡ መጀመሪያ ባደረግነው የስራ አመራር ቦርድ ስብሰባ በተቻለ ፍጥነት አሰልጣኞችን በመምረጥ ቡድናቸውን እንዲያደራጁ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት ለሁሉም ቡድኖች ዕጩ ቴክኒክ ዳይሬክተሮችን ፣ አሰልጣኞችንና የቡድን መሪዎችን ሊያቀርብ የሚችል አካል ሁለት ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ አንድ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የመረጥን ሲሆን ከደጋፊ ማህበር ሁለት አባላት እንዲሳተፉ በአጠቃላይ አምስት አባላት ያሉት ቡድን እንዲዋቀርና ስራውን እንዲሰራ በቦርዱ አቅጣጫ ተሰጥቷል፡፡ ቡድኑ በሶስት ቀናት ስራውን አጠናቆ ውጤቱን በፖስታ አሽጎ አቅርቧል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ሀሙስ ነሐሴ 24 ቀን 2010 ዓ.ም. በተደረገው የውይት መድረክ የተሰጡ ሀሳቦችንም መነሻ በማድረግ ቅዳሜ ነሐሴ 26 ቀን 2010 ዓ.ም. የስራ አመራር ቦርዱ የቀረበውን ፖስታ በመክፈትና የተሰጡ አስተያየተቶችን መሰረት በማድረግ መረጣውን አካሂዷል፡፡ የተቋቋመው ቡድን ያቀረባቸውን ዕጩዎች በአብዛኛው የተቀበለ ሲሆን የተወሰኑ ማስተካከያዎችን አድርጓል፡፡ ለዋናው የወንዶች እግር ኳስ ቡድን ቴክኒክ ዳይሬክተርና አሰልጣኝ የቀረቡት ዕጩዎች በሙሉ ድምጽ ተቀባይነት ካገኙት መካከል ናቸው፡፡ በክለባችን ተጫውተው ያሳለፉና ለእግር ኳስ ትልቅ ፍቅርና ችሎታ ያላቸው በተለያየ ምክንያት ርቀው የቆዩ ውድ ልጆቻችን ወደ ክለባቸው እንዲመለሱ አድርገናል፡፡ አቅም እንዳላቸውና መልካም ነገር እንደሚሰሩ ተስፋ አለን ያላቸውን እውቀትና ችሎታ ለማሳደግ በቀጣይ የተለያዩ ስልጠናዎችን የሚያገኙበትን ሁኔታ እናመቻቻለን፡፡ የምርጫው ውጤት በግልጽ እንዲለጠፍና የተመረጡ አካላትም በተሰጠው ጊዜ ገደብ ሪፖርት እንዲያደርጉ እንዲገለጽላቸውም በቦርድ በተሰጠው አቅጣጫ መሰረት መረጃው ተለጥፏል፡፡ 


ኢትዮ ኤሌክትሪክ እንደ ንግድ ባንክ ከመፍረስ ድኗል። በቀጣይስ እንደነ መድን በከፍተኛ ሊጉ ቆይቶ በወጣቶች ላይ ለመስራት ያስባል ወይስ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ዳግም በፍጥነት ለመመለስ ?  

 

ለስፖርት ፍቅር እንዳለው እንደየትኛውም ዜጋ እንደ ባንክና ሙገር ያሉ ክለቦች በመፍረሳቸው አዝኛለሁ፡፡ ክለባችን ከ57 አመት በላይ ታሪክ ያለው የዛሬን አያድርገውና የበርካታ ክለቦች ደጋፊዎች ሁለተኛ ተመራጭ ክለብ ነበር፡፡ ይህ የሆነው በሁለት ምክንያት ይመስለኛል በውጤት በታጀበ ማራኪና ድንቅ አጨዋወቱ እና በታዳጊዎች ላይ በነበረው ከፍተኛ እምነት፡፡ አላማችን ጠንክረን ሰርተን ወደ ፕሪምየር ሊጉ መመለስ እና በሊጉም መልካም አጨዋወትን የሚከተል ጠንካራ ተፎካካሪ ቡድን መሆን ነው፡፡ ይህ ማለት በታዳጊዎች ላይ አንሰራም ማለት አይደለም። ዋነኛ ትኩረታችን የሚሆኑት ታዳጊዎች ናቸው፤ ክለባችን ታዳጊዎችን በማፍራት ከሚጠቀሱ ክለቦች መካከል አንዱ በመሆኑ ይህንን ለመመለስ ነው የምንሰራው፡፡ 


በዋናው የወንዶች ቡድን ውስጥ ኮንትራት ካላቸው ተጨዋቾች ጋር በምን መልኩ ለመቀጠል አስባችኋል? 

 

በዋናው የወንዶች እግር ኳስ ቡድን 17 ውል ያላቸው ተጫዋቾች አሉን፡፡ በተለያየ ምክንያት ከቡድናችን መልቀቂያ መውሰድ የሚፈልጉ ተጫዋቾችን የማስቀረት ፍላጎት የለንም። መልቀቂያ ስንሰጥ ግን በውላችን መሰረት ለክለባችን መከፈል ያለበትን የገንዘብ መጠን አስቀምጠናል፡፡ ይህንን ስናደርግ ለክለባችን የቻሉትን ሁሉ ሲያደርጉ የቆዩ ከአምስት አመት በላይ አገልግሎት ያላቸውን ተጫዋቾቻችንን ለክለባችን ለሰሩት ውለታ አብረውን እያሉ ብቻ ሳይሆን ሲለዩንም ማመስገን ተገቢ በመሆኑ በልዩ ሁኔታ የምናይላቸው ይሆናል፡፡ ተጫዋቾቹ ለነበራቸው መልካም ስነ ምግባርና አገልግሎት ይህንን ማድረግ ክለባችን ላገለገሉት ዕውቅና የሚሰጥ መሆኑን የሚያሳይና በቀጣይም ሌሎች በተመሳሳይ መልኩ እንዲያገለግሉት የሚያደርግ በመሆኑ ይህንን እናደርጋለን፡፡ 


ክለቡ ሁለት ጊዜ የፕሪምየር ሊጉ ቻምፒዮን ከመሆኑ በላይ በታዳጊዎች ላይ በሚጥለው ዕምነቱ ይታወቃል። ይህን ታሪኩን የመመለስ ሀሳቡ እስከምንድረስ ነው ? ከአጭር ጊዜ ዕቅዱ ጋርስ በምን መልኩ ለማጣጣም ምን ያስባል ?  
ከላይ እንደገለጽኩልህ ክለባችን የበርካታ ክለቦች ደጋፊዎች ሁለተኛ ተመራጭ ክለብ ነበር፡፡ የደጋፊዎች ብቻ አይደለም የታዳጊ ተጫዋቾችም ምርጫ ነበር። ምክንያቱም በታዳጊዎች ላይ የነበረው እምነትና የሚሰጠው ዕድል ነው፡፡ ይህ መልካም ነገር ክለባችን ይታወቅበት የነበረና እኛም ለማስቀጠል የምንፈልገው ነው። ከዚህ ዓመት ጀምሮ ለታዳጊዎች ልዩ ትኩረት ሰጥተን ለመስራት ነው ያሰብነው። ትኩረት ስንሰጥ ደግሞ ከተጫዋቾቹና አሰልጣኞቹ ደመወዝ ጀምሮ ማየት ስለሚገባ በዚህ ላይ ማስተካከያ አድርገናል፡፡ በአንድ ጊዜ ዋናውን የእግር ኳስ ቡድን በታዳጊዎች እንሞላዋለን እያልኩህ አይደለም። ነገርግን ከዚህ ዓመት ጀምሮ ይህንን ስራ ትኩረት ሰጥተን የምንሰራበት መሆኑን አጽንኦት ለመስጠት ነው፡፡ ለዚህም ነው የተጫዋቾች ምልመላ ቡድን ማዋቀር ያስፈለገው፡፡ ቴክኒክ ዳይሬክተሮቻችንም ሆኑ አሰልጣኞች ይህንን ነገር የሚያውቁ ስለሆነ በዚህ ረገድ ከፍተኛ ስራ ይሰራሉ፡፡  


ለክለቡ ነባር ለሆኑ እና ከክለቡ ውጤት መጥፋት ጋር ለጠፉ ደጋፊዎች ምን መልዕክት አለዎት? ምንስ ተስፋ ያድርጉ? 

 

ክለባችን በርካታ ደጋፊዎች የነበሩት ክለብ ነው፡፡ ቅድም እንደገለጽኩልህ ክለባችን በሚገዛቸው አውቶቡሶች ላይ እንደ ሼኪና ጋሽ በቄ የመሳሰሉ ደጋፊዎችን ፎቶ ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምላሽ ባይሆንም ለማስታወሻና ያለንን አድናቆት ለመግለጽ የምንለጥፍ ይሆናል፡፡ ባለፉት ዓመታት በነበሩት ሁኔታዎች ክለባችን የነበረውን ደጋፊ ብቻ ሳይሆን ስምም አጥቷል፡፡ በዚህ ሁሉ ሁኔታ ውስጥ ግን ደጋፊዎች ክለቡን ከመደገፍ አልታቀቡም፤ ከመደገፍም አልፈው በክለባችን መሰራት የነበረባቸውን ስራዎች ሲሰሩ የነበሩ ደጋፊዎችም አሉ፡፡ በዚህ አጋጣሚ ለደጋፊዎች ያለኝን አድናቆትና ምስጋና ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡ ክለቡ በርካታ ባለድርሻ አካላት አሉት ደጋፊዎች ደግሞ በቀዳሚነት የሚነሱ ናቸው። ደጋፊዎች ክለባቸውን በተሻለ ሁኔታ መደገፍና መርዳት የሚችሉት በተቀናጀና በተደራጀ አግባብ ሲሰሩ በመሆኑ ከዚህ በፊት ከነበረው በበለጠ ተደራጅተውና አንድ ሆነው ክለባቸውን መደገፍ ይኖርባቸዋል፡፡ የተደራጀ የደጋፊ ማህበር ስላለ ይህንን ለማድረግ የሚያስቸግር ነገር አይኖርም፡፡ በቀጣይ ደግሞ የቀድሞ የኤሌክትሪክ እግር ኳስ ክለብ ተጫዋቾች ማህበር እንዲመሰረት የምናግዝ ይሆናል፡፡ ይህ በሌሎች የስፖርት ዓይነቶችም ይቀጥላል፡፡ ተስፋ የምናደረገው በጋራ ነው ክለባችንን ወደ ቀድሞ ታሪኩ መመለስ ! ይህ ደግሞ በመፈለግና በመመኘት ብቻ የሚመጣ አይደለም ጥረትና ህብረት ይፈልጋል፡፡ ስለዚህ ሁሉም ባለ ድርሻ አካል ሚናውን አውቆ የበኩሉን መወጣት ይኖርበታል ይህ ከሆነ ተስፋችን/ ዕቅዳችን የማይሳካበት ምንም ምክንያት አይኖርም፡፡