የከፍተኛ ሊጉ ቻምፒዮን በመሆን ከስምንት ዓመት በኋላ ዳግም ወደ ፕሪምየር ሊግ የተመለሰው ደቡብ ፖሊስ ዛሬ ምሽት በሀዋሳ ኃይሌ ሪዞርት ለቡድኑ አሰልጣኞች እና ተጫዋቾች ሽልማት እና የእራት ግብዣን አካሂዷል፡፡
በ1996 የተመሰረተው እና በ1999 ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አድጎ ከሶስት ዓመታት በኋላ ዳግም ከሊጉ በመውረድ ለስምንት ዓመታት በከፍተኛ ሊግ ሲሳተፍ ቆይቶ በዘንድሮው የከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ በ30ኛ ሳምንት ድሬዳዋ ፖሊስን በመርታት መግባቱን ያረጋጠጠው ደቡብ ፖሊስ የምድብ ሀ አሸናፊው ባህር ዳር ከተማን አዳማ ላይ 1-0 በማሸነፍ የ2010 የከፍተኛ ሊግ ቻምፒዮን በመሆን አጠናቋል። ክለቡ ዛሬ ወደ ሀዋሳ ሲገባ ደማቅ አቀባበል ከተደረገለት በኋላ በሀዋሳ ኃይሌ ሪዞርት ምሽት 1 ሰዓት ላይ የሽልማት እና የእራት ግብዣ መርሐ ግብር ተካሂደል።
በስነ-ስርዓቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሚሊዮን ማቲዮስ እና የደቡብ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር እና የክለቡ የበላይ ጠባቂ ቴዎድሮስ ወ/ሚካኤል ተገኝተው ንግግር እና ሽልማት አበርክተዋል። ኮሚሽነር ቴዎድሮስ በንግግራቸው “ክለቡ ፈታኝ ዓመትን አሳልፏል ከፍተኛ የፋይናንስ ችግሮች ነበሩበት። ፋይናንሱም ከሰራዊቱ የሚሰበሰብ በመሆኑ ተግዳሮቹ ብዙ ነበሩ። ይህ ክለብ ዳግም የመውረድ ስጋት እንዳይኖርበት ሁሉም የበኩሉን በመወጣት ከጎናችን ሊቆም ይገባል። የተመዘገበው ውጤት ግን እጅግ የሚያኮራ ቢሆንም ቀጣይ ብዙ ስራዎች አሉብን። ለተመዘገበው ድል ግን እንኳን ደስ አላችሁ። ” ብለዋል።
በመቀጠል የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሚሊዮን ማቲዮስ ንግግር አድርገዋል። “ይህ ትልቅ ታሪክ ነው። ይህን ስል ፖሊስ የራሱ የስራ ተልዕኮ እያለበት ጎን ከጎን ለሀገራችን የስፖርት ዕድገት በመትጋት ውጤታማ ሲሆን መመልከት ማንም ሊክደው የማይገባ ሀቅ ነው። ስፖርት ካለው ቁልፍ የእድገት ምንጭነት አንፃር ሁሉም ይህን ክለብ በትኩረት እንዲጠነክር ሁሉም የድርሻውን መወጣት አለበት። ላደረጋቹህት ተጋድሎ እና ስኬት እንኳን ደስ አላችሁ። ይህን ትልቅ ተልዕኮ ደግሞ በተሻለ ዳግም ክለቡ ችግር እንዳይገጥመው በማንኛውም መልኩ የክልሉ መንግሥት እንደሚደግፍ ቃል እገባለሁ።” በማለት በቀጣይ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልፀዋል።
በመጨረሻም ለክለቡ አሰልጣኞች ተጫዋቾች እና አስተዋፅኦ ላደረጉት የቡድኑ አባላት በድምሩ ከ1 ሚሊየን ብር በላይ የማበረታቻ የገንዘብ እና የምስጋና ሰርተፊኬት የተበረከተ ሲሆን የእራት ግብዣ ተደርጎ፣ በቀጣይ ክለቡን ለመደገፍ የቃል መግቢያ ለተጋበዙ ባለሀብቶች እና ጥሪ ለተደረገላቸው ተሰጥቶ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ ተላልፏል። ክለቡ የከፍተኛ ሊግ የምድብ እና የአጠቃላይ አሸናፊ የሆነበትን ዋንጫ ለክለቡ የበላይ ጠባቂ ቴዎድሮስ ወ/ሚካኤል በአምበሎቹ በኩል ርክክብ ተደርጎ የስነ ስርዓቱ ፍፃሜ ሆኗል።
በተያያዘም የክለቡ ፕሬዝዳንት ኮማንደር ዳንኤል ገዛኸኝ ለሶከር ኢትዮጵያ እንደገለፁት ከሆነ ከቀጣዩ ረቡዕ ጀምሮ ክለቡ ወደ ዝውውር ገበያው ይገባል።