በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ 30ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ወሎ ኮምቦልቻን 2-0 የረታው ደሴ ከተማ ከመውረድ ሲተርፍ ፌዴራል ፖሊስ በሽረ እንዳሥላሴ ተሸንፎ መውረዱ የሚታወስ ነው። ሆኖም ፌዴራል ፖሊስ በተሸነፍኩበት ጨዋታ ሽረዎች ያልተገባ ተጫዋች አሰልፈዋል የሚል ክስ በማስገባታቸው ወራጁ ክለብ ፌዴራል ፖሊስ ወይስ ደሴ ከተማ ይሆናል? የሚለው ጉዳይ በፌዴሬሽኑ ውሳኔ ላይ የተንጠለጠለ ሆኖ ሁለት ሳምንታትን አስቆጥሮ በመጨረሻም የፌዴሬሽኑ ውሳኔ ተሰምቷል።
የከፍተኛ ሊጉ ኮሚቴ የፌዴራልን ጉዳይ መርምሮ ክሱን ውድቅ በማድረግ በጨዋታው የተመዘገበው ውጤትን እንዳፀደቀ ታውቋል። ይህን ተከትሎም ፌዴራል ፖሊስ ወደ አንደኛ ሊጉ መውረዱ ሲረጋገጥ ደሴ ከተማ መትረፉን አረጋግጧል።
በጉዳዩ ዙርያ የከፍተኛ ሊግ ኮሜቴ ኃላፊዎችን ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ያልተሳካ ሲሆን የፌዴራል ፖሊስ ቡድን መሪ ኮማንደር በየነ በውሳኔው ክለቡ ማዘኑን እና የፌደረሽኑ ስራ በደንብ መጠናት እንዳለበት ገልፀው “ፌዴሬሽኑ ሽረ መልስ እንዲሰጥ በታዘዘው መሰረት ቅጣት የተላለፈባቸው ተጫዋቾች ማረፋቸውን እና ገንዘቡ ገቢ ማድረጉን ስለገለፀ የሚል ምላሽ ሰጥቷል። ሆኖም ግን ገንዘቡ የገባበትን ሰዓት ፌደረሽኑ አልጠቀሰም፤ ይህ እውነታን ግን እኛ አቅርበናል። በእውነት መስራት ለራስ ነው። እውነቱ እንዴት መቅረብ አለበት የሚለውን በጊዜ ሄደት የምናየው ነው። ለአሁኑ ግን ይግባኝ እንላለን።” ብለዋል።