” በሁሉም ተጫዋቾች ውስጥ ያለው አንድ አይነት የማሸነፍ መንፈስ ጠንካራ ጎናችን ነው ” የሽረ አምበል ሙሉጌታ ዓንዶም

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ወሳኝ የመለያ ጨዋታ ትላንት ሀዋሳ ላይ በጅማ አባ ቡና እና ሽረ እንዳሥላሴ መካከል ተከናውኖ ሽረ 2-1 በማሸነፍ በታሪኩ ለመጀመርያ ጊዜ ወደ ፕሪምየር ሊጉ አድጓል። የቡድኑ አምበል የሆነው ሙሉጌታ ዓንዶም የትላንቱ ድል እና የውድድር ዘመኑ ጉዟቸውን አስመልክቶ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርጓል።

የውድድር ዓመቱ ጉዟችሁ ምን ይመስል ነበር?

የውድድር ዓመቱ በጣም አስቸጋሪ ነበር። ዓመቱን ፈታኝ ካደረጉብን ጉዳዮች ዋንኛው ደግሞ አብዛኛውን ጨዋታችንን ከሜዳችን ውጪ ማድረጋችን ነው። ሆኖም በስተመጨረሻ ሁሉንም ተግዳሮቶች ተወጥተን እንዲሁም እግዚአብሔር ረድቶን የምንፈልገውን አሳክተናል።

በጨዋታው (ከአባ ቡና ጋር) በመጀመሪያው አጋማሽ ተበልጣችሁ ነበር። ከእረፍት መልስ ግን ተለውጣችሁ በመግባት አሸንፋችኋል። የለውጡ መነሻ ምን ነበር?

መጀመሪያ ይዘነው የገባነው አጨዋወት ጥንቃቄ አድርገን መጫወትን ነበር። የእነሱን አጨዋወት ለማጥናት ነበር። በዚህም ምክንያት አባ ቡናዎች የተሻለ ተንቀሳቅሰዋል። ከእረፍት መልስ ግን ሙሉ በሙሉ አቅማችችንን አውጥተን ተጫውተናል። አሰልጣኙም የተጫዋች እና የታክቲክ ለውጥ አድርጎ መግባቱ ለድለችን አስተዋጽኦ ነበረው። በእረፍት ሰዓት መልበሻ ክፍል ወረስጥ አሰልጣኛችን (ዳንኤል ፀኃዬ) ሙሉ አቅማችንን ከተጠቀምን እንደምናሸንፍ ሲነግረን ነበር። እኛም 1-0 ተመሪነታችንን ቀልብሰን አሸንፈን እንደምንወጣ እርግጠኛ ነበርን። ይህንንም አሳክተናል።

የቡድኑ ጠንካራ እና ደካማ ጎኖች በአንተ እይታ ምንድን ናቸው?

ጠንካራ ጎናችን በሁሉም ተጫዋቾች ውስጥ ያለው አንድ አይነት የማሸነፍ መንፈስ ነበር። ስንጫወትም ከግል እንቅስቃሴ ይልቅ የቡድን ጨዋታ ነበር የምናጫወተው። እንደ ቡድን ስትጫወት የተሻለ ነገር ይገኛል። ይህ ጠንካራ ጎናችን ነው ብለን እናምናለን። ደካማ ጎናችን፤ የፋይናስ ችግር ነበር። ያንንም ቢሆን ተቋቋመን እዚህ ደርሰናል።

አሁን ወደ ፕሪምየር ሊጉ ገብታችኋል። ሊጉ የራሱ የሆነ ባህርይ አለው። ለመጀመሪያ ጊዜ ከማደጋችሁ እና ዘግይታቹ በመግባታቹ ከዝግጅት ጊዜ ማጠር አንፃር ምን አይነት ስጋት ይፈጥራል?

ይህ የአሰልጣኙ ስራ ነው የሚመስለኝ። እንደኔ እይታ ግን የልምድ ጉዳይ ነው። የፕሪምየር ሊግ ቡድኖችን በቅድመ ውድድር ጨዋታዎች ላይ ስንገጥም የልምድ አስፈላጊነትን አይተንበታል። ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች መሰብስብ ከቻልን እንዲሁም ፌዴሬሽኑ የእኛ አይነት ቡድንን ታሳቢ አድርጎ ውድድሩን ቢጀምር ፋታ ልናገኝ እንችላለን። ከከፍተኛ ሊግ አድጎ በፕሪምየር ሊግ ተፎካካሪ መሆን እና ዋንጫ ማንሳት እንደሚቻል መቐለ ከተማ እና ጅማ አባ ጅፋር ዘንድሮ አሳይተውናል።

በሽረ ቡድን ውስጥ የተለየ ነገር ምንድነው?

ህብረታችን! በቃ ፍቅራችን የፋይናስ ችግራችንን እንዳናይ አድርጎናል። ከኛ ደሞዝ ይልቅ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ነገሮች እንዲከናወኑበት ይደረግ ነበር። የኛ ደሞዝ እስከ ሶስት ወር ድረስ ሳይከፈል ቢቆይም የኛ ደሞዝ የትም አይሄድም በማለት ለሚያስፈልገን ነገር ቅድሚያ ሰጥተናል።

ስለ አሰልጣኝ ዳንኤል ምን ትላለህ? ቡድኑ ወደ ከፍተኛ ሊግ ያደገው ባለፈው አመት ነበር። ባደገበት ዓመት ተፎካካሪ መሆን ችሎ ነበር። ዘንድሮ ደግሞ ወደ ፕሪምየር ሊግ አሳድጎታል…

ዳንኤል ፀሀዬ ማለት ባለሙሉ ስብእና ባለቤት ነው። ለኛ ጥንካሬ አንዱ ተጠቃሽ እርሱ ነው። በቡድኑ ውስጥ የሚገኙ 27 ተጫዋቾችን እኩል አድርጎ ነው የሚመለከተን። በስራ የሚያምን አሰልጣኝ ነው፤ ይህም በመሆኑ አብረን ለዚህ ደርሰናል።