ካፍ ወደ ኤሊት ደረጃ የሚያድጉ ዳኞችን ለመለየት የሚያከናውነው ፈተና ላይ ኢትዮጵያዊው ኢንተርናሽናል ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ ይካፈላል።
በሩዋንዳ በሚከናወነው ፈተና እና ስልጠና ላይ ከ36 የአፍሪካ አገራት ውስጥ የተወጣጡ ዳኞች የሚሳተፉ ሲሆን ኢትዮጵያዊው ኢንተርናሽናል ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ የሚሳተፍ መሆኑ ታውቋል። በካፍ እና በፊፋ አማካይነት የተዘጋጀው ይህ ፈተና የተለያዩ የስልጠና እርከኖች ያሉት ሲሆን የመጀመሪያው የአካል ብቃት ፈተና ነው። ይህን ፈተና ያለፉ ዳኞች በካፍ ሙሉ ወጪ ተሸፍኖላቸው የሜዳ ላይ እና የክፍል ውስጥ ተጨማሪ ስልጠና ሲያገኙ የቫር ቴክኖሎጂን ጨምሮ አዳዲስ የፊፋ ህጎች ስልጠናን ያካትታል። የአካል ብቃት ፈተናውን የሚወድቅ ዳኛ ግን ወጪው በሀገሩ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን የሚሸፈን ነው የሚሆነው።
በ2018 የኢንተርናሽናል ባጅ ያገኘው ቴዎድሮስ ምትኩ በግንቦት ወር ካይሮ ላይ ከተሰጠ ስልጠና በኋላ ይህን እድል ሲያገኝ ለሁለተኛ ጊዜ ነው። በ2010 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከሁሉም ዳኞች ከፍተኛ ቁጥር ያለው ጨዋታ የመራው ቴዎድሮስ ጳጉሜ 2 የሚጀመረው ፈተና እና ስልጠና በብቃት ከተወጣ ወደ ኤሊት ቢ ደረጃ የሚያድግ ይሆናል። ይህም አህጉር አቀፍ ውድድሮች ላይ ለመዳኘት እድል የሚፈጥርለት እና ወደ ኤሊት ኤ ደረጃ ለማደግ የሚያንደረድረው ይሆናል።
የካፍ ኤሊት ኤ ደረጃ ላይ በወንዶች በዓምላክ ተሰማ፣ በሴቶች ሊዲያ ታፈሰ የሚገኙ ሲሆን ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ተመስገን ሳሙኤል ዘንድሮ ወደ ኤሊት ኤ ደረጃ ማደጉ የሚታወስ ነው።
በተያየዘ ዜና ሁለት ኮሚሽነሮች ወደ ጆሀንስ በርግ ለስልጠና ተጉዘዋል። ከ24 አፍሪካ ሀገራት የተወጣጡ ኮሚሽነሮች የሚሳተፋበት ይህ ስልጠና በሁለት ጎራ ተከፍሎ የሚሰጥ ሲሆን በፊትነስ ኢንስትራክተርነት እንዲሁም በቴክንኒካል ኢንስትራክተርነት ስልጠና የሚሰጥ ይሆናል። በዚህ ስልጠና ላየም በፊትነስ ኃይለመላክ ተሰማ እንዲሁም ግዛቴ አለሙ ደግሞ በኢንስትራክተርነት በኢትዮጵያ በኩል በፊፋ እና በካፍ ጥሪ የተደረገላቸው ኮሚሽነሮች ናቸው።