የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ማክሰኞ በተደረገ የመለያ ጨዋታ ሶስተኛውን አዳጊ ክለብ ለይቷል። ሽረ እንዳስላሴ ጅማ አባ ቡናን 2-1 በማሸነፍ በተመሰረተ በአምስተኛ ዓመቱ ወደ ፕሪምየር ሊግ ማደግ እንዲችል ከፍተኛውን ሚና የተወጡት አሰልጣኝ ዳንኤል ፀኃዬ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር በክለቡ ውጤታማነት ዙርያ ቆይታ አድርገዋል።
ክለቡ ካለበት ሁኔታ ተነስቶ ወደ ፕሪምየር ሊግ ለመግባት አቅዶ ነበር?
ከሚገባው በላይ! አምና ሽረ ስሄድ ፈልጌ አልነበረም። ቢያንስ በአሰልጣኝነት ባልሰራ እንኳን ለማገዝ በሚል አሰልጣኞችን አብሬ ሳፈላልግላቸው ነበር። ነገር ግን አሰልጣኞቹ የሚጠይቁት ደሞዝ እና የክለቡ ፋይናንስ የሚመጣጠን አልነበረም። በአካባቢው የሚገኝ አሰልጣኝ ደግሞ የሊጉን ፈተና መቋቋም ስለማይችል ለሶስት ወር ራሴ ልያዘው ብዬ ነበር የገባሁት። ስጀምረው ቡድኑ ገና ወደ ከፍተኛ ሊጉ ማደጉ ስለነበር ያስፈራ ነበር። ቀስ በቀስ ግን ራሴ ወደምፈልገው ሲስተም አስገብቸዋለሁ። አምናም በገባበት ዓመት ሶስተኛ ወጥቷል። ያኔ ክለቡ ለተጫዋች የሚከፍለው ከፍተኛ ደሞዝ 5 ሺህ ብር ነበር። በዚህ መንገድ ከመሐል ሀገር ተጫዋች ማምጣት እንደማይቻል ግልፅ ነው። ነገር ግን ቀድሞ በሰራሁባቸው ቦታዎች ባለኝ ትውውቅ፣ ከመቐለ እና ከወልዋሎ የተቀነሱ ተጫዋቾችን እንዲሁም በደደቢት የማውቀው ኄኖክ ኢሳይያስን በማሳመን ነበር በዝቅተኛ ደሞዝ ያመጣነው። በዚህ ሁኔታ ቡድናችን እየጠነከረ ሄዷል። እንደውም በሁለተኛው ዙር ሄኖክ ወደ ጅማ ባይሄድብን ኖሮ ወደ ፕሪምየር ሊግ መግባትም እንችል ነበር።
በዚህ ሁኔታ ዓመቱን ካጠናቀቅን በኋላ ዘንድሮውም የመቀጠል ሀሳብ አልነበረኝም። ሆኖም የህዝቡ፣ የክለቡ እና የአካባቢው ባለስልጣኖች እና የደጋፊው “አንድ ነገር ማድረግ አለብህ” የሚል ጫና እንድቆይ አድርጎኛል። በክረምቱ ጅላሎ፣ አሸናፊ እና ልደቱ የመሳሰሉ ተጫዋቾችን በማምጣት ቡነድናችንን ይበልጥ አጠናክረናል። ” እኛ ከምንከፍላቸው በተሻለ ሊከፍሏችሁ ይችላል። ታሪክ መስራት ከፈለጋችሁ ግን አኔ ጋር ኑ። በህይታችሁ ሙሉ የለፋችሁበትን ማግኘት ትችላላችሁ፤ ፕሪምየር ሊግ እንደምናድግ እርግጠኛ ነኝ።” ብዬ በማሳመን ነው ወደ ክለቡ ያመጣኋቸው። ሌላው ከአምና ልምዴ በመነሳት የጨዋታ መንገዴ ላይ ማሻሻያ አድርጌያለሁ። አምና ኳስ የሚቆጣጠር ቡድን ስለሰራሁ ብዙዎች የፕሪምየር ሊግ ቡድን ይመስላል ይሉኝ ነበር። በከፍተኛ ሊግ ሜዳዎች ኳስ መስርተህ በመቆጣጠር መጫወት አስቸጋሪ ነው። ይህን በመረዳት ለከፍተኛ ሊግ በሚሆን አጨዋወት እቅድ አውጥቼ ነው የተንቀሳቀስኩት። በዚህ ሒደት የተሰራ ቡድን በመሆኑ ፕሪምየር ሊግ ለመግባት አቅደን ነው ውድድር የጀመርነው። በመጨረሻ ተሳክቶልናል።
ቡድኑ በሁለቱም ዓመታት ወጥነት የሚታይበት እና የተረጋጋ ነበር። እንዲህ አይነት ቡድን ለመስራት የተጠቀምከው የተለየ ነገር ምንድነው?
ቡድኑን ራሴ ውስጥ አስገብቼ ነው ስሰራ የቆየሁት። በአእምሮ ረገድ ጠንካራ እንዲሆኑ ስንሰራ ቆይተናል። በሜዳቸን በምናደርገው ጨዋታ ማግኘት የሚገባንን ሁሉ ማግኘት እና ከሜዳ ውጪ በሚደረጉ ጨዋታዎችን በበላይነት ለመወጣት ቡድኔ በአእምሮ ረገድ እንዲዘጋጅ አደርጋለሁ። ከት/ቤት ጀምሮ ለሳይኮሎጂ የተለየ ትኩረት እሰጥ ነበር። ከፍ እያልኩ ስመጣ እና ወደ አሰልጣኞነቱ ስገባ አድማሴን ለማስፋት የተለያዩ መፅሀፎችን አነባለሁ። ይህ የአእምሮ ጥንካሬ የጠቀመን ይመስለኛል።
ከሜዳ ውጪ የመጫወት ፈታኝነትን እንዴት ትገልፀዋለህ? ቡድናችሁ የውድድር ዓመቱን 2/3ኛ ጨዋታዎች ከሜዳው ውጪ ነው ያደረገው…
አስቸጋሪ የነበረው ነገር ይህ ነበር። ብዙዎች እኛ ወደ ፕሪምየር ሊግ እንደምንገባ አላሰቡም ነበር። ነገር ግን ከአምና ጀምሮ ለሜዳ ውጪ ጨዋታዎች ከፍተኛ የአእምሮ ዝግጅት እናደርግ ነበር። በኢትዮጵያ እግርኳስ ከሜዳ ውጪ ስትጫወት እግርኳሳዊ በሆነ ጉዳይ ውጤትህ ላይ ጫና ሊፈጥሩ የሚችሉ ክለቦች ጥቂት ናቸው። አሁን ካለው የሀገሪቱ ሁኔታ አንፃር ካልሆነ በስተቀር በሜዳ እና ከሜዳ ውጪ የሚገደረጉ ጨዋታዎች ብዙም ለውጥ የላቸውም።
ከጅማ አባ ቡና ጋር በተደረገው ጨዋታ የመጀመርያ አጋማሽ ጥሩ አልነበራችሁም። በሁለተኛው አጋማሽ ደግሞ ጨዋታውን ተቆጣጥራችሁ ማሸነፍ ችላችኋል…
በጨዋታው ላይ እቅዶችን ለመቀያየር ሞክረናል። አንዳንዴ ከአሰልጣኝነትህ ደፍረህ የምትወስዳቸው እርምጃዎች አሉ። እነዚህ ውሳኔዎች ሊሳኩልህም፣ ላይሳካልህም ይችላሉ። ጎል ለማግባት አጥቅትህ መጫወት ቢኖርብህም ጥንቃቄ ግን መኖር አለበት። ከእረፍት በፊት ከፊት ለፊት እና መሀል ሜዳ ላይ የነበረው ትስስር ጥሩ አልነበረም። በመጀመሪያ አጋማሽ ትንሽ ተደናግጠው ነበር። አንደኛ ምክንያቱ ሜዳው ነው፤ ሜዳው አርቴፊሻል ነው። ሁለተኛ ቡድኑ ለዚህ የውድድር ምዕራፍ የደረሰው ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። 90 ደቂቃ በጣም ጭንቀት ውስጥ ነበሩ። እነዚህ ምክንያቶች መሰለኝ በመጀመርያው አጋማሽ ጥሩ ያላደረገን። በሁለተኛው አጋማሽ አሻሽለናል ፈጣሪ ይመስገን የምንፈልገውን ማሳካት ችለናል።
በቀጣይ ለፕሪምየር ሊጉ የዝግጅት ጊዜ ማጠር የሚያመጣባቹ ተፅዕኖን እንዴት ታየዋለህ?
ወደ ፕሪምየር ሊጉ መግባትን አሳክተናል። አሁን ደሞ ሊጉ ላይ የመቆየት ትልቁ ስራ ከፊታችን ይጠብቀናል። እኛ ዛሬ ነው (ቃለ መጠይቁ የተከናወነው በጨዋታው እለት ነው) መግባታችንን ያረጋገጥነው። እኛ የዓመቱን ውድድር ገና እየጨረስን የፕሪምየር ሊግ ክለቦች የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን ጀምረዋል። ይህ ደግሞ አስቸጋሪ ያደርገዋል። እኛ ዝግጅት የጀመርነው ነሐሴ 20 ነበር፤ ውድድሩ የተጠናቀቀው ነሐሴ 29 ነው። ይህ ደሞ ለተጫዋቾች ራሱ ምን ያህል አድካሚ እና አሰልቺ እንደሆነ ማየት ቀላል ነው። ተጫዋቾች በአካል ብቃት ብቻ ሳይሆን በአእምሮ ረገድም ይጎዳሉ። በቂ እረፍት ማግኘት መቻል አለባቸው። ዞሮ ዞሮ ፌዴሬሽኑ ይህን ከግምት ውስጥ ያስገባዋል ብለን እናስባለን። ለኛ ትንሽ የሚከብድብን የዝውውር ጉዳይ ነው፤ አብዘኛዎች ፈርመዋል፤ ሌሎቹን ብትፈልጋቸውም እንኳን በቀላሉ አታገኛቸውም። ከ6-7 ተጫዋቹች ወደ ቡድናችን መቀላቀል ከቻልን ቡድኑን ሙሉ ያደርገዋል። እኔ በበኩሌ ከፕሪምየር ሊግ ይህ የከፍተኛ ሊግ ውድድር በጣም ከፍተኛ ፈተና የበዛበት ነው። በፕሪምየር ሊጉ ጥራት ያላቸው ተጫዋቾች ሊኖሩ ይችላሉ። ይህም ሆኖ እንኳን ቡድናችን ላይ የተወሰነ ተጫዋቾች ከጨመርን መቆቆም እንችላለን፤ ታግለንም ቢሆን ቡድናችንን ማትረፍ እንችላለን።
ስለ ውልህ ጉዳይ ምን ትላለህ? በየዓመቱ ከክለቡ ለመልቀቅ እየተቃረብክ ከመሆኑ አንፃር..?
ቀደም ብሎ አንደኛው ዙር ላይ ብዙ ነገሮች ስለነበሩ ከቡድኑ መልቀቅ የሚቻልባቸው መንገዶች ነበሩ። ነገር ግን ቡድኑንን ለማስገባት ህልም ነበረኝ። በጥቅም ደረጃ ካየኸው ብዙ ነገሮች አልፎብኛል። የያዝኩት አላማ ራሴን ጎድቼም ቢሆን ቡድኑን መጥቀም አለብኝ የሚል ነበር። እግዚአብሔር ይመስገን ይህን አሳክተናል። ቡድኑ እዚህ ለመድረሱ ኃላፊነት ስላለብኝ ነው። ተወልጀም ያደጉበት አከባቢ ነው። ለጉና ለመጫወት ነው ከዛ የወጣሁት። አሁንም እዛ ነው ያለሁት፤ እንደምቀጥል ሙሉ ተስፋ አለኝ።
በ1990ዎቹ በጉና ባሳለፍከው የተጫዋችነት ዘመን በሊጉ ከሚጠቀሱ ድንቅ ተጫዋቾች አንዱ ነበርክ። በአሰልጣኝነት በደደቢት እና በብሔራዊ ቡድን ውስጥ በምክትልነት አሳልፋሀል። እንደተጫዋች ዘመንህ በዋና አሰልጣኝነት በሊጉ ደምቀህ ለመታየት ያለህ ዝግጁነት ምን ያህል ነው?
የኔ ትልቁ አላማ በእግር ኳስ አንድ ነገር ጥሎ ማለፍ ነው። ምክንያቱም ሽረ ስመጣ አማራጭ አጥቼ አይደለም። ከዚህ በፊት ደደቢትም ሆነ ብሔራዊ ቡድን ውስጥ በምክትልነት ሳሰለጥን ያገኘውት ልምድ አለ። ይህን መሰረት አድርጌ የጨዋታ ሂደት ማንበብን የተጫዋቾች ልዩ ብቃትን መለየትን አዳብሪያዋለሁ። ለዛም ነው ይህ አይነቱ ውጤት በአጭር ጌዜ የተመዘገበው። እኔ አስታውሳለሁ የሲ ላይሰንስ ስልጠና ልንወስድ የሻይ ሰዓት ላይ ጨዋታ ለማየት ስወጣ ነው ሀይደር ሸረፋን ያየሁት። ሀይደር ያኔ የኮሌጅ ተማሪ ነበር፤ የእግር ኳስ እንቅስቃሴው ጥሩ ነበር ከሱ ሌላ ሄኖክ ኢሳያስ፣ ሄኖክ ካሳሁን፣ ሰለሞን ሐብቴ፣ ምኞት ደበበ፣ ዘካርያስ ፍቅሬ የመሳሰሉትን ተጫዋቾችን በደደቢት ተስፋ ቡድን ሶስት አመት ቆይታ ያወጣኋቸው ልጆች ናቸው። ለብሔራዊ ቡድን ከ5 በላይ ተጫዋቹችን መመረጥ ችለዋል። ደደቢት እያለሁ ቡድኑን በዋናነት የማሰልጠን ሀሳብ እና ህልም ነበረኝ። እነዚህን ልጆች አሳድጌ በዋና ቡድን ውስጥ ጠንካራ ቡድን መስራት እችል ነበር። ያም አልሆነም፤ ለዛ ነው ለእረፍት ወደ ሽረ ስመጣ ቡድኑን የያዝኩት የኔ አላማ በመጀመሪያ ቡድኑን ወደ ሌላ ምዕራፍ መለወጥ ነው። እኔም ራሴን ሰርቼ አሳይበታለሁ ብዬ ስላመንኩኝ ነው። በዛው አከባቢ የነበሩ ልጆችም ተጠቃሚ እንዲሆኑ ልጆቹን አቅርቤ የማያቸው ሲሆን ቡድኑ ውስጥ ከወላይታ፣ ከአዲስ አበባ፣ ከባህርዳር፣ ከጎንደር ከኦሮሚያ ከብዙ ቦታ አምጥቻለሁ። እንደዚህ አይነት ስብስብ ይዘ ማደግ ስትችል በጣም ነው የሚያስደስትህ።
ስለዚህ በሽረ አዳዲስ ፊቶች እንጠብቅ?
አዳዲስ ልጆችን ለማብቃት ጌዜ ይፈልጋል። መቼም እንደሚታወቀው የራሱ የሆነ ፕሮሰስ አለው። በጊዜ ሒደት በርካታ ወጣቶችን አፈራለሁ ብዬ አምናለሁ።